በአማኑኤል ይልቃል
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲን በመወከል የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባል በሆኑት አቶ ታረቀኝ ደግፌ ላይ ሰባት የምርመራ ቀናት በፍርድ ቤት መፍቀዱን ጠበቃቸው አስታወቁ። የምርመራ ጊዜውን የፈቀደው የደቡብ ክልል የሀዋሳ ማዕከል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤ “በደረሰባቸው ድብደባ ጉዳት ለደረሰባቸው” አቶ ታረቀኝ ህክምና እንዲያገኙ ትዕዛዝ መስጠቱን ጠበቃቸው ገልጸዋል።
የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮውን የፈቀደው እና ትዕዛዙን ያስተላለፈው፤ ትላንት ረቡዕ ህዳር 21 ከሰዓት በዋለው ችሎት መሆኑን ከተጠርጣሪው ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ አብዱረዛቅ ነስሩ ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በ2013 ዓ.ም. በተደረገው ሀገራዊ ምርጫ በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ለደቡብ ክልል ምክር ቤት አባልነት የተመረጡት አቶ ታረቀኝ፤ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፈው እሁድ ህዳር 17፤ 2015 ነበር።
በአዲስ አበባ ከተማ በፖሊስ የተያዙት አቶ ታረቀኝ፤ ወደ ሀዋሳ ከተማ ከተወሰዱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ከሰዓት እንደነበር ጠበቃቸው ገልጸዋል። የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባሉ በሀዋሳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ ሰንብት ነስሩ ከተባሉ ሌላ ግለሰብ ጋር አብረው መሆኑንም አክለዋል።
ሁለቱ ግለሰቦች በጉራጌ ዞን “ወልቂጤ ከተማ የተቀሰቀሰን ሁከት መርተዋል” በሚል መጠርጠሩን ፖሊስ ለፍርድ ቤት ማስታወቁን አቶ አብዱረዛቅ ተናግረዋል። ፖሊስ በግለሰቦቹ ላይ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ፤ የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ጠይቆ እንደነበርም አስታውሰዋል።
ያለ ጠበቃ ፍርድ ቤት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች፤ “በወልቂጤ ሁከት ተፈጽሟል” በተባለበት ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እንደነበሩ በማስታወስ፤ የተወነጀሉበትን ድርጊት አለመፈጸማቸውን ለችሎቱ መናገራቸውን ጠበቃው አክለዋል። ከዚህ በተጨማሪ አቶ ታረቀኝ፤ የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባልነታቸውን በመጥቀስ፤ ያለመከሰስ መብት እንዳላቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል ብለዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ችሎቱ “አንድ አቋም መያዝ ባለመቻሉ” ጉዳዩ በማግስቱ እንዲታይ ቀጠሮ መስጠቱን ጠበቃው ተናግረዋል። በተለዋጭ ቀጠሮው መሰረት ትላንት ረቡዕ አስር ሰዓት ገደማ የተሰየሙት የችሎቱ ዳኛ፤ “ፍርድ ቤቱ ያለመከሰስ መብትን የተመለከተ ጉዳይ ለማየት ስልጣን እንደሌለው” በመጥቀስ፤ ተከራካሪ ወገኖች በጊዜ ቀጠሮው ላይ አስተያየት እንዲሰጡ መጠየቃቸውን ጠበቃው ገልጸዋል።
በትላንቱ የችሎት ውሎ፤ መርማሪ ፖሊስ እና በችሎት የተገኙት ሌላኛው የአቶ ታረቀኝ ጠበቃ ክርክር ማድረጋቸውን አቶ አብድረዛቅ አስረድተዋል። አቶ ታረቀኝ በቁጥጥር ስር የዋሉት “ወንጀል ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ” በመያዛቸው መሆኑን ለፍርድ ቤት የገለጸው መርማሪ ፖሊስ፤ በዚህ ምክንያት የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባሉን ያለመከሰስ መብት አስቀድሞ ማስነሳት እንደማይጠበቅበት ማስረዳቱ በችሎቱ አከራክሯል።
