በተስፋለም ወልደየስ
በኢትዮጵያ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተናን በ“ዲጂታል” ለመስጠት የሚያስፈልጉ “ታብሌቶችን” በሀገር ውስጥ ለማምረት እንቅስቃሴ መጀመሩን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ። ፈተናውን ደህንነቱን በጠበቀ መልኩ በ“ኦንላይን” ለመስጠት የሚያስችሉ የ“ሶፍትዌር እና ሲስተም” ስራዎች፤ ተቀማጭነታቸውን ውጭ ሀገር ባደረጉ ኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በመሰራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት፤ የመስሪያ ቤታቸውን የ2015 ዕቅድ እና የሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም፤ ጉዳዩ ለሚመለከተው የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ ሰኞ ህዳር 19፤ 2015 ባቀረቡበት ወቅት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ነው። በዛሬው ስብስባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የተዘጋጁ ዘጠኝ ጥያቄዎች ቀርበዋል።
የቋሚ ኮሚቴ አባል በሆኑት አቶ ፍሬው ተስፋዬ ከቀረቡት ከእነዚህ ጥያቄዎች ውስጥ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን የተመለከተው አንዱ ነበር። የፓርላማ አባሉ “የ12ኛ ክፍል ፈተናን በ’ኦንላይን’ ለማድረግ ታስቦ የነበረው ዕቅድ ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው? በዚህ ዓመትስ ምንድነው የሚጠበቀው?” ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን በ“ኦንላይን” ለመስጠት የታየዘው ዕቅድ እርሳቸው ወደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከመምጣታቸው አስቀድሞ የታሰበ መሆኑን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ መንደርደሪያ ላይ አንስተዋል። ዕቅዱ በዚህ ዓመት ግንቦት ወር በሚከናወነው ሀገር አቀፍ ፈተና ወቅት ተግባራዊ ይደረጋል የሚል “ጥርጣሬ” እንዳላቸውም ለፓርላማ አባላቱ አስረድተዋል።
ሀገር አቀፍ ፈተናውን በ“ዲጂታል” መልኩ ለመስጠት ተግዳሮት ሆኖ ያስቸገረው አንዱ ጉዳይ፤ ፈተናውን ለመስጠት የሚያስችሉ “ታብሌቶች” የመግዣ ዋጋ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመወደዱ ምክንያት እንደሆነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚያስፈልጉ “ታብሌቶች” ብዛት አንድ ሚሊዮን ገደማ መሆኑን የጠቀሱት የትምህርት ሚኒስትሩ፤ መሳሪያዎቹን ከውጭ ለማስመጣት “በጣም ውድ በመሆኑ” ዕቅዱ ተግባራዊ ሳይደረግ መቅረቱን አብራርተዋል።
የዘንድሮውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተና ይፈተናሉ ተብለው በእቅድ የተያዙ ተማሪዎች ብዛት 948, 322 እንደነበር ትምህርት ሚኒስቴር ዛሬ ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ በቀረበው ሪፖርቱ አመልክቷል። ከእነዚህ ተማሪዎች ውስጥ 98.8 በመቶው ያህሉ ፈተናውን ለመውሰድ በዩኒቨርስቲዎች ወደተዘጋጁ የፈተና ጣቢያዎች ገብተው እንደነበር ሪፖርቱ አመልክቷል።
ወደፊት በ“ኦንላይን” ለመስጠት ለታሰበው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና፤ የ“ታብሌት” አቅርቦት ችግር እንዳይፈጥር ከወዲሁ እንቅስቃሴ መጀመሩን ፕሮፌሰር ብርሃኑ በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ተናግረዋል። ትምህርት ሚኒስቴር የጀመረው እንቅስቃሴ “መሳሪያዎቹን ከውጭ ከማስገባት ይልቅ በሀገር ውስጥ ማምረት የሚቻልበት አቅም መገንባት ይኖርበታል” በሚል ዕሳቤ እንደሆነም አስረድተዋል።
