ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “በአዲስ ድል በቅርቡ እንገናኛለን” አሉ 

ኢትዮጵያ “ለአንድ ወር እንኳን ሰላም እንዳትሆን፤ አዳዲስ አጀንዳ እየፈጠሩ የሚያውኩ” አካላት እንዳሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ጠላቶች” ሲሉ የጠሯቸው አካላት፤ በቅርቡ የፈጠሩት አጀንዳ “አትዮጵያን ማፍረስ ቀርቶ ሊነቀንቃት አይችልም” ብለዋል።   

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት ዛሬ ሐሙስ ህዳር 29 በሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። አብይ 17 ደቂቃዎች ገደማ በፈጀው በዚሁ ንግግራቸው፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ገጥሟታል ስላሉት “አሳዛኝ ፈተና” አንስተዋል። ሀገሪቱ ይህን ፈተና ተሻግረን “በአዲስ ድል በቅርቡ እንደምንገናኝ ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ የለኝም” ሲሉም ተደምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ክብረ በዓል ላይ ከተናገሯቸው ውስጥ ከታች የቀረቡት ይገኙበታል፦  

  • “ኢትዮጵያ ውስጥ ከግራ ከቀኝ ዋልታ የረገጡ እሳቤዎች አሉ። ከትላንትና መላቀቅ ያልቻሉ፣ ነገ የሚሰራበትን እያንዳንዱን ብሎኬት ዛሬ የሚያፈርሱ፣ በጋራ መኖርን ሳይሆን መገፋፋትን የሚመርጡ፣ በራሳቸው አጀንዳ ሳይሆን በሰዎች አጀንዳ የተገዙ፣ በንጹሃን ደም ፖለቲካ ሰራን ብለው የሚያስቡ፣ ጥቂት ግለሰቦች እና ቡድኖች እንዲሁም የሚዲያ ሰዎች አሉ። ለእነዚህ ለጊዜው ለሳቱ ወንድሞች እና እህቶች ያለኝ ምክር ዛሬም ኢትዮጵያ ትፈተናለች እንጂ አትሸነፍም።”   
  • “ከግራም ከቀኝም ያሉ ዋልታ የረገጡ እሳቤዎች ለኢትዮጵያ ስለማይበጁ፤ እጅግ የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ዜጎች፣ ወጣቶች፣ የተማራችሁም ያልተማራችሁም ኢትዮጵያውያን፤ ለእያንዳንዱ አጀንዳ ምላሽ ከመስጠታችሁ በፊት የአጀንዳውን ባለቤት እና ምንጭ ለማወቅ እንድትሞክሩ፣ በሰከነ መንገድ ነገር እንድታዩ፤ ኢትዮጵያን ለመናጥ፣ ለአንድ ወር እንኳን ሰላም እንዳትሆን አዳዲስ አጀንዳ እየፈጠሩ ለሚያውኩን ሰዎች ጆሮ የምትሰጡ እንዳትሆኑ አደራ ልላችሁ እወዳለሁ።”
  • “ሰዎች ለከፋ እሳቤዎቻቸው፣ ለእኩይ ስራዎቻቸው፣ ጊዜያቸውን ገንዘባቸውን ጉልበታቸውን ህይወታቸውን እያጠፉ ስለሆነ፤ እኛ ለታላቋ ኢትዮጵያ ሰላም እና ብልጽግና አስር ቦታ ብንበጣጠስ፤ ልጆቻችን ቀጣጥለውና አጉልተው የሚያሳዩት ማንነት ስላለን፤ ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ፍቅር፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ያላችሁን ሁሉ ሰጥታችሁ በትጋት እንድትሰሩ በታላቅ ትህትና አደራ ልላችሁ እፈልጋለሁ።” 
  • “ዛሬም እንደ ትናንቱ ይህንን ፈተና ለጥንካሬ፣ ለብርታት፣ ለመሻገር፣ ለማሻገር ተጠቅመንበት በአዲስ ድል በቅርቡ እንደምንገናኝ ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ የለኝም። ለጠላቶቻችን፤ ትንሽ ከፍ ያለ ጠንከር ያለ ሀሳብ እስከሚኖራችሁ ድረስ ተረጋጉ። የአሁኑ አጀንዳችሁ አትዮጵያን ማፍረስ ቀርቶ ሊነቀንቃት ስለማይችል በደንብ ተዘጋጅታችሁ እንድትመጡ ምክር እለግሳችኋለሁ።” 
  • “የኢትዮጵያ ህዝቦች ምንም ድንግዝግዝ፣ ምንም ጨለማ የሚመስሉ ጉዳዮች ቢታዩም፤ አሁንም እኔ በጉልህ የሚታየኝ የኢትዮጵያ ብልጽግና፣ የኢትዮጵያ ጽናት፣ የኢትዮጵያ ታላቅነት፣ የኢትዮጵያ ከፍታ ስለሆነ፤ ሪቫን የምትቆርጡ እንጂ ተስፋ የምትቆርጡ ዜጎች አትሁኑ።”
  • “በሰሜን ኢትዮጵያ የጀመርነው ሰላም ዘላቂ አስተማማኝ እንዲሆን በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ስለሆነ፤ ሰላም ለሰሜን፣ ሰላም ለምዕራብ፣ ሰላም ለምስራቅ፣ ሰላም ለደቡብ፣ ሰላም ለኢትዮጵያ፣ ሰላም ለአፍሪካ እንዲሆን፤ በጋራ በትብብር እና በፍቅር እንድንቆም በታላቅ ትህትና አደራ ልላችሁ እፈልጋለሁ።”

[በ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተጠናቀረ]