የህዳር ወር የዋጋ ግሽበት 35.1 በመቶ ሆኖ ተመዘገበ

በአማኑኤል ይልቃል

በኢትዮጵያ በተጠናቀቀው ህዳር ወር የነበረው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር 35.1 በመቶ ጭማሪ አሳየ። የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዛሬ ረቡዕ ታህሳስ 5 በድረ ገጹ ያወጣው ወርኃዊ የዳሰሳ ሪፖርት፤ የህዳር ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ከጥቅምት ወር ጋር ሲነጻጸር በ3.4 ነጥብ ከመቶ (percentage points) መጨመሩን አመልክቷል።

የኢትዮጵያን ኦፊሴላዊ ስታቲስቲክስ “ወጥ በሆነ እና በታለመለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲሰበሰብ የማድረግ ኃላፊነት” የተጣለበት የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት፤ ወርኃዊ የችርቻሮ ዋጋ ጥናትን የሚያካሄደው በሁሉም ክልሎች በተመረጡ 119 የገበያ ቦታዎች ላይ ነው። መስሪያ ቤቱ በሰበሰበው መረጃ መሰረት፤ ጥቅምት ወር ላይ መታየት የጀመረው የዋጋ ግሽበት ጭማሪ ባለፈው ወርም ቀጥሏል።

የዋጋ ግሽበቱ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ከፍተኛ የተባለውን 37.2 በመቶ ከደረሰ በኋላ እስከ መስከረም ወር ቅናሽ ሲያሳይ ቆይቷል። ባለፈው ጥቅምት ወር በአንጻሩ የዋጋ ግሽበቱ የአንድ በመቶ ጭማሪ ታይቶበት 31.7 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።  

በህዳር ወር የዋጋ ግሽበት ከፍ ያለበት ዋና ምክንያት “የምግብ እና ምግብ-ነክ ያልሆኑት የኢንዴክሱ ክፍሎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ” መሆኑን ሪፖርቱ አብራርቷል። የዋጋ ጭማሪ ከታየባቸው የምግብ ሸቀጦች ውስጥ እህሎች፣ ጥራጥሬ፣ የምግብ ዘይት እና ቅባቶች እንዲሁም ስጋና ወተት ተጠቅሰዋል። ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጦች ዝርዝር ውስጥ ደግሞ ልብስ እና ጫማ፣ የቤት ጥገና ዕቃዎች፣ ነዳጅ፣ ጫት እና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ተካትተዋል። 

የምግብ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት በህዳር ወር በ3.6 በመቶ ቢጨምርም፤ እንደ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ቃርያ እና ድንች ያሉ አትክልቶች ቅናሽ እንዳሳዩ በሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል። ቡና እና ለስላሳ መጠጦችም መጠነኛ ቅናሽ ማሳየታቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል። 

በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ግሽበት ባለፉት አራት ዓመታት ተከታታይ ጭማሪ ሲያሳይ ቆይቷል። የፌደራል መንግስት በተያዘው በጀት ዓመት የዋጋ ግሽበቱን ወደ 11.9 በመቶ የማውረድ እቅድ እንዳለው የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት በቀረቡበት ወቅት ተናግረው ነበር። ሚኒስትሩ በዚሁ ንግግራቸው፤ በተያዘው በጀት ዓመት የዋጋ ግሽበቱን ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ እንደማይቻል ለፓርላማ አባላት አስታውቀዋል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶ/ር ይናገር ደሴ ባለፈው ሳምንት ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅትም ተመሳሳይ ሀሳብ አንጸባርቀዋል። ብሔራዊ ባንክ  የዋጋ ግሽበቱን ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ ምን አይነት ስራዎችን እየሰራ እንደሆነ የተጠየቁት ዶ/ር ይናገር፤ “እንደ እቅድ [የዋጋ ግሽበትን] ወደ ነጠላ አሃዝ የማውረድ እቅድ የያዝን ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ ወደዚያ ማውረድ፤ በስድስት ወር ውስጥ እስከሚቀጥለው ሰኔ ድረስ ይቻላል የሚል እምነት የለኝም” ሲሉ ለፓርላማ የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተናግረዋል። 

የብሔራዊ ባንክ ገዢው ለዋጋ ግሽበቱ በዋነኛ ምክንያትነት የጠቀሱት “የአቅርቦት ችግርን” ነው። እርሳቸው የሚመሩት ተቋም በገንዘብ አቅርቦት በኩል ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየጣረ ቢሆንም፤ የዋጋ ቅናሽ መታየት የሚችለው ሌሎች ተቋማት ከሚወስዷቸው እርምጃዎች ጋር ሲቀናጅ መሆኑን ዶ/ር ይናገር በማብራሪያቸው ላይ አስረድተዋል። “የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ሁሉም ከምርት እና ምርታማነት ጋር ግንኙነት ያላቸው ተቋማት፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ክልሎች መረባረብ አለባቸው” ሲሉም ተደምጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[ይህ ዘገባ የተወሰነ ማስተካከያ ተደርጎበታል]