በኦሮሚያ ክልል በአምስት ወራት ውስጥ ብቻ “በብዙ መቶዎች የሚገመቱ” ሰዎች በታጣቂዎች እንደተገደሉ ኢሰመኮ አስታወቀ

በአማኑኤል ይልቃል

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኙ አስር ዞኖች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች፤ ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ “በብዙ መቶዎች የሚገመቱ” ሰዎችን “በአሰቃቂ ሁኔታ” መግደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። በእነዚህ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች “አይነት እና ቁጥር” ጨምሯል ያለው ኮሚሽኑ፤ የታጣቂዎቹ ጉዳይም “የመወሳሰብ አዝማሚያ” ማሳየቱን ገልጿል።

ኢሰመኮ ይህንን ያለው፤ በኦሮሚያ ክልል የሚፈጸሙ ጥቃቶችን እና ተያይዞ የተከተሉ “መጠነ ሰፊ ሰብአዊ ቀውሶችን” አስመልክቶ ዛሬ ረቡዕ ህዳር 28፤ 2015 ባወጣው መግለጫ ነው። በኦሮሚያ ክልል ጥቃት የሚፈጸምባቸው አካባቢዎች ስፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን የጠቆመው ኮሚሽኑ፤ ባለፉት አምስት ወራት ብቻ በ54 አካባቢዎች ግጭቶች መመዝገቡን አትቷል። 

በመንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ተቋም ዝርዝር መሰረት፤ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አራት የወለጋ እና ሶስት የሸዋ ዞኖች ግጭቶች ተከስተዋል። በአርሲ፣ በኢሉ አባቦር እና በቡኖ በደሌ ዞኖች የሚገኙ አካባቢዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ግጭቶች እንደነበሩ ኮሚሽኑ ገልጿል። 

በተጠቀሱት አካባቢዎች ውስጥ የሚከሰቱት አብዛኛዎቹ ጥቃቶች “ሆን ተብሎ ሲቪል ሰዎችን ኢላማ ያደረጉ” መሆናቸውን ኢሰመኮ ዛሬ ባወጣው ባለ አምስት ገጽ መግለጫ ላይ አመልክቷል። አብዛኞቹ ጥቃቶች “ብሔርን መሰረት ያደረጉ” ናቸው ያለው ኮሚሽኑ፤ “በተወሰኑ ሁኔታዎች የፖለቲካ አመለካከትን” መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንደሚፈጸሙም አክሏል።
 
በእነዚህ ጥቃቶች “በብዙ መቶዎች የሚገመቱ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ” መገደላቸውን እና “ብዛታቸው የማይታወቅ ሰዎች” ለአካል ጉዳት መዳረጋቸው ኮሚሽኑ በዛሬው መግለጫው አስታውቋል። በኦሮሚያ ክልል የተፈጸሙ ጥቃቶችን እና ግጭቶችን ተከትሎ፤ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውንም ኢሰመኮ አመልክቷል።

በኦሮሚያ ክልሉ ያሉ “ንጹሃን” የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እየደረሰባቸው ያለው፤ “ግጭት ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች” ጭምር መሆኑን የኮሚሽኑ መግለጫ አትቷል። በክልሉ ያሉ አካባቢዎችን ታጣቂዎች አሊያም የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በሚቆጣጠሩበት ወቅት፤ ግድያዎችን እንደሚፈጸሙም በመግለጫው ሰፍሯል። 

አንዱን ወይም ሌላኛውን “ታጣቂ ቡድን ትደግፋላችሁ” በሚል፤ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች “ከፍርድ ውጪ ግድያዎች” እንደሚፈጽሙ ኮሚሽኑ ባሰባሰባቸው መረጃዎች እና ማስረጃዎች መረዳቱን በመግለጫው ጠቅሷል። ኢሰመኮ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ይፈጸማሉ ያላቸውን ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችንም በመግለጫው ዘርዝሯል።

“ተገቢ የሆነ ማጣራት ሳይደረግ፤ ታጣቂ ቡድኖችን ኢላማ በማድረግ፤ በሲቪል ሰዎች የመኖርያ ሰፈሮች አቅራቢያ የተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች” በዝርዝሩ ከተካተቱት ውስጥ ይገኝበታል። “ሕገ ወጥ እና የዘፈቀደ እስሮች፣ ተጠርጣሪዎችን የማሰቃየት ተግባራት በሲቪል ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛሉ” ሲልም ኢሰመኮ በመግለጫው አመልክቷል። 

