የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፤ በሆስፒታል፣ በትምህርት እና በእምነት ተቋማት ግቢ ውስጥ ህዝባዊ መዋጮ እንዳያካሄዱ የሚከለክል መመሪያ ስራ ሊውል ነው     

በአማኑኤል ይልቃል

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለበጎ አድራጎት ተግባራት የሚደረግ የህዝባዊ መዋጮ ማሰባሰብ ስራን በሆስፒታሎች፣ በትምህርት እና በእምነት ተቋማት ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳይፈጽሙ የሚከለክል መመሪያ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ተግባራዊ ሊደረግ ነው። በአዲሱ መመሪያ መሰረት፤ በሌላ ተቋም አማካኝነት መዋጮ የሚያሰባስቡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚከፍሉት የኮሚሽን ክፍያ፤ ከአጠቃላይ መዋጮው ከ10 በመቶ ያነሰ መሆን አለበት። 

አዲሱ መመሪያ በ2011 የወጣውን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑን በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የህግ አማካሪ የሆኑት አቶ ዮናስ ምስጋናው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፤ የንግድ ድርጅቶችን በማቋቋም፣ አክሲዮን በመግዛት እና ህዝባዊ መዋጮ በማሰባሰብ የገቢ ማስገኛ ስራዎችን ማከናወን እንደሚችሉ በአዋጁ ተደንግጓል።   

በአምስት ክፍሎች የተከፋፈለው አዲሱ መመሪያ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ገቢ በሚያስገኙ ስራዎች ላይ በምን አይነት መንገድ እንደሚሰማሩ ዝርዝር ድንጋጌዎችን የያዘ ነው። መመሪያው ካሉት 35 አንቀጾች ውስጥ አስሩ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህዝባዊ መዋጮ የሚያሰባስቡበትን ሂደት የተመለከቱ ናቸው።  

ህዝባዊ መዋጮ የሚሰበሰበው “ለበጎ አድራጎት ዓላማ” ወይም “ለጠቅላላው ህዝብ ጥቅም” ለሚውል ጉዳይ መሆኑን በመመሪያው ሰፍሯል። “በህዝባዊ መዋጮ” ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች ውስጥ፤ በተፈጥሮ ወይም ሰው ሰራሽ አደጋ ተጎዱና ለተፈናቀሉ ሰዎች የሚደረግ እርዳታ እና እገዛ አንዱ ነው። ለአካል ጉዳተኛ፣ ለአረጋውያንና ለህጻናት እንክብካቤ፣ አቅም ለሌላቸውና ለደካሞች፣ ለስራ አጦች እንዲሁም ለህክምና አገልግሎት የሚውል መዋጮም ድርጅቶቹ ከህዝብ ሊሰበስቡ እንደሚችሉ በመመሪያው ተቀምጧል። 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መዋጮዎችን በገንዘብ ወይም በአይነት ለመሰብሰብ ከመነሳታቸው አምስት ቀናት በፊት ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ማሳወቅ እንዳለባቸው መመሪያው ያዝዛል። ድርጅቶቹ ህዝባዊ መዋጮዎችን በፖስታ፣ በሳጥን፣ በካርኒ፣ በሞባይል ስልክ፣ በአጭር የመልዕክት አገልግሎት፣ በባንክ ወይም በሌላ ማናቸውም ዘዴዎች በመጠቀም ሊሰበስቡ እንደሚችሉ በመመሪያው ቢገልጽም፤ መዋጮዎች የሚካሄዱባቸው ቦታዎች ላይ ግን ክልከላ ተቀምጧል።  

አዲሱ መመሪያ፤ “በትምህርት ተቋማት፣ በሆስፒታሎች እና በእምነት ተቋማት ቅጥር ግቢ ውስጥ ህዝባዊ መዋጮ ማካሄድ የተከለከለ ነው” ሲል ቦታዎችን ይገድባል። ክልከላው የተቀመጠው፤ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ የሚከናወኑ ስራዎች እና ስርዓቶች “እንዳይረበሹ” በሚል እንደሆነ የባለስልጣኑ የህግ አማካሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከዚህ ጋር በተያያዘ “ብዙ ቅሬታዎች” ሲቀርቡለት እንደነበር የገለጹት አቶ ዮናስ፤ አንዳንድ ጊዜ በተጠቀሱት ተቋማት ግቢ ውስጥ መዋጮ የማሰባሰብ ስራው የሚከናወነው ከእነርሱ “እውቅና ውጪ” መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል። እነዚህ ተቋማት ህዝባዊ መዋጮ በቅጥር ግቢያቸው እንዳይደረግ በራሳቸው መከለክል የሚችሉ ቢሆንም፤ በመመሪያው በግልጽ እንዲቀመጥ የተደረገው “ክልከላው ህጋዊ መሰረት እንዲይዝ ለማድረግ በመፈለጉ” መሆኑን የህግ አማካሪው አስረድተዋል።

