የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ ፓርላማውም ጭምር አጀንዳ ሊቀርጽለት እንደማይችል አሳሰበ 

በሃሚድ አወል

ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ ፓርላማውም ቢሆን አጀንዳዎች እንዲቀርጽለት እንደማይፈልግ አስታወቀ። አጀንዳ የማሰባሰብ እና የመቅረጽ ኃላፊነት በአዋጅ የተሰጠው ለኮሚሽኑ ብቻ መሆኑንም ገልጿል።

በአስራ አንድ ኮሚሽነሮች የሚመራው ኮሚሽን ይህን ያስታወቀው፤ የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ዛሬ ረቡዕ ህዳር 21፤ 2015 ባቀረበበት ወቅት ነው። በሱሉልታ ከተማ በሚገኘው የአፍሪካ አመራር ልህቀት ማዕከል በተካሄደው በዛሬው ስብስባ፤ ኮሚሽኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት በዋና ኮሚሽነር ፕ/ር መስፍን አርዓያ አማካኝነት ቀርበዋል። 

ከዋና ኮሚሽነሩ ሪፖርት በኋላ፤ የፓርላማ አባላቱ ያሏቸውን ጥያቄዎች እና አስተያየቶቻቸውን ሰንዝረዋል። በፓርላማ አባላቱ መካከል ከቀረቡ አስተያየቶች መካከል፤ የሀገራዊ ምክክሩ አጀንዳዎች ምን መምሰል እንዳለባቸው ጥቆማ ያቀረቡባቸው ይገኙበታል።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

አንድ የምክር ቤት አባል፤ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት፣ የፌደራል ስርዓት እና ታሪክ የምክክሩ “ቀዳሚ አጀንዳዎች” ሊሆኑ እንደሚገባ አስተያየት ሰጥተዋል። ሌላ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው “የሀገረ መንግስት ግንባታ እና የጋራ ታሪክ ጉዳይ ዋና አጀንዳዎች ናቸው” ሲሉ በሀገራዊ ምክክሩ ሊካተቱ ይገባቸዋል ያሏቸውን ዋነኛ ጉዳዮች አንስተዋል።  

የፓርላማ አባላቱ ይህን መሰል አስተያየት፤ በዛሬው ስብስባ በተገኙ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ተቃውሞ ገጥሞታል። ከኮሚሽነሮቹ አንዱ የሆኑት አቶ መላኩ ወልደማሪያም “ዛሬ የተገናኘነው ሪፖርት ለማቅረብ እንጂ አጀንዳ ለመሰብሰብ አይደለም” ብለዋል። “አጀንዳ set እንዲደረግልን አንፈልግም። እሱን በጣም በጥብቅ ነው የምንቃወመው” ሲሉ ጠንከር ባሉ ቃላት ቅሬታቸውን አሰምተዋል። 

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ትላንት ማክሰኞ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ ይህንኑ ጉዳይ ማንሳቱን አቶ መላኩ በምላሻቸው አስታውሰዋል። “ትላንት በሰጠነው መግለጫ አንዳንድ አካላት አጀንዳ ሊቀርጹልን እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው ብለን ገልጸናል። ይሄ ከአክብሮት ጋር ይሄን ምክር ቤትም ይመለከታል” ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ኮሚሽኑ ትላንት ለጋዜጠኞች ባሰራጨው መግለጫ፤ “በአዋጅ የተቋቋመው እና ህጋዊ ሰውነት ያለው፣ ስልጣን እና ኃላፊነት በህግ የተሰጠው አንድ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን መኖሩ እየታወቀ፤ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ አጀንዳ ለመስጠት የሚደረግ እንቅስቃሴ” መኖሩን አስታውቆ ነበር። በዛሬው ስብስባ ከተገኙ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አምስት ኮሚሽነሮች አንዱ የሆኑት አቶ መላኩ፤ አጀንዳ መቅረጽ በህግ ለኮሚሽኑ የተሰጠ ተግባር መሆኑን ለፓርላማ አባላቱ አስገንዝበዋል። 

አቶ መላኩ “አጀንዳ እንዴት እንደሚቀረጽ በግልጽ ተቀምጧል። በሌሎች ሀገራት ከነበረው ተሞክሮ በተለየ ሁኔታ እኛ አጀንዳ አልተሰጠንም” ሲሉም ተደምጠዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አዋጅ፤ በፖለቲካ እና በሀሳብ መሪዎች እንዲሁም በህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ያሉ ልዩነቶችን በጥናት እና በህዝባዊ ውይይቶች ወይም በሌሎች መንገዶች የሚለዩት በኮሚሽኑ እንደሆነ ደንግጓል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የለያቸውን ጉዳዮች መሰረት በማድረግ፤ የምክክር አጀንዳዎችን እንደሚቀርጽ፣ ምክክር እንዲደረግባቸው እንደሚያመቻች እንዲሁም ምክክሮችን እና ውይይቶችን እንደሚያሳልጥ በማቋቋሚያ አዋጁ ሰፍሯል።  አጀንዳዎች የሚመረጡበትን፣ በውይይቶች ላይ የሚሳተፉ አካላት የሚለዩበትን ስርዓት ለመዘርጋት፤ ደንብ እና መመሪያዎችን የማውጣት እና ስራ ላይ የማዋል ስልጣን በአዋጁ የተሰጠውም ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ነው። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ከአጀንዳ ቀረጻ በተጨማሪ በፓርላማ አባላት የተነሱት ሌሎች ጉዳዮች፤ የተሳታፊ ልየታ እና አካታችነት ላይ የሚያጠነጥኑ ነበሩ። ኮሚሽኑ አካል ጉዳተኞችን በምክክር ሂደቱ ተሳታፊ ለማድረግ ምን ያህል ርቀት እንደተጓዘ ከምክር ቤት አባላቱ ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል። አንድ የምክር ቤት አባል “አካል ጉዳተኞችን ለማካተት የተለየ ፕሮግራም መቅረጽ ያስፈልጋል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

ከኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች አንዷ የሆኑት ብሌን ገብረመድህን፤ ኮሚሽኑ ሰነዶችን በብሬል እና በምልክት ቋንቋ ጭምር እያዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል። ሌላኛው ኮሚሽነር ዶ/ር አምባዬ ኦጋቶ በተመሳሳይ “ሴቶች፣ ወንዶች፣ የአካል ጉዳተኞችን ጨምሮ የተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች ‘ተካትተዋል፤ አልተካተቱም’ የሚሉትን ነገሮች እናረጋግጣለን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)