የአቶ ታረቀኝ ጠበቃ ለዚህ የፖሊስ ማብራሪያ ባቀረቡት መከራከሪያ፤ “ግለሰቡ የተያዙት የተወነጀሉበትን ድርጊት ሲፈጽሙ ከሆነ፤ የያዟቸው አካላት ቀርበው እንዲያስረዱ በማድረግ ክሱ ሊመሰረት እንጂ የጊዜ ቀጠሮ ሊጠየቅ አይገባም” ብለዋል። ተጠርጣሪዎቹ “በስልክ ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ እንደነበር” ለፍርድ ቤት ያስረዳው መርማሪ ፖሊስ፤ ግለሰቦቹ እጅ ከፍንጅ የተያዙበት ማስረጃ በእጅ ስልካቸው ላይ እንደሚገኝ ማስታወቁን አቶ አብዱረዛቅ ገልጸዋል። የተጠርጣሪዎቹ የእጅ ስልክ “ምርመራ እየተደረገበት በመሆኑ” ለፍርድ ቤት ማቅረብ አለመቻሉን መርማሪ ፖሊስ ጨምሮ ማስረዳቱንም አክለዋል።
በችሎቱ ላይ ክርክር የተደረገበት ሁለተኛ ጭብጥ ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት የቀረቡበት ከተማ ተገቢነትን የሚመለከት እንደነበር ጠበቃው ተናግረዋል። በአንድ ላይ የቀረቡት ሁለቱም ግለሰቦች የተያዙት በአዲስ አበባ ከተማ በመሆኑ፤ ጉዳዩን ሊያየው የሚገባው “በከተማዋ ላይ ችሎት የሚያስችለው የፌደራል ፍርድ ቤት መሆኑን” የሚያስረዳ ክርክር መቅረቡንም አመልክተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም፤ በተጠርጣሪዎቹ ተፈጽሟል የተባለው ወንጀል ፍሬ ነገር ያለው ወልቂጤ ከተማ ላይ በመሆኑ፤ ጉዳዩ የሚመለከተው በከተማዋ ያለውን ፍርድ ቤት እንጂ በሀዋሳ ከተማ የሚገኝ ፍርድ ቤት አለመሆኑን በመጥቀስ የአቶ ታረቀኝ ጠበቃ መከራከራቸው ተገልጿል። ለዚህ መከራከሪያ መርማሪ ፖሊስ በሰጠው ምላሽ፤ “የተጠየቀው የጊዜ ቀጠሮ ስለሆነ በየትኛውም ፍርድ ቤት መታየት ይችላል” ማለቱን አቶ አብዱረዛቅ ተናግረዋል።
በእነዚህ ጭብጦች ላይ የቀረቡትን ክርክሮች ያደመጠው የሀዋሳ ማዕከል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤ የሰባት ቀን ጊዜ ቀጠሮ በመፍቀድ ፖሊስ በቀጣይ ቀጠሮ ምርመራውን አጠናቅቆ እንዲያቀርብ ማዘዙን ጠበቃው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። በትላንትናው የችሎት ውሎ የአቶ ታረቀኝ የህክምና ጉዳይ በተጨማሪነት ተነስቶ እንደነበርም አክለዋል።
አቶ ታረቀኝ በፖሊስ በተያዙበት ወቅት በተፈጸመባቸው ድብደባ ምክንያት ቀኝ እጃቸው እና ጀርባቸው ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለፍርድ ቤት መናገራቸውን ጠበቃቸው ጠቅሰዋል። የደቡብ ምክር ቤት አባሉ በተያዙ በማግስቱ በግል ሀኪም ህክምና ለማግኘት ቢሞክሩም መከልከላቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል ተብሏል። የተጠርጣሪውን አቤቱታ ያደመጠው ፍርድ ቤቱ፤ አቶ ታረቀኝ ህክምና እንዲያገኙ ትዕዛዝ በመስጠት የዕለቱን የችሎት ውሎ ማጠናቀቁን አቶ አብዱረዛቅ ተናግረዋል።
ኢዜማ ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ፤ የፓርቲው የደቡብ ክልል ምክር ቤት ተወካይ የሆኑት አቶ ታረቀኝ ደግፌ የታሰሩት ያለመከሰስ መብታቸው ባልተነሳበት ሁኔታ መሆኑን ጠቅሶ፤ እርምጃውን “ህጋዊ ያልሆነ” ሲል ኮንኖት ነበር። የምክር ቤት አባሉ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲጠበቅ በሰኞ መግለጫው የጠየቀው ኢዜማ፤ “ህጋዊ እርምጃዎች መወሰድ ያለባቸው ህግ እና ህግን ብቻ ተከትለው ሊሆን ይገባል” ሲል ማሳሰቡ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)