ኢህአፓ፣ መኢአድ እና እናት ፓርቲ የትብብር ስምምነት ሊፈራረሙ ነው 

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና እናት ፓርቲ አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን የትብብር ስምምነት ሊፈራረሙ ነው። ሶስቱ ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ትብብር ወደ ቅንጅት ሊያመራ እንደሚችል የፓርቲዎቹ አመራሮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ሶስቱ ፓርቲዎች በመጪው አርብ ታህሳስ 14፤ 2015 የትብብር ስምምነት እንደሚፈራረሙ የኢህአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም ገልጸዋል። የእናት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ ጌትነት ወርቁ እና የመኢአድ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይበቃል ደሳለኝ፤ ሶስቱ ፓርቲዎቹ በጋራ ለመስራት ሊፈራረሙ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። 

የትብብር ስምምነቱን የያዘው ሰነድ፤ ፓርቲዎቹ የሚያግባቧቸው ጉዳዮች ምን እንደሆኑ፣ ትብብሩ እንዳይፈርስ ከፓርቲዎች የሚጠበቁ ኃላፊነቶች እና በትብብሩ አተገባበር ላይ ችግሮች ቢፈጠሩ የሚፈቱባቸው መንገዶች የሰፈሩበት መሆኑን መጋቢ ብሉይ አስረድተዋል። አቶ ይበቃል በበኩላቸው “በጋራ ለመስራት ከተስማማንባቸው ጉዳዮች መካከል ምርጫ አንዱ እና የመጀመሪያው ነው” ሲሉ ሶስቱ ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ከተግባቡባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱን ጠቅሰዋል። 

በስምምነቱ መሰረት ሶስቱ ፓርቲዎች፤ በዚህ ዓመት ሊካሄድ በዕቅድ በተያዘው የአካባቢ ምርጫ እና ከሶስት አመት በኋላ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በጋራ ይሰራሉ። “ወደፊት ለሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ መሰራት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጠን የምናደርገው ዝግጅት ይኖራል። አሁን ግን ዋና ትኩረታችን በቀጣዩ የአካባቢ ምርጫ በጋራ መስራት ነው” ሲሉ አቶ ይበቃል ምርጫን በተመለከተ የፓርቲዎቹ ዕቅድ ምን እንደሆነ አብራርተዋል። 

የኢህአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር በበኩላቸው ምርጫን በተመለከተ የሶስቱ ፓርቲዎች የረዥም ጊዜ ዕቅድ “ምርጫን በጋራ ተወዳድሮ ማሸነፍ” መሆኑን ገልጸዋል። ይህን ዕቅድ እውን ለማድረግ ፓርቲዎቹ “የጋራ [የምርጫ] ፕሮግራም እና አርማ በማዘጋጀት” ሊወዳደሩ እንደሚችሉ መጋቢ ብሉይ አብርሃም ጠቁመዋል።

ሶስቱ ፓርቲዎች ከምርጫ በተጨማሪ በመጪው የካቲት ወር ይጀመራል ተብሎ በሚጠበቀው የሀገራዊ ምክክር ላይም በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን አስታውቀዋል። ትብብር የሚፈጥሩት ፓርቲዎች በሀገራዊ ምክክሩ ላይ አጀንዳዎችን በጋራ እስከ ማቅረብ የሚደርስ ዕቅድ አላቸው። መጋቢ ብሉይ አብርሃም “በየክልሉ ላሉ ለአባሎቻችን መመሪያ እንሰጣለን። የትብብሩ አካል የሆኑ ፓርቲዎች አባላትም የጋራ አቋም ያንጸባርቃሉ” ሲሉ በምክክሩ አጀንዳ ቀረጻ ላይ ፓርቲዎቹ ስለሚሳተፉበት ሂደት አብራርተዋል።  

“የህገ መንግስት፣ የብሔር ፌደራሊዝም እና የጣምራ ዜግነት” ጉዳይ፤ ፓርቲዎቹ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ እንዲነሱ የሚፈልጓቸው የጋራ አጀንዳዎች መሆናቸውን የኢህአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አስረድተዋል። መጋቢ ብሉይ አብርሃም “የሚለያዩን ጉዳዮች ላይ በተናጥል የምናነሳቸው ጉዳዮች ይኖራሉ” ሲሉም ፓርቲዎቹ ለየብቻቸው ሊያቀርቧቸው የሚችሉ አጀንዳዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል።

