በሃሚድ አወል
በኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ወራት የወርቅ ምርት “በከፍተኛ መጠን” መቀነሱን የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶ/ር ይናገር ደሴ ተናገሩ። የባንኩ ገዢ በሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት ጥብቅ የፊስካል እና የገንዘብ ፖሊሲ መከተል አለመቻሉን ገልጸዋል።
ዶ/ር ይናገር ይህን ያሉት የብሔራዊ ባንክን የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ እና የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት፤ ለፓርላማ የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ ሐሙስ ህዳር 29 ባቀረቡበት ወቅት ነው። የባንኩ ገዢ በዚሁ ሪፖርታቸው፤ በሩብ ዓመቱ የነበረውን የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ሁኔታ ዳስሰዋል።
ባለፉት ሶስት ወራት ያለው የንግድ ሚዛን (trade balance) በከፍተኛ ሁኔታ መስፋቱን ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ በሩብ ዓመት 977 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገመት ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረቧን ያስታወቁት ዶ/ር ይናገር፤ 3.6 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ዕቃዎች ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን ደግሞ ገልጸዋል።
የሩብ ዓመቱ የወጪ ንግድ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር “መጠነኛ ጭማሪ” ማሳየቱን ያነሱት ዶ/ር ይናገር፤ ገቢው “በተወሰኑ ዘርፎች ላይ” የተገኘ መሆኑን ጠቁመዋል። ሀገሪቱ ላገኘችው ገቢ “ከፍተኛውን ድርሻ” የያዙት አበባ እና ቡና መሆናቸውን የጠቆሙት የብሔራዊ ባንክ ገዢ፤ በሌሎች ምርቶች ግን “አነስተኛ አፈጻጸም” መመዝገቡን አስረድተዋል።
አነስተኛ አፈጻጸም አላቸው ከተባሉ እና ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡ ምርቶች ግንባር ቀደሙ ወርቅ ነው። “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወርቅ ምርት በከፍተኛ መጠን ቀንሷል” ያሉት ዶ/ር ይናገር፤ ሀገሪቱ ባለፈው ሩብ ዓመት ለውጭ ገበያ ያቀረበችው የወርቅ መጠን ከሌላው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑን አስረድተዋል።
ዶ/ር ይናገር ሪፖርታቸውን ካቀረቡ በኋላ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል። የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ “ለወርቅ ምርት መቀነስ ችግሩ ምንድን ነው? የአሰራር ችግር አለ ወይስ የተለየ ነገር ነው?” ሲሉ ጥያቄ አንስተዋል። ችግሩ “ባንኩ ወርቅ ከሚገዛበት ዋጋ ጋር የተያያዘ” መሆን አለመሆኑን በተመለከተም ማብራሪያ ጠይቀዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ “አሁን ያጋጠሙን ትልቅ ክብደት ያላቸው ከመግዣ ዋጋ በላይ ያሉ ጉዳዮች ናቸው” ሲሉ የችግሩ መንስኤ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው እንዳሰቡት አለመሆኑን ጠቁመዋል። ባንኩ የወርቅ መግዣ ዋጋ ላይ ለሁለት ጊዜያት ያህል ማሻሻያ ማድረጉን ያስታወሱት ዶ/ር ይናገር፤ ሆኖም በአቅርቦት ረገድ ያለው ችግር አለመቀረፉን ተናግረዋል።
ብሔራዊ ባንክ ከዓለም የወርቅ ገበያ ላይ 35 በመቶ ጭማሪ አድርጎ ከአምራቾች እንደሚገዛ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ተናግረዋል። ገዢው “ወርቅ የሚመረትባቸው አካባቢዎች [ካለባቸው] ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ጋር ተዳምሮ፤ በወርቅ ግዢ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ፣ ከላይ እስከታች ያለ መዋቅር፣ በጥቅማጥቅም፣ በህገ ወጥ መልክ ስምሪት አድርጓል” ሲሉ የችግሩን ጥልቀት አስረድተዋል።
በዚህ የህገ ወጥ ወርቅ ንግድ ላይ “ቻይናውያን በስፋት ገብተውበታል” ሲሉም የድርጊቱ ተዋንያን ኢትዮጵያውያን ብቻ አለመሆናቸውን ጠቁመዋል። የማዕድን ሚኒስቴር ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ባወጣው መግለጫ፤ “በህገ ወጥ መንገድ ወርቅ ሲያወጡና ሲያዘዋውሩ የተገኙ የውጭ ሀገር ዜጎች መያዛቸውን አስታውቆ ነበር። በኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል እና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች ተያዙ ከተባሉት ተጠርጣሪዎች ውስጥ፤ የቻይና ዜጎች በብዛት እንደሚገኙበት ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ መግለጻቸው ይታወሳል።
ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ ምርት ባለፈው ሩብ ዓመት በከፍተኛ መጠን ቢቀንስም፤ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ከኦሮሚያ ክልሎች የሚመጣው ወርቅ ግን ባለፉት ሶስት ሳምንታት መሻሻል ማሳየቱን ዶ/ር ይናገር በምላሻቸው ማሳረጊያ ላይ ገልጸዋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሃሰን፤ በክልሉ በወርቅ ምርት የተሰማሩ ኩባንያዎች እና ልዩ አነስተኛ ማህበራት ምርታቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲያስገቡ የዛሬ ሶስት ሳምንት ገደማ ማሳሰቢያ ሰጥተው ነበር።
በዛሬው የብሔራዊ ባንክ ገዢ ሪፖርት፤ በኢትዮጵያ ያለውን የዋጋ ግሽበትን እና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትን የተመለከቱ ጉዳዮችም ተነስተዋል። የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር እየተከናወኑ ስላሉ ስራዎች ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር ይናገር፤ “በእኛ ሀገር ሁኔታ የዋጋ ግሽበቱን የምንቆጣጠረው፤ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን የገንዘብ መጠን በመጨመር እና በመቀነስ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ጥብቅ የሆነ የፊስካል እና የገንዘብ ፖሊሲ ለመከተል፤ አሁን ያለው የሀገሪቱ ሁኔታ የሚፈቅድ አለመሆኑን የብሔራዊ ባንክ ገዢው ጠቁመዋል። “በሀገር ውስጥ እና በውጭ በተፈጠሩ አንዳንድ ሁኔታዎች፤ ገንዘብ ሚኒስቴር እና እኛ ጥብቅ የሆነ የፊስካል እና የmonetary ፖሊሲ መከተል አዳጋች ሆኖብናል። የሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ ያንን ማድረግ የሚያስችል ሆኖ አላገኘነውም” ሲሉ ዶ/ር ይናገር ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)