በሃሚድ አወል
በሀዋሳ ከተማ በሚገኝ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ በሚገኙት የጉራጌ ዞን የደቡብ ክልል ምክር ቤት ተወካይ አቶ ታረቀኝ ደግፌ ላይ፤ ለሁለተኛ ጊዜ 10 የምርመራ ቀናት ተፈቀደ። የምርመራ ጊዜውን ዛሬ አርብ ህዳር 30 በዋለው ችሎት የፈቀደው፤ የደቡብ ክልል የሀዋሳ ማዕከል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው።
በዛሬው ውሎ ፖሊስ “ቀሪ የምርመራ ስራዎችን ለማከናወን” በሚል 14 ተጨማሪ ቀናት እንዲሰጡት ፍርድ ቤቱን መጠየቁን የተጠርጣሪው ጠበቃ አቶ አብዱረዛቅ ነስሩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ፖሊስ በዛሬው ችሎት የምርመራ ጊዜ ለመጠየቅ በምክንያትነት ያቀረበው ከሁለት የመንግስት ተቋማት እንዲሁም ከባንኮች ማስረጃዎችን ለማምጣት እና የዘጠኝ ምስክሮችን ቃል ለመቀበል መሆኑን ጠበቃው ገልጸዋል።
መርማሪ ፖሊስ “ማስረጃ አመጣባችኋለሁ” ያላቸው የመንግስት ተቋማት፤ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት እና የመንገዶች ባለስልጣን መሆናቸውን አቶ አብዱረዛቅ ጠቅሰዋል። ከመንገዶች ባለስልጣን የሚመጣው መረጃ፤ አቶ ታረቀኝ በተጠረጠሩበት ወንጀል ሳቢያ በመንገዶች ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን የሚያስረዳ ነው ተብሏል።
ፖሊስ ከባንኮች ሊያሰባስበው ያቀደው ማስረጃዎች የተጠርጣሪዎቹን የገንዘብ ዝውውር የሚያመለክት መሆኑን ገልጿል። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ተወካይ ከሆኑት አቶ ታረቀኝ ጋር በተመሳሳይ ወንጀል የተጠረጠሩት፤ አቶ ሰንብት ነስሩ የተባሉ ግለሰብ ናቸው።
ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በጉራጌ ዞን “ወልቂጤ ከተማ የተቀሰቀሰን ሁከት መርተዋል” በሚል መጠርጠራቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስታውቆ ነበር። ተጠርጣሪዎቹ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ህዳር 21 ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት፤ ችሎቱ ለፖሊስ ሰባት የምርመራ ቀናት መፍቀዱ ይታወሳል።
ፖሊስ በዛሬው ችሎት የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ መጠየቂያ በጹሁፍ ካቀረበ በኋላ፤ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አስተያየት የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ ለፍርድ ቤቱ በቃል አሰምተዋል። ተጨማሪ የምርመራ ጊዜውን የተቃወሙት ጠበቃው አቶ አብዱረዛቅ፤ ፖሊስ ያቀረበው ጥያቄ “ሊፈቀድለት አይገባም” በሚል ተከራክረዋል።
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ ለችሎት ካቀረቧቸው መከራከሪያዎች መካከል አንዱ ማስረጃ ይመጣባቸዋል የተባሉ ተቋማትን የተመለከተ ነው። “ከተቋማቱ ይመጣል” የተባለው ማስረጃ፤ ተጠርጣሪዎቹ ሊደርሱበት የሚችሉት ነገር ስላልሆነ “ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ሊሰጥ አይገባም” ሲሉ ጠበቃው ተሟግተዋል።
ተጠርጣሪዎቹ ቋሚ አድራሻ ያላቸው መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ በተጨማሪ ነጥብነት ያነሱት ጠበቃው፤ በዋስትና ከእስር ቢለቀቁ ግዴታቸውን አክብረው እንደሚገኙ ለችሎቱ አስረድተዋል። ለዚህ አስተያየታቸው በደጋፊ ማስረጃነት የጠቀሱት ከተጠርጣሪዎቹ አንዱ የሆኑት አቶ ታረቀኝ ደግፌ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ተመራጭ መሆናቸውን ነው።
ችሎቱ የግራ ቀኙን መከራከሪያ በጽሁፍ እና በቃል ከተቀበለ በኋላ፤ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ባለመቀበል ለፖሊስ 10 የምርመራ ቀናትን መፍቀዱን አቶ አብዱረዛቅ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ፍርድ ቤቱ የምርመራ ቀናቱን የፈቀደው፤ መርማሪ ፖሊስ ቀሪ ስራዎችን በመጪው ቀጠሮ ታህሳስ 10፤ 2015 አጠናቅቆ እንዲቀርብ መሆኑን ጠበቃው ገልጸዋል።
በጽህፈት ቤት በኩል በተካሄደው በዛሬው ችሎት እንዲገኙ የተፈቀደላቸው፤ የተጠርጣሪዎቹ “ሶስት የቅርብ ዘመድ የሆኑ ታዳሚዎች ብቻ” መሆናቸውን አቶ አብዱረዛቅ አክለዋል። በዛሬው የችሎት ውሎ፤ በቁጥጥር ስር ከዋሉ 13 ቀናት ያስቆጠሩት ሁለቱም ተጠርጣሪዎች፤ በአካል ተገኝተው ጉዳያቸውን ተከታትለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)