የምስራቅ ወለጋ አካባቢዎች በኮማንድ ፖስት እንዲተዳደሩ ሶስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ

በሃሚድ አወል

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን በሚገኙት ኪረሙ፣ ጊዳ አያና እና ሀሮ አካባቢዎች፤ ዘላቂ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ በኮማንድ ፖስት እንዲተዳደሩ እና የመከላከያ ሰራዊት ስፍራዎቹን እንዲቆጣጠር ሶስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ። በአካባቢዎቹ በተፈጸሙ “የንጹሃን እልቂት ባለስልጣናት ጭምር ተሳትፈዋል” ሲሉ የወነጀሉት ፓርቲዎቹ፤ በድርጊቱ የተሳተፉ የትኛውም ኃይሎች “በአስቸኳይ ለህግ እንዲቀርቡ” ጥያቄ አቅርበዋል።

ዛሬ ማክሰኞ ህዳር 27፤ 2015 በሰጡት የጋራ መግለጫ እነዚህን ጥያቄዎች ያቀረቡት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና እናት ፓርቲ ናቸው። ሶስቱ ፓርቲዎች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት በዚሁ መግለጫቸው፤ በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ፣ ጊዳ አያና እና ሀሮ አካባቢዎች ከሰሞኑ “እጅግ የሚሰቀጥጡ ፍጅቶች” መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ “ዘግናኝ ጭፈጨፋ” ሲሉ በጠሩት በዚሁ ድርጊት፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን፣ ሺህዎች ከቤት ንብረት መፈናቀላቸውን እና ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት መውደሙን ጠቅሰዋል። በምስራቅ ወለጋ፣ ጉትን በተሰኘችው ቀበሌ ያሉ ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግም፤ በአካባቢው ተሰማርተው የነበሩ “የክልል የጸጥታ ኃይል ልብስ የለበሱ ኃይሎች” በንጹሃን ላይ “ጭካኔ የተሞላው ተግባር” መፈጸማቸው “እጅጉን አሳዝኖናል” ብለዋል። 

ላለፉት አራት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል፣ በወለጋ ዞኖች በተደጋጋሚ በተፈጸሙ ግድያዎች፤ የድርጊቱ ቀጥታ ሰለባ “የአማራ ማህበረሰብ” መሆኑን ፓርቲዎቹ በዛሬው መግለጫቸው አመልክተዋል። ከእነርሱ በተጨማሪ “ጭፍጨፋውን የሚቃወሙ፣ ‘ተው አይበጅም’ እያሉ የጮኹ፣ የኦሮሞ ማንነት ያላቸው ዜጎች” ከእልቂቱ አለመትረፋቸውን ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ አስታውሰዋል። 

የ“ሸኔ” ቡድን “ለመንግስት መረጃ ሰጥታችኋል” በሚል፣ የመንግስት ኃይሎች ደግሞ “ሸኔን ደግፋችኋል” በሚል ሰበብ በአካባቢው ባሉ ነዋሪዎች ላይ በሚፈጽሙት ጥቃት፤ ዜጎች “በሁለት ቢላዋ እየታረዱ ይገኛሉ” ሲሉ ፓርቲዎቹ ለጋዜጠኞች ባሰራጩት ባለሁለት ገጽ መግለጫ ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል። ባለፉት አራት ዓመታት በእነዚህ አካባቢዎች የተፈጸሙት ጭፍጨፋዎች በ“ኦነግ ሸኔ” እንደተደረጉ ለተወሰኑ ጊዜያት ቢነገርም፤ ከጊዜ በኋላ ግን “የመንግስት ጸጥታ ኃይሎች ጭምር ግንባር ቀደም ተሳታፊነት ያለበት መሆኑ እየታየ ነው” ሲሉ ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አትተዋል።

