የምስራቅ ወለጋ ግጭትን በተመለከተ የአቋም መግለጫ ያዘጋጁ የፓርላማ አባላት፤ ከተወካዮች ምክር ቤት አመራሮች ጋር ተወያዩ 

በሃሚድ አወል

ከኦሮሚያ ክልል የተመረጡ የፓርላማ አባላት፤ ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ ከተወካዮች ምክር ቤት አመራሮች ጋር ውይይት አካሄዱ። በውይይቱ ወቅት፤ በኦሮሚያ ክልል በአሁኑ ወቅት እየታየ ላለው የጸጥታ ችግር መፍትሔ ለማምጣት “የሰላም ስምምነት መደረግ አለበት” የሚል ምክረ ሃሳብ በፓርላማ አባላቱ ቀርቧል ተብሏል።

የፓርላማ አባላቱ ውይይቱን ያካሄዱት ትላንት ረቡዕ ህዳር 28፤ 2015 ከሰዓት በኋላ ነው። በተወካዮች ምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው በዚህ ውይይት፤ የፓርላማ አፈ ጉባኤው አቶ ታገሰ ጫፎ፣ ምክትላቸው ሎሚ በዶ እና በፓርላማ የመንግስት ተጠሪው አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ተገኝተዋል።   

ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ገደማ ድረስ በተካሄደው በዚህ ውይይት፤ የኦሮሚያ ክልልን ወክለው ፓርላማ ከገቡ ተመራጮች መካከል 80 ገደማ የሚሆኑት መገኘታቸውን በስብሰባው የተገኙ ተሳታፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የኦሮሚያ ክልል በተወካዮች ምክር ቤት ያሉት 178 መቀመጫዎች ቢሆንም፤ አሁን በፓርላማ የሚገኙት በ2013ቱ ምርጫ በተካሄደባቸው 170 የምርጫ ክልሎች የተመረጡ ተወካዮች ናቸው።

ከእነዚህ ተመራጮች ውስጥ 167 ያህሉ ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ወክለው ወደ ፓርላማ የገቡ ናቸው። ቀሪዎቹ ሶስት ተመራጮች በግል ተወዳድረው የተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑ ናቸው። ከእነዚህ ተወካዮች ውስጥ ዶ/ር ዲማ ነገዎ እና ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ የተመረጡት ከኢሉ አባቦር ዞን ነው። የምስራቅ ሐረርጌ ዞንን በመወከል በግል ተወዳድረው ፓርላማውን የተቀላቀሉት አቶ ጋላሳ ዲልቦ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

በትላንቱ ውይይት የተካፈሉት ሁሉም የፓርላማ አባላት፤ የገዢውን ፓርቲ ወክለው የተወካዮች ምክር ቤት የተቀላቀሉ ናቸው። የተወካዮች ምክር ቤት አመራሮች ከፓርላማ አባላቱ ጋር ለውይይት የተቀመጡት፤ ተመራጮቹ ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ ዞን የነበረውን ግጭት በማስመልከት ያወጡትን የአቋም መግለጫ ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ ለማድረግ ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው።

ትላንት ረቡዕ ረፋድ ላይ በተወካዮች ምክር ቤት ቅጥር ግቢ ሊሰጥ የነበረው ይህ የፓርላማ አባላቱ መግለጫ፤ ለሌላ ጊዜ መተላለፉ ከተነገረ በኋላ ነበር ውይይቱ የተካሄደው። መግለጫው እንዲራዘም የተደረገው፤ የፓርላማ አመራሮቹ “ይህን ለሚዲያ ለምን ታወጣላችሁ፤ መጀመሪያ ከእኛ ጋር እንወያይ” የሚል ጥያቄ በማቅረባቸው እንደሆነ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የፓርላማ አባል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በዚህ ሃሳብ ከስምምነት ላይ የደረሱት የፓርላማ አባላት፤ ውይይቱን ከመጀመራቸው በፊት በኦሮሚያ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ያዘጋጁትን ባለ ሶስት ገጽ ደብዳቤ ለፓርላማ አመራሮች አቅርበዋል ተብሏል። ባለ አስር ነጥብ የአቋም መግለጫ የተካተተበት ይህ ደብዳቤ የተዘጋጀው፤ የፓርላማ አባላቱ ከትላንት በስቲያ ሰኞ ህዳር 26፤ 2015 ካደረጉት ስብሰባ በኋላ ነበር። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ይህ ደብዳቤ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እና የኦሮሚያ ክልል መንግስትን ጨምሮ ለስድስት አካላት የተጻፈ ነው። ከፓርላማ አባላቱ ጋር የትላንቱን ውይይት ያካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት ደብዳቤው በግልባጭ እንዲደርሳቸው ከተደረጉ አካላት አንዱ ነው። 

