መንግስት፤ የጸጥታ ኃይሎቹ መድረስ በማይችሉባቸው ቦታዎች ያሉ ማህበረሰቦችን እንዲያስታጥቅ ኢዜማ ጥሪ አቀረበ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ)፤ መንግስት የጸጥታ ኃይሎች በቀላሉ መድረስ በማይችሉባቸው እና በመደበኛ የጸጥታ ኃይል መጠበቅ አስቸጋሪ በሆኑባቸው አካባቢዎች ያሉ ማህበረሰቦችን እንዲያስታጥቅ ጥሪ አቀረበ። መንግስት ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘ የወሰደው እርምጃ ካለ፤ ለህዝብ እንዲያሳውቅም ፓርቲው ጠይቋል።

ኢዜማ ጥሪውን ያቀረበው፤ ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ተፈጽሟል ያለውን “የንጹሃን ዜጎች ጭፍጨፋ” አስመልክቶ ዛሬ ማክሰኞ ህዳር 27፤ 2015 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ አካባቢ በሚገኘው የኢዜማ ዋና ጽህፈት ቤት በተሰጠው በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ ምክትላቸው አቶ ዮሐንስ መኮንን እና የፓርቲው ዋና ጸሀፊ አቶ አበበ አካሉ ተገኝተዋል። 

ፓርቲው ለጋዜጠኞች ባሰራጨው መግለጫ፤ በምስራቅ ወለጋ የተፈጸመውን አይነት “ብሔርን መሰረት ያደረጉ ጭፍጨፋዎች” በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ሲፈጸሙ መቆየታቸውን አስታውሷል። “ይህን አይነት ጭፍጨፋዎች በተፈጸሙ ቁጥር ጊዜያዊ ጫጫታ ከመፍጠር እና የፖለቲካ ትርፍ ለመሸመት ከሚደረግ ወቅታዊ ግርግር ወጥተን፤ የችግሩን መንስኤ ከምንጩ ለማድረቅ እስካልሰራን ድረስ፤ የእኛ የምንለውን ብሔር እየለየን በየተራ እናዝን እንደሆን እንጂ ሀዘናችን ማብቂያ አይኖረውም” ሲል ኢዜማ በመግለጫው አስፍሯል።

“ይህ አዙሪት የሚያበቃው፤ እያንዳንዱን ግፍና በደል በጋራ ቆመን በማውገዝ፤ ተግባራዊ ለውጥ እንዲመጣም በጋራ መስራት ስንጀምር ብቻ ነው” ያለው ኢዜማ፤ ኢትዮጵያውያንን በጽናት ቆመው ሊታገሉት የሚገባው ጉዳይ “በብሔር ላይ የተንጠላጠለ ስርዓት” መሆኑን በአጽንኦት ጠቅሷል። ፓርቲው “ከፋፋይ” ሲል የጠራው ይህ ስርዓት፤ ኢትዮጵያውያንን “በተደጋጋሚ ሀዘን ውስጥ እየከተተ” ያለ መሆኑንም አስገንዝቧል።  

ኢዜማ በዚሁ መግለጫው የኦሮሚያ ክልል እና የፌደራል መንግስት  የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት ማስጠበቅ እና የህግ የበላይነት ማስከበር አልቻሉም የሚል ወቀሳን ሰንዝሯል። “የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት በማስጠበቅ ንጹሃን ላይ የሚደርስን ግፍ ያስቆማል ተብሎ የሚታሰብ የጸጥታ ኃይል፤ ከግፈኞች ጎን በመቆም የማፈናቀል እና የግድያዎች አስተባባሪ ሆነው [ተመልክተናል]” ሲልም ኢዜማ ወንጅሏል። 

“በነጻ አውጪነት ስም የተደራጁ አሸባሪ ቡድኖች ከመንግስት መዋቅር ድጋፍ ማግኘታቸው የአደባባይ ሚስጥር በሆነበት ሁኔታ፤ የንጹሃን ደም በከንቱ መፍሰሱ ይቆማል ብሎ ማሰብ አይቻልም” ያለው አዜማ፤ “በእነዚህ መሰል ጭፍጨፋዎች ውስጥ በቀዳሚነት እየተሳተፉ ያሉ፤ በተለያዩ የመንግስት መዋቅሮች ውስጥ የተሰገሰጉ አካላትን ለይቶ ማውጣት እና ለፍርድ ማቅረብ” እንደሚገባ አሳስቧል። መንግስት በዚህ ረገድ የወሰደውን እርምጃ “ለህዝቡ ማሳወቅ ይገባል” ሲልም ፓርቲው በመግለጫው አክሏል።  

