ከክልሎች በሚሰጡ መሸኛዎች ከሀገር ውጪ የሚላኩ ምርቶችን ማስተናገድ ማቆሙን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ

በአማኑኤል ይልቃል

የጉምሩክ ኮሚሽን፤ በክልሎች እና በስራቸው በሚገኙ መዋቅሮች በሚጻፉ የመሸኛ ደብዳቤዎች የሚንቀሳቀሱ የወጪ ንግድ  (export) ምርቶችን ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ማስተናገድ ማቆሙን አስታወቀ። ከዚህ በኋላ ወደ ውጪ ሀገር የሚላክ ማንኛውም ምርት፤ በንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ማረጋገጫ ማግኘት አለበት ተብሏል።

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት መሰረት፤ ከሀገር ውጪ ለሚወጡ ምርቶች ፈቃድ የመስጠት ስልጣን ያለው የፌደራል መንግስት  ነው። ከዚህ በተጓዳኝ ተግባራዊ ሲደረግ በቆየው አሰራር ግን ክልሎች እና በስራቸው ያሉ የአካባቢ አስተዳደሮች፤ ለወጪ ንግድ ምርቶች የሚሆኑ ፍቃዶች፣ መሸኛዎች እንዲሁም ሌሎች የይለፍ ማስረጃዎችን ሲሰጡ ቆይተዋል።

በክልሎች ከሚገኙ መዋቅሮች መካከል አንዳንዶቹ “ፈቃድ የመስጠት ኃላፊነት ያላቸው እየመሰላቸው” ደብዳቤ እንደሚጽፉ በንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ግንኙነትና የወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍ ኃላፊ አማካሪ አቶ ፍሬው ማሞ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሌሎች ደግሞ “ከግል ጥቅም ጋር በተያያዘ መልኩ” ድርጊቱን ሲፈጽሙ መቆየታቸውን አማካሪው አስረድተዋል።

በሀገሪቱ የተለያየ ቦታ የሚገኙ የጉምሩክ ኬላዎች በዚህ መልኩ የሚሰጡ ፍቃዶችን በመቀበል ምርቶችን እንዲያልፉ ሲያደርጉ መቆየታቸውን የሚገልጹት አቶ ፍሬው፤ እነዚህን መሰል ፍቃዶች ለኮንትሮባንድ ንግድ መባባስ ምክንያት እየሆኑ መምጣታቸውንም አክለዋል። በጉምሩክ ኮሚሽን የህግ ተገዢነት ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት አቶ ሙሉጌታ በየነም በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ። 

ምክትል ኮሚሽነሩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንዳሉት፤ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ የወጪ ንግድ ምርቶች፤ ከክልል፣ ዞን፣ ወረዳና ቀበሌ የመንግስት መዋቅሮች በሚጻፉ የመሸኛ ደብዳቤዎች “ህጋዊ ባልሆነ” መንገድ እየወጡ ለኮንትሮባንድ ተጋልጠዋል። በኮንትሮባንድ ከአገር እየወጡ ካሉ ምርቶች መካከል ቀዳሚዎቹ፤ የቁም እንስሳት፣ ጫት፣ በቆሎ እና ቦሎቄ እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በ2014 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ያገኘችው ገቢ 4.12 ቢሊዮን ዶላር ነበር። ይህ የገቢ መጠን በእቅድ ከተያዘው በ510 ሚሊዮን ዶላር ያነሰ ነው። ከእቅዳቸው በታች አፈጻጸም ካሳዩ ዘርፎች ውስጥ አንደኛው የቁም እንስሳት ንግድ ነው። በዚህ ዘርፍ ከታቀደው አንጻር መሳካት የታቻለው 54 በመቶው ብቻ መሆኑን ከንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ለቁም እንስሳት ዘርፍ ገቢ ማሽቆለቆል ምክንያት ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ የኮንትሮባንድ ንግድ ዋነኛው መሆኑን ሚኒስቴሩ ይገልጻል። የጉምሩክ ኮሚሽን የወጪ ኮንትሮባንድ ንግድን በተመለከተ ባደረጋቸው ጥናቶች፤ በክልሎች የሚጻፉ መሸኛ ደብዳቤዎች እና ሌሎች ማስረጃዎች ለቁጥጥር አስቸጋሪ ሁኔታ እንደፈጠሩ መረዳቱን ምክትል ኮሚሽነር ሙሉጌታ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ፤ የጉምሩክ ኮሚሽን ከንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ጋር በመሆን “የጋራ ውሳኔ” በማስተላለፍ ከክልሎች የሚጻፉ መሸኛዎች ተቀባይነት እንዳይኖራቸው መደረጉን አቶ ሙሉጌታ አስረድተዋል። ሁለቱ የመንግስት ተቋማት ባለፈው ቅዳሜ ህዳር 24፣ 2015 በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ ውሳኔው ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ተግባራዊ  መደረግ እንደሚጀምር አስታውቀዋል።

