በአማኑኤል ይልቃል
ብልጽግና ፓርቲ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን በመጪው አርብ ህዳር 30 በሀዋሳ ከተማ ሊያካሄድ ነው። ገዢው ፓርቲ አስቸኳይ ስብሰባውን የጠራው፤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ መሰረት የፓርቲውን ኢንስፔክሽንና ሥነ-ምግባር ኮሚሽን አባላትን በድጋሚ ለመምረጥ መሆኑን የፓርቲው ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ፓርቲው አንደኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሄደው ከስምንት ወራት በፊት በመጋቢት 2014 ዓ.ም ነበር። ብልጽግና ፓርቲ በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤው፤ የፓርቲውን ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የስራ አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን መርጦ ነበር።
አስራ አንድ አባላት ያሉበት የፓርቲው ኢንስፔክሽንና ሥነ-ምግባር ኮሚሽን አባላት ምርጫም የተከናወነው በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነበር። ይህንን ኮሚሽን በወቅቱ እንዲመሩ የተመረጡት፤ ከኮሚሽኑ አባላት ውስጥ ብቸኛዋ ሴት የሆኑት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ናቸው። የኮሚሽኑ ምክትል ሰብሳቢ በመሆኑ የተመረጡት ዶ/ር ደስታ ተስፋው ሲሆኑ ዶ/ር ሁሴን አብዱላሂ ደግሞ የጸሀፊነት ቦታ አግኘተዋል።
የጠቅላላ ጉባኤውን ሂደት እና በብልጽግና ፓርቲ የቀረቡለትን ሰነዶች ሲመረምር የቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የኢንስፔክሽንና ሥነ-ምግባር ኮሚሽን አባላትን ምርጫ ውድቅ የሚያደርግ ውሳኔ ባለፈው ነሐሴ ወር አሳልፏል። ምርጫ ቦርድ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው፤ በጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ካሰማራቸው ታዛቢዎች በሰበሰባቸው መረጃዎች እና በፓርቲው የቀረቡለትን ሰነዶች መሰረት በማድረግ እንደሆነ በወቅቱ አስታውቋል።
ምርጫ ቦርድ በዚሁ ውሳኔው፤ የኢንስፔክሽንና ሥነ-ምግባር ኮሚሽን አባላት የሆኑት ግለሰቦች “ግልጽ፣ ነጻ እና ፍትሃዊ በሆነ፤ በሚስጥር በሚሰጥ ድምጽ ያልተመረጡ” መሆናቸውን ገልጿል። የኮሚሽኑ አባላት “በጠቅላላ ጉባኤው ሳይመረጡ ስም ዝርዝራቸው ለጉባዔው የተገለጸ” መሆኑን በስፍራው ከነበሩ ታዛቢዎቹ ማረጋገጡንም ጠቅሷል።
የኮሚሽኑ አባላት አመራረጥ ሂደት፤ በምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ እና በፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ያልተከተለ መሆኑን ቦርዱ በውሳኔው ላይ አስፍሯል። በዚህም መሰረት ፓርቲው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በመጥራት፣ በድጋሚ የኮሚሽኑን አባላት እንዲመርጥ፤ ምርጫ ቦርድ ቀነ ገደብ ሰጥቶ ነበር።
ብልጽግና ፓርቲ የተሰጠው ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ አንድ ወር ጊዜ ቢቀረውም፤ በመጪው አርብ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ መወሰኑን የፓርቲው ምንጮች ገልጸዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሶስት የፓርቲው አባላት፤ ለአንድ ቀን በሚካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ እንዲገኙ ጥሪ እንደደረሳቸው አስታውቀዋል።
ፓርቲው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን የሚያካሄደው፤ በሀዋሳ ከተማ በሚገኘው “ሚሊኒየም አዳራሽ” መሆኑን ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የሲዳማ ክልል ዋና ከተማ የሆነችው ሀዋሳ፤ በገዢው ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ ዋዜማ የሚከበረውን የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ለማስተናገድ ከወዲሁ እንግዶችን መቀበል ጀምራለች።
ብልጽግና ፓርቲ በመጪው አርብ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚያካሄድ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቁን የመስሪያ ቤቱ የኮሚዩኒኬሽን ክፍል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጧል። በዚሁ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የቦርዱ ታዛቢዎች እንደሚገኙም የኮሚዩኒኬሽን ክፍሉ ጨምሮ ገልጿል።
የገዢው ፓርቲ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤን በተመለከተ ከብልጽግና ፓርቲ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ክፍል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግናቸው ተደጋጋሚ ሙከራዎች፤ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አልተሳካም። የብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፤ ካለፈው ቅዳሜ ህዳር 24 ጀምሮ እስከ ዛሬ ማክሰኞ ድረስ ለአራት ቀናት የቆየ ስብሰባ ሲያካሄዱ መቆየታቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)