ካለፈው ዓመት መስከረም ወር ጀምሮ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ካቢኔ የተቀላቀሉት የኢዜማ መሪ፤ በምስራቅ ወለጋ ያጋጠመውን አይነት ግድያ ለመከላከል “በመንግስት በኩል ሰፊ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ሆኖም በመንግስት የተደረጉ ጥረቶችን “አንሰማም” ሲሉ አክለዋል። 

“በመንግስት በኩል ግልጽ የሆነ [የህዝብ] ግንኙነት ይፈልጋል” ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ “መንግስት ሰላሙን ሊያስከብር እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ ህብረተሰቡ ማወቅ አለበት። ካልሆነ ደግሞ [መንግስት] ምን ችግር እንዳለበት ማሳወቅ አለበት” ሲሉ አሳስበዋል። እርሳቸው የሚመሩት ፓርቲ ባወጣው መግለጫም “የተሰሩ ስራዎች ካሉ እንኳን ማህበረሰቡ እንዲያውቃቸው አለመደረጉ እና ለጉዳዩ የሚገባውን ትኩረት አለመሰጠቱ፤ ከፍተኛ ቸልተኝነት መሆኑ የሚታመን ነው” ብሏል። 

ኢዜማ በዛሬው መግለጫው፤ ግጭት ባሉባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚሆን ጊዜያዊ መፍትሔንም ጠቁሟል። “የመንግስት የጸጥታ ኃይል በቀላሉ መድረስ በማይችልባቸው እና በመደበኛ የጸጥታ ኃይል መጠበቅ አስቸጋሪ በሆኑባቸው አካባቢዎች፤ በህጋዊ አሰራርና በተደራጀ መንገድ ማህበረሰቡን ማስታጠቅ እና ራሱን ከመሰል እልቂት በጽናት እንዲከላከል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተን ለማሳሰብ እንወዳለን” ሲል ፓርቲው በመግለጫው አትቷል።

ይህ የፓርቲው አቋም፤ ጋዜጣዊ መግለጫውን በታደሙ ጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦበታል። “ማህበረሰቡን ማስታጠቅ ወደ ከፋ የእርስ በርስ ግጭት አያስገባም ወይ?” በሚል ከአንድ ጋዜጠኛ ለቀረበ ጥያቄ የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ምላሽ ሰጥተዋል። 

“በተደጋጋሚ ሲቪሊያኖች የሚገደሉባቸው ቦታዎች አሉ። እነዚህ ሲቪሎች ከሚገደሉባቸው [ምክንያት] አንዱ፤ መደበኛ የሆነው የመከላከያ የጸጥታ ኃይል ስላልደረሰላቸው ነው። መንግስት ‘እነኚህ ቦታዎች ላይ መድረስ አልችልም’ ካለ ምን አድርግ ነው የሚለው? እሱ ካልቻለ እዚያ አካባቢ ያሉ ሰዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ ነው” ሲሉ ፕሮፌሰር ብርሃኑ አብራርተዋል።

ከመደበኛው የጸጥታ ኃይል ጋር አብረው የሚሰሩ ሚሊሺያዎችን ማደራጀት በሌሎች ሀገራትም ያለ ልምድ መሆኑን የጠቀሱት የኢዜማ መሪ፤ በግጭት አካባቢዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከታጠቁ “ያለው የጸጥታ ኃይል እስከሚደርስም ቢሆን፤ በተወሰነ ደረጃ ራሳቸውን መከላከል የሚችሉበት መንገድ ይኖራቸዋል” ሲሉ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አቋም አንጸባርቀል። 

“በተደራጀ መንገድ” የህብረተሰብ ክፍሎችን ማስታጠቅ “ለተወሰነ ጊዜ፣ የመንግስት ኃይሎች እስከሚመጡ” መደረግ አለበት የሚሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ ይህ ማለት ግን ችግር በሌለበት ሁሉ “ህብረተሰቡ ይታጠቅ እና እርስ በርሱ [ይገዳደል]” ማለት እንዳልሆነ አስገንዝበዋል። “መስመር አልፎ እንዳይሄድ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። በደንብ በተደራጀ እና ህጋዊ በሆነ መንገድ መሆን አለበት” ሲሉም ፓርቲያቸው ያቀረበው የማስታጠቅ ምክረ ሃሳብ ሊመራበት ይገባል ያሉትን አካሄድ ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)