በኦሮሚያ ክልል ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ላይ የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖች “በአይነታቸው እና በቁጥራቸው” መጨመራቸውን የገለጸው ኢሰመኮ፤ በተለያዩ ወቅቶች፣ የተለያዩ ቡድኖች “ሙሉ ቀበሌዎችን ወይም ወረዳዎችን ጭምር” ተቆጣጥረው እንደቆዩ ጠቁሟል

በኦሮሚያ ክልል ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ላይ የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖች “በአይነታቸው እና በቁጥራቸው” መጨመራቸውን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ በተለያዩ ወቅቶች፣ የተለያዩ ቡድኖች “ሙሉ ቀበሌዎችን ወይም ወረዳዎችን ጭምር” ተቆጣጥረው እንደቆዩ ጠቁሟል። ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ላይ የሚንቀሳቀሱ አካላትን በአራት የከፈለው ኢሰመኮ፤ ከእነዚህ ውስጥ “የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች” እና “በመንግሥት እራሳቸውን እንዲከላከሉ በሚል የታጠቁ የየአካባቢው ነዋሪዎች” እንደሚገኙበት አስታውቋል።

በግጭቱ ከሚሳተፉ አካላት መካከል “ከሌሎች ክልሎች ጭምር የመጡ እና በተለምዶ በአካባቢው ‘የአማራ ታጣቂዎች’ መሆናቸው የሚነገሩ የታጠቁ ቡድኖች” እንዳሉበት የኢሰመኮ መግለጫ ይፋ አድርጓል። በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ለሚፈጸሙ ጥቃቶች በፌደራል እና በክልሉ መንግስት በተደጋጋሚ የሚወነጀለው “ኦነግ ሸኔ” ወይም ራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት” ብሎ የሚጠራው ቡድንም፤ በግጭቶቹ እንደሚሳተፍ በኢሰመኮ መግለጫ ተጠቅሷል። 

“እነዚህ የታጠቁ ቡድኖች እና የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች፤ በተለያዩ ወቅቶች እርስ በእርሳቸው በሚያደርጓቸው ውጊያዎች፣ በሌላ ወቅት በተናጠል በሚያደርሷቸው ጥቃቶች ሳቢያ በርካታ ሲቪል ሰዎች ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለመፈናቀል እና ለንብረት ውድመት ተዳርገዋል” ብሏል ኢሰመኮ። በአካባቢዎቹ ላይ ባሉ ጥቃትና ውጊያዎች የተነሳም “አንዳንድ ቀበሌዎች ወይም የገጠር ከተሞች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ወይም በከፊል ወድመዋል” ሲል   ኮሚሽኑ ገልጿል። 

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ ግጭት ባለባቸው የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ “ሰቆቃ” ሲሉ ገልጸውታል። የክልሉ ነዋሪዎች “በተዋጊ ቡድኖች መካከል መውጫ የሌለው አጣብቂኝ ውስጥ መጠለፋቸው፤ ቢያንስ በተሟላ መልኩ ለመግለጽ ወይም ለማስተጋባት የሚያስችል ሁኔታ እንኳን አለመኖሩ፤ ከደረሰው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተነጥሎ ሊታይ የማይገባ ነው” ማለታቸውንም ኮሚሽኑ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል። 

ዶ/ር ዳንኤል “አጠቃላይ ሰቆቃው ከዚህ የበለጠ ሊቀጥል ስለማይችል ሳይውል ሳያድር ሰላማዊ እና ዘላቂ መፍትሔ ሊደረግለት ይገባል” ሲሉም አሳስበዋል። በንጹሃን ነዋሪዎች ላይ እየደረሰ ላለው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት “ተጠያቂነትና ፍትህ የማስገኘት ጥረትም” መዘንጋት እንደሌለበት አክለዋል። ዋና ኮሚሽነሩ መወሰድ አለባቸው ካሏቸው ከእነዚህ እርምጃዎች በተጨማሪ፤ ኢሰመኮ መፍትሔ ያመጣል ያለውን ምክረ ሀሳብ በዛሬው መግለጫ ማጠቃለያ ላይ አቅርቧል። 

ኮሚሽኑ በዚሁ ምክረ ሃሳቡ፤ በኦሮሚያ ክልል “የጸጥታ እና የደህንነት ሁኔታ የመፍጠር” ኃላፊነት ያለው እንዲሁም የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን የሚያስተባብር “የልዩ ሁኔታ ጊዜያዊ መዋቅር በአፋጣኝ ሊቋቋም ይገባል” ብሏል። ይህ ጊዜያዊ መዋቅር፤ የክልሉን እና የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የጸጥታ ኃላፊዎችን፣ የሚመለከታቸውን መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እንዲሁም የተጎጂዎች ተወካዮችን ማካተት እንዳለበት ኢሰመኮ ምክረ ሃሳቡን አቅርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[ይህ ዘገባ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]