በሃሚድ አወል
ዛሬ ቅዳሜ ረፋድ በፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋለው ሰለሞን ሹምዬ፤ ከአምስት ሰዓታት እስር በኋላ 10 ሰዓት ከ40 ገደማ መለቀቁን ቤተሰቦቹ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ ። ሰለሞን ዛሬ አምስት ሰዓት ገደማ ላይ በፖሊስ ከተያዘ በኋላ፤ በአዲስ አበባ ገነት ሆቴል አቅራቢያ ወደሚገኘው “የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ መወሰዱን” እህቱ ትግስት ሹምዬ አስታውቃ ነበር።
“ገበያኑ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነው ሰለሞን ከእስር ከተፈታ በኋላ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጋር ባደረገው የስልክ ቆይታ፤ እንዴት እንደተለቀቀ እና በፖሊስ ሲያዝ የነበሩ ሁኔታዎችን በተመለከተ ለቀረቡለት ጥያቄዎች አጭር ምላሽ ሰጥቷል። ሰለሞን ከእስር ስለተለቀቀበት ሁኔታ ሲገልጽ “ምንም የነገሩኝ ነገር የለም። ስንፈልግህ እንጠራሃለን አሉኝ” ሲል ሂደቱን አስረድቷል።
በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ በአስር ላይ በቆየባቸው አምስት ሰዓታት በመደበኛ መልኩ ቃሉን እንዳልሰጠ የገለጸው ሰለሞን፤ “ኢንፎርማሊ ጥያቄዎች ነበሩ” ብሏል። ሆኖም ስለቀረቡለት ጥያቄዎች ዝርዝር ጉዳዮች ከመናገር ተቆጥቧል። ዛሬ ረፋድ ላይ ፈረንሳይ ለጋሲዮን በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በቁጥጥር ስር የዋለው ሰለሞን፤ የያዙት ፖሊሶች የፍርድ ቤት ማዘዣ አለመያዛቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል።
“የፍርድ ቤት ማዘዣ በቃል ተሰጥቶናል ነው ያሉት። ወረቀት አላሳዩኝም” የሚለው ሰለሞን፤ የፌደራል ፖሊስ ደንብ ልብስ እና ሲቪል ለበሱት የጸጥታ ኃይሎች የአንድ ዳኛን ስም በመጥራት “የመበርበሪያ ፈቃድ ሰጥቶናል” ብለው ቤቱን እንደበረበሩ አክሏል። የጸጥታ ኃይሎቹ ሲወስዱት በፍተሻ ወቅት ያገኟቸውን፤ ላፕቶፕ ኮምፒዩተር፣ የሞባይል ስልክ እና “ፍላሽ ዲስክ” አብረው መውሰዳቸውን ጠቁሟል። እነዚህን ዕቃዎች ሰኞ ጠዋት መጥቶ መውሰድ እንደሚችል በተለቀቀበት ወቅት እንደተነገረውም ጨምሮ ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)