ተቋማቱ በዚሁ መግለጫቸው “በክልሎች አስፈጻሚ አካላት የሚሰጡ ፍቃዶች፣ መሸኛዎች እንዲሁም ሌሎች የይለፍ ማስረጃዎች ተቀባይነት የላቸውም” ብለዋል። የክልል መዋቅሮችም እነዚህን ፍቃዶች፣ መሸኛዎች እና ሌሎች የይለፍ ማስረጃዎች እንዳይሰጡ ተጨማሪ ውሳኔ መተላለፉንም በንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ተወካይ ዳይሬክተር ቁምነገር እውነቱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

“ማንኛውም ወደ ውጪ ኤክስፖርት የሚደረግን ምርት በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በኩል ነው መጥተው ማረጋገጥ የሚችሉት” ሲሉም የኮሙዩኒኬሽን ተወካይ ዳይሬክተሯ አክለዋል። በአዲሱ ውሳኔ መሰረት፤ በንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከሚሰጥ የወጪ ምርት መላኪያ ፍቃድ ውጪ፤ በክልል መዋቅሮቹ የተጻፉ ማስረጃዎች ይዘው የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች ተጠያቂ እንደሚሆኑም አስገንዝበዋል። 

ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገውን ውሳኔ ተከትሎ፤ በክልል መዋቅሮች የተጻፉ መረጃዎችን የያዙ ግለሰቦች፣ የንግድ ድርጅቶች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወይም ኩባንያዎች የወጪ ምርቶችን ይዘው የጉምሩክ ኬላዎችን እንዳያቋርጡ መደረጉን የጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ገልጸዋል። “ከአሁን በኋላ የትኛውም የጉምሩክ ኬላ ይሄንን አያስተናግድም” ሲሉም አቶ ሙሉጌታ በአጽንኦት ተናግረዋል። 

የጉምሩክ ኮሚሽን እና ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በጋራ ያሳለፉትን ይህን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ፤ የፌደራል ፖሊስ የተካተተበት “የኦፕሬሽን ቡድን” እንዲሰማራ መደረጉን ምክትል ኮሚሽነሩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።  የ“ኦፕሬሽን ቡድኑ” ቀዳሚ ተግባር፤ ከአገር የሚወጡ ምርቶች ላይ መደበኛ የቁጥጥር ስራ የሚሰሩ የጸጥታ አካላት፣ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶችና መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች የተላለፈውን ውሳኔ እያስተገበሩ መሆኑን መቆጣጠር መሆኑን አስረድተዋል።  

ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገውን ውሳኔ ተከትሎ፤ በክልል መዋቅሮች የተጻፉ መረጃዎችን የያዙ ግለሰቦች፣ የንግድ ድርጅቶች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወይም ኩባንያዎች የወጪ ምርቶችን ይዘው የጉምሩክ ኬላዎችን እንዳያቋርጡ መደረጉን የጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ገልጸዋል። 

የኦፕሬሽን ቡድኑ ሁለተኛ ተግባር ከዋና መተላለፊያ መንገድ ውጪ በኮንትሮባንድ የሚንቀሳቀሱ ምርቶች ላይ ክትትል ማድረግ መሆኑን አቶ ሙሉጌታ አመልክተዋል። “የኦፕሬሽን ቡድኑ” የክትትል ስራውን “በበረራ እና በደፈጣ” እንደሚያከናውንም ጠቁመዋል። ቡድኑ “አውቶማቲካል የሆነ እርምጃ እንዲወስድ የተደራጀ ኃይል ነው” ሲሉም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)