በሃሚድ አወል
በኢትዮጵያ ተመዝግበው ፍቃድ ከተሰጣቸው የማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ውስጥ አምስተኛ የሆነው የካፋ ቴሌቪዥን፤ ከሁለት ወራት በኋላ መደበኛ የሳተላይት ስርጭቱን ሊጀምር እንደሆነ አስታወቀ። የቴሌቪዥን ጣቢያው አማርኛ እና እንግሊዘኛን ጨምሮ በአምስት ቋንቋዎች ዜና እና ፕሮግራሞችን ለማስተላለፍ ማቀዱ ተገልጿል።
ከአንድ ወር ገደማ በፊት የ24 ሰዓት የሙከራ ስርጭቱን የጀመረው የካፋ ቴሌቪዥን፤ መደበኛ ዝግጅቶቹን ለመጀመር ላለፈው አንድ ዓመት ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን የካፋ ቴሌቪዥን የዜና እና ፕሮግራም አስተባባሪ እና ከፍተኛ አርታኢ አቶ አዳሙ እሸቱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ጣቢያው በራሱ የሳተላይት ቻናል እያስተላለፈ በሚገኘው የሙከራ ስርጭቱ፤ የካፋ ዞንን ተፈጥሮ ሃብቶች እና ገጽታ “በሙዚቃ በማጀብ” እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።
የቴሌቪዥን ጣቢያው የራሱን የሳተላይት ቻናል ከመክፈቱ በፊት፤ ከደቡብ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት በገዛው የአየር ሰዓት ዜና እና ፕሮግራሞችን ላለፉት አምስት ዓመታት ሲያስተላልፍ ቆይቷል። እነዚህ ዝግጅቶች በደቡብ ቴሌቪዥን በሳምንት ለሁለት ቀናት እየተላለፉ የሚገኙት በካፊኛ ቋንቋ ነው።
የካፋ ቴሌቪዥን መደበኛ ስርጭቱን በሚጀምርበት ጊዜ፤ በካፋ ዞን በሚነገሩት የናኦ እና ጫራ ብሔሮች ቋንቋዎች ጨምሮ በአምስት ቋንቋዎች ዝግጅቶቹን የማስተላለፍ ዕቅድ እንዳለው አቶ አዳሙ ገልጸዋል። የቴሌቪዥን ጣቢያው ባለበት የፋይናንስ እጥረት ምክንያት በአምስቱም ቋንቋዎች ወደ ስርጭት ላይገባ እንደማይችል የጠቆሙት የዜና እና ፕሮግራም አስተባባሪው፤ በዚህ ዓመት መደበኛ ስርጭት ለመጀመር የታቀደው በአማርኛ እና ካፊኛ ቋንቋዎች ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።
የካፋ ቴሌቪዥን ድርጅት፤ ካሜራዎችን ጨምሮ ለቀጥታ ስርጭት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ግዢ በ15 ሚሊዮን ብር ገደማ የፈጸመው ከአምስት ዓመት በፊት መሆኑን ስራ አስኪያጁ አቶ አስራት ኃይሌ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በአዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ስር ላለው የካፋ ዞን መስተዳድር ምክር ቤት ተጠሪ የሆነው ድርጅቱ፤ በዞኑ አስተዳደር በተመደበ 90 ሚሊዮን ብር ወጪ ባለ አራት ወለል ህንጻ እያስገነባ ይገኛል።
ግንባታው ከሶስት ዓመት በፊት የተጀመረው የካፋ ቴሌቪዥን ህንጻ በጊዜ ባለመጠናቀቁ፤ ድርጅቱ የመስሪያ ቦታ ችግር እንዳለበት አቶ አዳሙ አመልክተዋል። ድርጅቱ አሁን የሚገለገልባቸውን ቢሮዎች በውሰት ያገኘው ከቦንጋ ኤፍ ኤም 94.7 ራዲዮ ጣቢያ ነው። የኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያው የሚተዳደረው በደቡብ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት ስር ነው።
የካፋ ቴሌቪዥን ያለበትን የመስሪያ ቦታ ችግር ለማቃለል፤ እየተገነባ ያለው የጣቢያው ህንጻ ሙሉ ለሙሉ ሳይጠናቀቅ ከፊሉን ለመጠቀም እንደተወሰነ አቶ አዳሙ ገልጸዋል። “[ህንጻው] ሙሉ በሙሉ ባያልቅም፤ ከላይ ያለው አልቆ እዚያ ላይ ስራ እየሰራን ደረጃ በደረጃ ለማጠናቀቅ ነው የተወሰነው” ብለዋል።
የካፋ ቴሌቪዥን ድርጅት በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ከተመዘገቡ አምስት የማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች መካከል ፍቃድ በማግኘት የመጨረሻው መሆኑን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከባለስልጣኑ ያገኘችው መረጃ ያሳያል። ባለስልጣኑ ከዚህ ቀደም በማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያነት ለተቋቋሙት የሲዳማ፣ ወላይታ፣ አዳማ እና ሃድያ ቴሌቪዥኖች ፈቃድ ሰጥቷል። የካፋ ቴሌቪዥን የባለስልጣኑን ፍቃድ ያገኘው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ነው።
የማህብረሰብ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተቋቋሙበት አካባቢ ካሉ የህብረተሰን ክፍሎች የተውጣጡ አባላት ባሉት ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚተዳደሩ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ ተጠሪነት ለጠቅላላ ጉባኤዎቹ መሆኑ በባለስልጣኑ መረጃ ሰፍሯል።
የካፋ ቴሌቪዥን ድርጅት በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ከተመዘገቡ አምስት የማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች መካከል ፍቃድ በማግኘት የመጨረሻው ነው
የካፋ ቴሌቪዥን 150 አባላት ያሉት ጠቅላላ ጉባኤ እንዳሉት የጣቢያው ስራ አስኪያጅ አቶ አስራት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የጠቅላላ ጉባኤው አባላት በካፋ ዞን ካሉት ሰባት የከተማ አስተዳደሮች እና 10 የገጠር ወረዳዎች የተውጣጡ መሆናቸውን የቴሌቪዥን ጣቢያው ስራ አስኪያጅ አስረድተዋል። ከጠቅላላ ጉባኤው ስር በዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ የሚመራ ሰባት አባላት ያሉት ቦርድ እንዳለም አቶ አስራት ጨምረው ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)