በሃሚድ አወል
“ገበያኑ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነው ሰለሞን ሹምዬ በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ። ሰለሞን በቁጥጥር ስር የዋለው ዛሬ ቅዳሜ ታህሳስ 8፤ 2015 ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ መሆኑን እህቱ ትግስት ሹምዬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግራለች።
ሰለሞን ከመያዙ በፊት የፌደራል ፖሊስ አባላት እና የየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ 1 አመራሮች፤ ወደ መኖሪያ ቤቱ ረፋድ አምስት ሰዓት አካባቢ መሄዳቸውን ትግስት አስረድታለች። የጸጥታ ኃይሎቹ እና አብረዋቸው የነበረ ሲቪል የለበሰ ሰው ወደ መኖሪያ ቤታቸው የመጡት፤ የፖሊስ ታርጋ በለጠፈች አንድ ፒክ አፕ እና በኮድ ሶስት “ዶልፊን” ተሽከርካሪዎች መሆኑን ጨምራ ገልጻለች።
የፌደራል ፖሊስ አባላቱ ሰለሞንን ይዘው ከመውጣታቸው በፊት በመኖሪያ ቤቱ ለአንድ ሰዓት ያህል “ብርበራ እና ፍተሻ” ማድረጋቸውን እህቱ ተናግራለች። ፍተሻው ሲከናወን እንዲሁም ፖሊሶቹ ሰለሞንን ሲያናግሩት “ከመኖሪያ ቤቱ አርቀው” እንዳስቀመጧት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የገለጸችው ትግስት፤ ከብርበራው በኋላ የወንድሟን ላፕቶፕ ኮምፒዩተር እና ሞባይል ስልክ ይዘው ሲወጡ ተመልክቼያለሁ ብላለች።
ሰለሞን በአዲስ አበባ ገነት ሆቴል አቅራቢያ ወደሚገኘው “የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ” መወሰዱን በስፍራው ጭምር ተገኝታ ማረጋገጧን እህቱ ተናግራለች። “ሻይ ቡና” በተሰኘው የቴሌቭዥን ፕሮግራም ይበልጥ የሚታወቀው ሰለሞን ሹምዬ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሲውል ይህ ለሁለተኛ ጊዜው ነው።
ሰለሞን ከስድስት ወራት በፊት ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል” ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ነበር። የውይይት ፕሮግራም አዘጋጁ፤ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት ውስጥ በሚገኘው ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ለአንድ ወር ገደማ በእስር ላይ ከቆየ በኋላ በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር መፈታቱ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)