“መጪው ጊዜ በፈተና ላይ ብቻ ሳይሆን በሌላም ጉዳይ የበለጠ ‘ዲጂታል’ እየሆነ የሚሄድ ከሆነ፤ ዜጎቻችን ለዚያ የሚያስፈልጋቸው ቁሳቁስ ያስፈልጋቸዋል በሚል ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጋር ውይይት ጀምረናል” ሲሉም የትምህርት ሚኒስትሩ በመስሪያ ቤታቸው እየተደረገ ነው ያሉትን ክንውን ገልጸዋል። ውይይቱ ከመንግስታዊው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በተጨማሪ “ታብሌት” የሚያመርቱ የውጭ ሀገር ኩባንያዎችን ጭምር ያካተተ እንደሆነም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ፤ በሀገር ውስጥ እንዲቋቋም ለታሰበው የ“ታብሌት” ፋብሪካ የመጀመሪያውን መዋዕለ ንዋይ እንዲያፈስስ ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት ጥር ወር በወጣ አዋጅ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከተመሰረተባቸው ዓላማዎች አንዱ፤ “የመንግስትን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም የኢንቨስትመንት ውጤታማነትን ማሳደግ እንዲሁም ተጨማሪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንደስትራቴጂያዊ መሳሪያ በመሆን” ማገልገል ነው።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስን ዓላማና ተግባር ለመወሰን በተመሳሳይ ወቅት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው ደንብ፤ ተቋሙ “አትራፊ ናቸው ብሎ በሚያምንባቸው ማንኛቸውም የንግድና የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ መዋዕለ ንዋይ ያፈሳል” ሲል ደንግጓል። በሀገር ውስጥ የሚቋቋመው የ“ታብሌት” ፋብሪካ ምርቶቹን ማምረት እስኪጀምር ድረስ ጊዜ እንደሚወስድ የገለጹት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ በዚህ ምክንያት ታብሌቶችን የመጠቀም “ተስፋ” ያለው በዘንድሮው የፈተና ወቅት ሳይሆን “በሚቀጥለው ጊዜ” እንደሆነ ጠቁመዋል።
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በ“ዲጂታል” ይሰጥ ቢባል፤ ከ“ታብሌት” አቅርቦት በተጨማሪ ሌሎች ችግሮችም አዲሱን አሰራር ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል በትምህርት ሚኒስትሩ ማብራሪያ ተነስቷል። በገጠር እና በከተማ መካከል ያለው ልዩነት እንዲሁም ተማሪዎች ለቴክኖሎጂ አጠቃቀም ያላቸው ቅርበት፤ ፕሮፌሰር ብርሃኑ በተግዳሮትነት ያነሷቸው ሌሎች ነጥቦች ናቸው።
እነዚህ ተግዳሮቶች “ተማሪዎቹን ምን አይነት ችግሮች ውስጥ ሊከቷቸው ይችላሉ?” የሚለው ታሳቢ መደረጉን የገለጹት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ በዚህም ምክንያት አዲሱን አሰራር በአንድ ጊዜ ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ “ድብልቅ (hybrid) አካሄድ ለመከተል” የሚያስችል ጥናት መካሄዱን አስረድተዋል። የትምህርት ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ ሰዎችን እና በውጭ ሃገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የዘርፉ ባለሙያዎችን ያሳተፈው ይህ ጥናት፤ የ“ኦንላይን” ፈተና ለመስጠት የሚያስችሉ የ“ሶፍትዌር እና ሲስተም” ስራዎችን ማዘጋጀት ያካተተ እንደሆነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል።
“ By the time ‘ታብሌቱ’ በሚደርስበት ጊዜ፤ ፈተናውን absolutely secure በሆነ መልኩ ልናካሄድ የምንችልበትን ሶፍትዌር እየገነባን ነው” ሲሉ ለፓርላማ አባላት የተናገሩት የትምህርት ሚኒስትሩ፤ እነዚህ የዝግጅት ስራዎች “hybrid” አካሄድን በመጠቀም ፈተና ለመስጠት በሚፈልግበት ጊዜ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ እንደሆነ አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)