በሽሬ ከተማ የቴሌኮም አገልግሎት “በጥቂት ቀናት” ወስጥ እንደሚጀምር ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ

በአማኑኤል ይልቃል

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ከተቋረጠባቸው የትግራይ ክልል ከተሞች ውስጥ አንዷ በሆነችው ሽሬ፤ “በጥቂት ቀናት” ውስጥ አገልግሎት እንደሚጀመር ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ። በከተማዋ አገልግሎቱን ለማስጀመር የተሰማራው የተቋሙ የጥገና ቡድን፤ በቴሌኮም መስመሩ ላይ ሙከራ እያደረገ መሆኑንም ገልጿል። 

መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ የጥገና ስራውን በሽሬ የጀመረው ካለፈው ሰኞ ጀምሮ መሆኑን የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ መሳይ ውብሸት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የጥገና ስራውን ለማከናወን የሚያስችል የኤሌክትሪክ አገልግሎት በከተማዋ ባለመኖሩ፤ ቡድኑ ስራዎችን እየሰራ ያለው በነዳጅ የሚንቀሳቀሱ ጄነሬተሮችን በመጠቀም መሆኑን አመልክተዋል። 

የኢትዮ ቴሌኮም የጥገና ቡድን በሽሬ ከተማ አገልግሎት ለማስጀመር በመጀመሪያ ቅድሚያ የሰጠው፤ “ጉዳት ለደረሰባቸው እና መስተካከል ለሚፈልጉ” የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች መሆኑን አቶ መሳይ አስረድተዋል። በከተማዋ የቴሌኮም መሰረት ልማት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን በትክክል ለማወቅ የጥገና ቡድኑ ሪፖርት ማቅረብ እንዳለበት የተናገሩት ቺፍ ኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰሩ ፤ አሁን ባለው መረጃ “የደረሰው ጉዳት ይህንን ያህል ነው” ለማለት እንደሚቸገሩ አስታውቀዋል።  

እስካሁን በተደረገው የጥገና ስራ፤ ለቡድኑ ግንኙነት የሚያገለግል የቴሌኮም አገልግሎት በሙከራ ደረጃ መጀመሩንም ጠቁመዋል። ይህ የሙከራ አገልግሎት “ህዝቡ መጠቀም በሚችልበት ደረጃ” አለመድረሱንም አቶ መሳይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። “አገልግሎት ሙሉ በሙሉ አልጀመርንም። ግን የጥገና ስራው የሚጠናቀቀው በጥቂት ቀናቶች ውስጥ ምናልባት በአንድ ሁለት ቀንም ሊሆን ይችላል” ብለዋል።

በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል የዛሬ ወር ገደማ ከተካሄደው የሰላም ንግግር በኋላ፤ ስምምነት ከተደረሰባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የነበረው በጦርነት ምክንያት የተቋረጡ “መሰረታዊ አገልግሎቶችን እንደገና ማስጀመር” የሚለው ነው። የሁለቱ ተፈላሚ ወገኖች የጦር አዛዦች በናይሮቢ በተገናኙበት ወቅትም፤ በትግራይ ክልል ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማስጀመር መሆኑን የተደራዳሪ ልዑካን መሪዎች ገልጸው ነበር።

ኢትዮ ቴሌኮም የፌደራል መንግስት በተቆጣጠራቸው የክልሉ አካባቢዎች ላይ “እግር በእግር” በመግባት አገልግሎት ለማስጀመር እየሰራ መሆኑን የተቋሙ ቺፍ ኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ኢትዮ ቴሌኮም፤ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መፈረም ሁለት ቀናት በኋላ በጦርነት ውስጥ በቆዩ ዘጠኝ አካባቢዎች የቴሌኮም አገልግሎት መጀመሩን ይፋ አደርጎ ነበር። የቴሌኮም አገልግሎት እንደተጀመረ የተገለጸባቸው ከተሞች፤ አላማጣ፣ ኮረም፣ ዓዲ አርቃይ፣ ጸለምት፣ ጪሮ ለና፣ ጎብዬ ቆቦ፣ ቆቦ ሮቢጥ፣ ዞብል እና ዋጃ ናቸው።

ከዚህ በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ፤ ከሽሬ በ80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ማይጸብሪ ከተማ የቴሌኮም አገልግሎት እንዲጀምር መደረጉን አቶ መሳይ ገልጸዋል። ኢትዮ ቴሌኮም የሚያሰማራው የጥገና ቡድን ከሽሬ ከተማ በኋላ በቀጣይ ከተሞች ላይ አገልግሎት የማስጀመር ስራውን እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። ኢትዮ ቴሌኮም ወደ አድዋ እና አክሱም ከተሞች የጥገና ቡድን ልኮ እንደው ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ቺፍ ኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰሩ፤ “እርሱ ገና ነው። አሁን እንዲህ ነው ብለን መናገር አንችልም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)