የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ፤ ከነገ ጀምሮ ለአራት ቀናት የሚቆይ ስብሰባ ሊያካሄድ ነው

በአማኑኤል ይልቃል

የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ፤ ከነገ ቅዳሜ ህዳር 24 ጀምሮ ለአራት ቀናት የሚቆይ ስብሰባ ሊያካሄድ ነው። የነገው ስብስባ፤ የፌደራል መንግስት እና የህወሓት ተደራዳሪዎች በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ የሚካሄድ የመጀመሪያው ስብሰባ ነው። 

ከነገ ቅዳሜ ጠዋት እስከ ማክሰኞ ከሰዓት ይቆያል የተባለው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የሚካሄደው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዳራሽ እንደሆነ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተግረዋል። ሶስት የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ጥሪ እንደደረሳቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቢያረጋግጡም፤ ዝርዝር የውይይት አጀንዳዎች ምን እንደሆኑ እንዳልተገለጸላቸው አመልክተዋል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አንድ ምንጭ፤ የስብሰባው ዋና ትኩረት “ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች” ናቸው ብለዋል። የብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ኢትዮጵያ ኢንሳደር” ለፓርቲው የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሳዳት ነሻ ጥያቄ ብታቀርብም፤ “በራሳችን ሚዲያ እንገልጻለን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የገዢው ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለመጨረሻ ጊዜ ስብሰባውን ያካሄደው ከአምስት ወራት በፊት በሰኔ 2014 ዓ.ም ነበር። በወቅቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ፤ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነትን በሰላም ለመፍታት መንግስት ሊተገብረው ስላቀደው “አማራጭ” በተመለከተ መወያየታቸው ተገልጾ ነበር። 

የሰኔው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ከተጠናቀቀ በኋላ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባሉ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በሰጡት መግለጫ፤ ገዢው ፓርቲ ጦርነቱን ለመቋጨት “ሰላማዊ አማራጮችን” ለመከተል ውሳኔ ማሳለፉን ማስታወቃቸው ይታወሳል።  

በ2012 ዓ.ም. የተመሰረተው ብልፅግና ፓርቲ የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤውን ያደረገው ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ውስጥ ነበር። በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤው፤ 225 የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን መመረጣቸው አይዘነጋም። ይህንን ጠቅላላ ጉባኤ በቦታው ተገኝቶ የታዘበው እና የጉባኤውን ውሳኔዎች በተመለከተ የቀረቡለትን ሰነዶችን የመረመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ በፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ዝርዝር ማስተካከያ እንዲደረግ ማሳሰቢያ ሰጥቶ ነበር። 

ቦርዱ ባለፈው መስከረም ወር መጀመሪያ ለብልጽግና ፓርቲ በጻፈው ደብዳቤ፤ ከፓርቲው የቀረበለት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ዝርዝር፤ የቦርዱ ታዛቢዎች በጉባኤው ላይ ተገኝተው ከመዘገቡት የተለየ መሆኑን ጠቅሶ ነበር። በማዕከላዊ ኮሚቴ  አባላት ዝርዝር ላይ ልዩነቱ የተፈጠረው፤ በኮሚቴው ውስጥ “ተመጣጣኝ ውክልና” እንዲኖር ለማድረግ ሲባል እንደነበር ፓርቲው ለቦርዱ በሰጠው ምላሽ ማስታወቁም በደብዳቤው ተመልክቷል። 

በማዕከላዊ ኮሚቴ ምርጫ ወቅት ከፍተኛ ድምጽ አግኝተው የነበሩ አስር አባላት፤ ዝቅተኛ ድምጽ ባገኙ ሌሎች ተመራጮች እንዲተኩ የተደረገው፤ በፓርቲው ውስጥ “ተመጣጣኝ ውክልና” ለማስጠበቅ በሚል እንደነበር የብልጽግና ፓርቲ ለምርጫ ቦርድ በሰጠው ምላሽ አስታውቆ ነበር ተብሏል። ይሁንና ቦርዱ ከፓርቲው የተሰጠው ይህ ምላሽ፤ ጠቅላላ ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት ለጉባኤው ታዳሚዎች ቀርቦ ውይይት ያልተደረገበት እንደነበር ከታዛቢዎቹ ማረጋገጡን ገልጿል። 

የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ “የመጨረሻ የውሳኔ ሰጪ” አካል መሆኑን የጠቀሰው የመስከረሙ የምርጫ ቦርድ ደብዳቤ፤ የኮሚቴው አባላት የሚሆኑት በጉባኤው የተመረጡት ግለሰቦች ብቻ መሆናቸውን አስታውቆ ነበር። ምርጫ ቦርድ እውቅና የሚሰጠው በራሱ ታዛቢዎች የቀረቡለትን የማዕከላዊ ኮሚቴ ዝርዝር እንደሆነ በደብዳቤው ጠቅሷል። 

የብልጽግና ፓርቲም “በዚሁ መሰረት እንዲፈጽም” ውሳኔ ማስተላለፉን ቦርዱ በደብዳቤው አስታውቋል። ይህን የምርጫ ቦርድ ውሳኔ በተመለከተ ገዢው ፓርቲ ስለጉዳዩ በይፋ ያለው ነገር የለም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)