አዲሱ መመሪያ ከቦታዎች በተጨማሪ ህዝባዊ መዋጮ መሰብሰብ በሚቻልበት ጊዜ ላይ ገደብ አስቀምጧል። በመመሪያው መሰረት፤ ከቤት ውጭ ባለ ቦታ ላይ ህዝባዊ መዋጮ ማሰባሰብ የሚቻለው ከጠዋቱ አንድ ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ ነው። ይህም ገደብ የተቀመጠው በተመሳሳይ ሁኔታ ለባለስልጣኑ ከሚቀርቡለት ቅሬታዎች መነሻነት መሆኑን የሚናገሩት አቶ ዮናስ፤ “የሰዓት ገደብ የተቀመጠው ሰላማዊ የሆነ ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ እንዲሰሩ በሚል ነው” ሲሉ ምክንያቱን አብራርተዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህዝባዊ መዋጮን በሌላ ተቋም አማካኝነት በሚያሰባስቡበት ወቅት የሚፈጸም የኮሚሽን ክፍያ ጉዳይም በአዲሱ መመሪያ ድንጋጌ ተቀምጦለታል። ህዝባዊ መዋጮ የማሰባሰብ ስራን ለማከናወን “አቅም ወይም ልምድ የሌላቸው” የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፤ የማስታወቂያ ድርጅቶች እና የሁነት አዘጋጅ የመሳሰሉ ተቋማትን በመቅጠር ገንዘብ የማሰባሰብ አሰራርን ይከተሉ እንደነበር አቶ ዮናስ ይገልጻሉ። 

ሆኖም እነዚህ ተቋማት ላከናወኑት ስራ የሚያገኙት ኮሚሽን “የህግ መሰረት ያልነበረው” በመሆኑ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ ለሌሎች ስራዎች ከያዙት የፕሮጀክት በጀት ላይ “ክፍያ” ይፈጽሙ እንደነበር ያስረዳሉ። በአዲሱ መመሪያ መሰረት ግን በሌላ ተቋም አማካኝነት መዋጮ የሚያሰባስቡ ድርጅቶች፤ ለተቋሙ ክፍያ መፈጸም የሚችሉት ራሳቸው ካሰባሰቡት መዋጮ ላይ ብቻ እንደሆነ መስፈሩን ተናግረዋል። ከዚህ መዋጮ ላይ የሚከፈለው ኮሚሽንም ከ10 በመቶ ያነሰ መሆን እንዳለበት መደንገጉን አክለዋል። 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ገቢ በሚያስገኙ ስራዎች ላይ የሚሰሩበትን መንገድ የደነገገው አዲሱ መመሪያ፤ በዝርዝር ካስቀመጣቸው ጉዳዮች ውስጥ ሌላኛው የንግድ ድርጅት የሚያቋቁሙ ድርጅቶች ካፒታልን የሚመለከት ነው። ድርጅቶቹ ለሚያቋቁሙት የንግድ ድርጅት የሚሆን ካፒታል ለፕሮግራም ወጪነት ከያዙት በጀት፣ ከባንክ ከሚገኝ ብድር ወይም “ከሌላ ምንጭ” ሊመድቡ እንደሚችሉ በመመሪያው ላይ ሰፍሯል። 

ይሁንና ለሚያቋቁመት የንግድ ድርጅት በመነሻ ካፒታልነት የሚመድቡት ገንዘብ፤ የተቋቋሙበትን ዓላማ ለማስፈጸም ከያዙት በጀት “ከ30 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት” መመሪያው ገደብ አስቀምጧል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በዓመት ውስጥ ከሚመድቡት በጀት ውስጥ 80 በመቶውን ለተቋቋሙበት ዓላማ ማስፈጸሚያነት ማዋል እንዳለባቸው የሚናገሩት አቶ ዮናስ፣ “[ድርጅቱ] ሙሉ የፕሮግራም ወጪውን የንግድ ድርጅት ለማቋቋም የሚያውለው ከሆነ፤ ለተጠቃሚዎቹ የሚሰጠው ምንም አይነት አገልግሎት አይኖርም ማለት ነው” ሲሉ ገደቡ የተቀመጠበትን ምክንያት አስረድተዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሚያቋቁሙት የንግድ ተቋም የሚይዙት በጀት፤ ለፕሮግራም በሚል ከመደቡት “ከ30 በመቶ የሚበልጥ ከሆነ” ገንዘቡ የሚያዘው “በአስተዳደራዊ ወጪነት” እንደሚሆን በመመሪያው ላይ ተገልጿል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከገቢያቸው ውስጥ ለአስተዳደራዊ ወጪዎች መጠቀም የሚችሉት “20 በመቶውን ብቻ መሆኑን” በ2011 ዓ.ም. በወጣው አዋጅ ተደንግጓል። 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ የሚሰማሩበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣው አዲስ መመሪያ፤ በፍትህ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት የተመዘገበ ሲሆን ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን የህግ አማካሪው አቶ ዮናስ ገልጸዋል። በአዲሱ መመሪያው ላይ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች የሚተላለፉ ድርጅቶች፤ ለሁለት ጊዜያት ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጣቸው ተገልጿል። 

ከማስጠንቀቂያዎቹ በኋላ ለሶስተኛ ጊዜ ጥፋት ከተፈጸመ፤ “ግዴታውን ባልተወጣ የድርጅቱ ኃላፊ ወይም ሰራተኛ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ” የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ለድርጅቱ የበላይ አካል እንደሚያሳውቅ በመመሪያው ላይ ተቀምጧል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከዚህ ያለፈ ጥፋት የፈጸመን ድርጅት፤ ህዝባዊ መዋጮውን እንዲያቋርጥ ወይም ድርጅቱ እንዲፈርስ ትዕዛዝ ሊሰጥ እንደሚችል በመመሪያው ተደንግጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)