“በኦሮሚያ ክልል ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጭፍጨፋዎችን መንግስት እስካሁን ድረስ ማስቆም ያለመፈለጉ፣ በቅጡ እንኳን በማውገዝ ለፍጅቱ እውቅና ያለመስጠቱ፣ ማድበስበሱ እና በጥቂቱም ቢሆን የሕግ ተጠያቂነት ያለመኖሩ እጁ እንዳለበት ከበቂ በላይ ማሳያ ይሆናል ብለን እናምናለን” ሲሉ ሶስቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወንጅለዋል። በኦሮሚያ ክልል ከሰሞኑ የተፈጸመውን “ጭፍጨፋ” በተመለከተ የፌደራል እና የክልሉ መንግስታት “በአስቸኳይ” ማብራሪያ እንዲሰጡ ጥያቄ አቅርበዋል። በ“ጭፍጨፋው” የተሳተፉ የትኛውም ኃይሎች “በአስቸኳይ ለሕግ እንዲቀርቡም” ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል። 

የሰሞኑን ድርጊት በተመለከተ፤ ሶስቱ ፓርቲዎች አባል በሆኑበት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት “መግለጫ ለምን ማውጣት እንዳልተቻለ” በዛሬው መግለጫ ላይ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦ ነበር። በመግለጫው ላይ የተገኙት የእናት ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰይፈስላሴ አርዓያ “[የጋራ ምክር ቤቱ] በዚህ ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም ይያዛል ተብሎ አይታመንም። ነገር ግን እዚያ ላይ ዝምታን እንመርጣለን ማለት አይደለም። ጥያቄዎቻችን እናነሳለን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። 

ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ 53 የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት ያቀፈው የጋራ ምክር ቤቱ፤ ስብሰባዎችን በየጊዜው የሚያደርግ ባለመሆኑ በዚያ በኩል መግለጫ ለማውጣት የሚያስቸግር መሆኑንም የእናት ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት በተጨማሪነት አንስተዋል። “የጋራ ምክር ቤቱን ጠቅላላ ጉባኤ ጠብቆ እነዚህን ጉዳዮች ማንሳት፤ ከእኛ ወገን ኃላፊነት የጎደለው ነው ብለን ነው የምናስበው” ያሉት ዶ/ር ሰይፈስላሴ፤ የምክር ቤቱን የስብሰባ ጊዜ ሳይጠብቁ “ከመሰል የፖለቲካ ፓርቲዎች” ጋር በመሆን መግለጫ ማውጣታቸውን ገልጸዋል።  

በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከተገኙ ጋዜጠኞች ከቀረቡ ጥያቄዎች ውስጥ፤ “መግለጫውን የሰጣችሁት ለአማራ የተለየ ስሜት ስላላችሁ ነው ወይ?” የሚለው ይገኝበታል። የእናት ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል ስሜት ነው ያለን። ሶስታችንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዘውግ ፖለቲካ የራቅን ፓርቲዎች ነን። የተለየ ስሜት ስላለን አይደለም” ብለዋል። 

በመግለጫው ላይ ኢህአፓን ወክለው የተገኙት የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት በበኩላቸው፤ “ህብረብሔራዊ እና የአንድነት አቀንቃኞች” የሆኑት ፓርቲዎቹ፤ ለሁሉም ህዝብ “በእኩልነት የሚቆሙ” መሆናቸውን ተናግረዋል። “እዚህ ጋር በማፈር፤ የአማራ ህዝብ እየተጨፈጨፈ በይሉኝታ የምናልፈው ነገር የለም። የኦሮሞ ህዝብ እየተጨፈጨፈ በይሉኝታ የምናልፈው ነገር የለም። በግልጽ ልንናገር ይገባል። ብሔርተኞች በዚህ ነው የሚያሸማቅቁን” ሲሉ ዘለግ ያለ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ የቀረበው ሌላኛው ጥያቄ በኦሮሚያ ክልል ያለውን የጸጥታ ችግር እና ጥቃት በንግግር መፍታት ላይ ያላቸውን አቋም የተመለከተ ነው። ለዚህኛው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የመኢአድ ፕሬዝዳንት አቶ ማሙሸት አማረ “ለተጎዱ፣ ለተደፈሩ፣ ለተገደሉ፣ አካላቸው ለጎደለ፣ ሀብት እና ንብረታቸው ለወደመባቸው የመንግስት እና የግል ተቋማት ፍትህ ያስፈልጋል። [አጥፊዎች] ፍትህ ፊት ቀርበው መጠየቅ ካልቻሉ፤ የህግ የበላይነት ካልተረጋገጠ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ሰላም ሊመጣ አይችልም” ሲሉ አቋማቸውን አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)