ከምርጫ እና ሀገራዊ ምክክር የጋራ ተሳትፎ ባሻገር ኢህአፓ፣ መኢአድ እና እናት ፓርቲ ወደ ፊት በሀገሪቱ ውስጥ በሚፈጠሩ ወቅታዊ ሁነቶች ላይ “የጋራ አቋም” በመያዝ መግለጫዎች ለማውጣት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውንም አቶ ይበቃል ተናግረዋል። የመኢአዱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ይህን ቢሉም፤ ፓርቲዎቹ በትብብር ለመስራት ከስምምነት ከመድረሳቸው አስቀድሞ የጋራ መግለጫዎችን በተደጋጋሚ ሲሰጡ ቆይተዋል። ሶስቱ ፓርቲዎቹ ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር ጀምሮ ባሉት ስምንት ወራት ውስጥ ለአራት ጊዜያት ያህል በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሶስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን የሚያደርጉት ትብብር ወደ ቅንጅት፣ ጥምረት አሊያም ውህደት ሊያመራ እንደሚችል አመራሮቹ ፍንጭ ሰጥተዋል። “ይሄ ትብብር እያደገ መጥቶ የተሻለ፣ በጋራ ሊያሰሩ የሚችሉ ጉዳዮች ሲኖሩ እና የበለጠ መግባባቶች እየተፈጠሩ ከመጡ በኋላ፤ ቅንጅትም፣ ግንባርም ሊፈጠር የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል” ሲሉ አቶ ይበቃል የፓርቲዎቹ ቀጣይ እርምጃ ምን ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

የኢህአፓው ተቀዳሚ ፕሬዝዳንትም የአቶ ይበቃልን ሃሳብ አስተጋብተዋል። “ከትንሽ ጀምረን ከዚያ ወደ ቅንጅት፣ ጥምረት እስከ ውህደትም ልንደርስ እንችላለን” ሲሉ ፓርቲዎቹ “እየተግባቡ ሲመጡ” ትብብራቸውን ከፍ ወዳለ ደረጃ ሊያሸጋገሩት እንደሚችሉ አመልክተዋል። በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ መሰረት፤ ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተዋህደው አንድ የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት ይችላሉ። 

የራሳቸው ፕሮግራም፣ መተዳደሪያ ደንብ እና አባላት ያሏቸው የፓለቲካ ፓርቲዎች ፓርቲዎች የጋራ ግንባር ሊፈጥሩ እንደሚችሉም በአዋጁ ተቀምጧል። ከዚህ በተጨማሪም ፓርቲዎች “ለተወሰነ ጊዜ እና በተወሰኑ ጉዳች ዙሪያ ተቀናጅተው፤ እንደ ሁኔታው በሀገር ወይም በክልል ደረጃ ሊንቀሳቀሱ” እንደሚችሉ በአዋጁ ተደንግጓል። 

የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት፣ ግንባር ወይም ቅንጅት ሲፈጥሩ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረብ እንደሚገባቸው በአዋጁ ላይ ተቀምጧል። ፓርቲዎች ውህደት ወይም ቅንጅት ለመፍጠር የሚቀርቡት ጥያቄ፤ ጠቅላላ ወይም የአካባቢ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ከመውጣቱ ሁለት ወራት በፊት በጽሁፍ መቅረብ እንዳለበት በአዋጁ ሰፍሯል። ግንባር የሚፈጥሩ ፓርቲዎች በተመለከተ ግን ጥያቄያቸውን ለቦርዱ በጽሁፍ የሚቀርብበት የጊዜ ገደብ በአዋጁ በግልጽ አልተቀመጠም። 

“ይህ ትብብር ስለሆነ ለምርጫ ቦርድ ማሳወቅ አይጠበቅብንም። ግንባር ወይም ቅንጅት ፈጥረን የምንሰራ ቢሆን ኖሮ ለምርጫ ቦርድ የማሳወቅ ግዴታ ይኖርብን ነበር”

ኢህአፓ፣ መኢአድ እና እናት ፓርቲ ስለደረሱበት የትብብር ስምምነት ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ

ህጋዊ እውቅና የተሰጣቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች “በትብብር ስለሚሰሩባቸው” ሌሎች መንገዶች በተመለከተ በአዋጁ የሰፈረ ድንጋጌ የለም። ኢህአፓ፣ መኢአድ እና እናት ፓርቲ የሚፈራረሙትን የትብብር ስምምነት በተመለከተ ለምርጫ ቦርድ አስታውቀው እንደሆነ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “ይህ ትብብር ስለሆነ ለምርጫ ቦርድ ማሳወቅ አይጠበቅብንም። ግንባር ወይም ቅንጅት ፈጥረን የምንሰራ ቢሆን ኖሮ ለምርጫ ቦርድ የማሳወቅ ግዴታ ይኖርብን ነበር” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)