የኦሮሚያ ክልል የፓርላማ ተመራጮችን ፊርማ የያዘው ይህ ደብዳቤ፤ “ለኦሮሞ ህዝብ ደህንነት እና ለሃገር ግንባታ ሂደት ያስፈልጋሉ” የተባሉ አስር ነጥቦች ተዘርዝረውበታል። “በኦሮሚያ ክልል ያለው የጸጥታ ችግር፣ ግድያ እና መፈናቀል አስደንግጦናል” ሲሉ በደብዳቤያቸው ያሰፈሩት የፓርላማ አባላቱ፤ “ይህ ችግር በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለበት” ሲሉ አቋማቸውን አስታውቀዋል።

በትግራይ ያለውን ጦርነት የቋጨውን ሰላም ስምምነት በበጎ እንደሚመለከቱት የጠቆሙት ተመራጮቹ፤ በኦሮሚያ እና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎችም ተመሳሳይ ስምምነት እንዲተገበር ጠይቀዋል። ይህ ሃሳብ በትላንቱ ውይይት ላይም በድጋሚ መነሳቱን የምስራቅ ወለጋ ዞን የፓርላማ ተመራጩ አቶ ብዙአየሁ ደገፋ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

“በሰሜኑ በኩል የተደረገው የሰላም እርቅ ኦሮሚያ ውስጥም በተመሳሳይ መልኩ መደረግ አለበት። ኢትዮጵያ ሙሉ ሰላም እንድትሆን፤ በሰሜኑ የተደረገው የሰላም ስምምነት ኦሮሚያ ውስጥም መደረግ አለበት ነው ያልነው” ሲሉ አቶ ብዙአየሁ በውይይቱ ላይ የተነሳውን ሃሳብ አብራርተዋል።

በፓርላማ አባላቱ ደብዳቤ የተጠቀሰው እና በትላንቱ ውይይት በአጽንኦት የተነሳው ሌላው ጉዳይ፤ የ“ኦሮሚያ ክልል ወሰን መከበር” የተመለከተ መሆኑን ተሳታፊዎቹ አስረድተዋል። የተወካዮች ምክር ቤት ተመራጮቹ በደብዳቤያቸው ላይ “ሁሉም የድንበር ጉዳዮች በሀገ መንግስቱ መንገድ መፈታት አለባቸው። የትኛውም ክልላዊ መንግስት፤ በየትኛውም ክልል ላይ የሚያደርገውን ማንኛውንም የኃይል ሙከራ እንቃወማለን” ሲሉ ጠንከር ባሉ ቃላት አቋማቸውን ይፋ አድርገዋል። 

በረቡዕ ውይይት “አሁን ያለው ህገ መንግስት እስከሚሻሻል ድረስ፤ ማንም ከመሬት ተነስቶ ‘ህገ መንግስቱ አይሰራም’ ማለት አይችልም። ህገ መንግስቱ መከበር አለበት” የሚል ሃሳብ መነሳቱን አቶ ብዙአየሁ ተናግረዋል። አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የውይይቱ ተሳታፊ በበኩላቸው፤ “የህግ የበላይነት ማስከበር” ጉዳይ በስብሰባው ላይ ተነስቶ እንደነበር ጠቁመዋል።  

“ችግሩ ወደ ከፋ የፖለቲካ ቀውስ እና እልቂት ሳያመራ፤ ‘መንግስት ራሱን ማስተካከል፣ ውስጡን መፈተሽ አለበት። የህግ የበላይነትን ማስከበር አለበት። ንጹሃን ሰዎች በማንነታቸውም ቢሆን በፖለቲካ መሞት የለበትም’ ብለናል”

– ከኦሮሚያ ክልል የተመረጡ የፓርላማ አባል

“ችግሩ ወደ ከፋ የፖለቲካ ቀውስ እና እልቂት ሳያመራ፤ ‘መንግስት ራሱን ማስተካከል፣ ውስጡን መፈተሽ አለበት። የህግ የበላይነትን ማስከበር አለበት። ንጹሃን ሰዎች በማንነታቸውም ቢሆን በፖለቲካ መሞት የለበትም’ ብለናል” ሲሉ የፓርላማ አባላት የሰነዘሯቸውን ሃሳቦች አስታውሰዋል። በውይይቱ ማገባደጃ ላይ “መንግስት በሆደ ሰፊነት ማየት የለበትም። ከዚህ በኋላ ህግ መከበር አለበት” የሚለው አቋም በተሳታፊዎች መያዙን ሌሎች የስብሰባው ተሳታፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። 

የትላንትናው ውይይት ሲጠናቀቅ፤ የተወካዮችን ምክር ቤት አመራሮች እና የፓርላማ የመንግስት ተጠሪው፤ ለችግሩ እልባት ለማበጀት “የተወሰነ ጊዜ ስጡን” ማለታቸውን የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል። የፓርላማ አባላቱ ያዘጋጁትን የአቋም መግለጫ በመያዝ፤ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር ለመነጋገር ማቀዳቸውንም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)