በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ክስ ላይ ፍርድ ለመስጠት፤ የመከላከያ ሚኒስቴር ቃለ ጉባኤ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጠ 

በሃሚድ አወል

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ የ“ፍትሕ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ በቀረበበት ክስ ላይ ፍርድ ለመስጠት ያስችለው ዘንድ፤ “ለመከላከያ ሰራዊት አባላት ሽልማት እና ማዕረግ የተሰጠበት ቃለ ጉባኤ እንዲቀርብለት” ትዕዛዝ አስተላለፈ። ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን ያስተላለፈው “ለትክክለኛ ፍርድ እንዲረዳው” መሆኑን ዛሬ ረቡዕ ታህሳስ 12፤ 2015 በዋለው ችሎት አስታውቋል።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው በጋዜጠኛው ጉዳይ ላይ የቀረበውን ክስ መርምሮ ፍርድ ለመስጠት ነበር። ሆኖም ፍርድ ቤቱ “ብይን ለመስጠት የሚያስፈልገው” ተጨማሪ ማስረጃ መኖሩን በመጥቀስ ፍርዱን ሳይሰጥ ቀርቷል። 

ፍርድ ቤቱ የጠቀሰው ማስረጃ፤ ከአንድ ዓመት በፊት ለመከላከያ ሰራዊት አባላት ከተሰጠው ሽልማት እና የማዕረግ ዕድገትን በተመለከተ የተያዘን ቃለ ጉባኤ ነው። ችሎቱ ይኸው ቃለ ጉባኤ ከመከላከያ ሚኒስቴር እንዲመጣለት በዛሬው ውሎው አዝዟል። 

ጋዜጠኛ ተመስገን እንዲከላከል በፍርድ ቤት በተወሰነበት ክስ ከቀረቡት ሁለት ፍሬ ነገሮች መካከል አንደኛው፤ የመከላከያ ሰራዊት ሽልማት እና የማዕረግ አሰጣጥን አስመልክቶ “ፍትሕ” መጽሔት ላይ የጻፈው ጽሁፍን የተመለከተ ነው። ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ በ“ፍትሕ” መጽሔት የወጣው ይህ የተመስገን ጽሁፍ፤ “መከላከያ ተቋማዊ ወይስ ኔትዎርክ” በሚል ርዕስ የታተመ ነው።

ተመስገን በዚህ ጽሁፉ ለመከላከያ ሰራዊት አባላት የተሰጠውን ሽልማት እና ማዕረግ አሰጣጥ “የብሔር የበላይነት የተጫነው ነው” ሲል ተችቷል። በሽልማት እና ማዕረግ አሰጣጡ “ግንባር ደርሰው የማያውቁ እና በሰላም አስከባሪነት በውጪ ሀገር የነበሩ ኦሮምኛ ተናጋሪ መኮንኖችንም ጨምሯል” ሲል ተመስገን የሽልማት እና ማዕረግ አሰጣጡን መንቀፉ በክሱ ላይ ተገልጿል። ለመከላከያ ሰራዊት አባላት ሽልማት እና የማዕረግ የተሰጠው፤ “በጦር ሜዳ ጀብዱ ለሰሩ ወታደሮች እና ኃይል ለመሩ አመራሮች” መሆኑ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።   

ጋዜጠኛው ይህን ሽልማት እና የማዕረግ ዕድገት በተመለከተ የጻፈውን ጽሁፍ፤ ዐቃቤ ህግ በመሰረተው ክስ በሰነድ ማስረጃነት አካትቶታል። ዐቃቤ ህግ በበተመስገን ላይ በመጀመሪያ ያቀረባቸው ሶስት ተደራራቢ ክሶች ሲሆኑ፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ባሳለፈው ውሳኔ ግን ተከሳሹን ከሁለቱ ክሶች በነጻ አሰናብቷል። 

ተመስገን ነጻ ከተባለባቸው ሁለት ክሶች የመጀመሪያው “ወታደራዊ ምስጢርን መግለጽ” በተመለከተ በወንጀል ህጉ የተደነገገውን አንቀጽ ተላልፏል የሚል ነው። በጋዜጠኛው ላይ የቀረበው እና ውድቅ የተደረገው ሁለተኛው ክስ ደግሞ “የሀሰት ወይም የሚያደናግር መረጃ አሰራጭቷል” በሚል የቀረበ ነበር።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጥቅምት ወር መጀመሪያ በነበረው የችሎት ውሎ፤ በዐቃቤ ህግ የቀረበውን ሶስተኛ ክስ ድንጋጌ በመቀየር ተመስገን በተቀየረው አንቀጽ እንዲከላከል ወስኗል። ጋዜጠኛው ላይ የቀረበው ሶስተኛ ክስ “መገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት የወንጀል ተግባር” ፈጽሟል የሚል ነበር። ተመስገን “የህዝቡን ሞራል ዝቅ ለማድረግ፣ እምነቱን ወይም የመቋቋም ኃይሉን በተቀናጀ ዘዴ ለማፍረስ በማሰብ” በ“ፍትሕ” መጽሔት የተለያዩ እትሞች ላይ “ስምንት ጹሁፎችን እንዲሰራጭ አድርጓል” በሚል ነበር የተወነጀለው። 

በተከሳሹ ላይ የቀረበውን የወንጀል ድንጋጌ የቀየረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ተመስገን “የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር” በወጣው አዋጅ መሰረት እንዲከላከል ውሳኔ አሳልፎ ነበር። ፍርድ ቤቱ በዚህኛው ፍሬ ነገር እንዲቀርብለት ያዘዘውን ማስረጃ ውጤት ለመጠባበቅ፤ ለታህሳስ 27፤ 2015 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። 

ተመስገን ደሳለኝ ከቀረቡበት ሁለት ክሶች ነጻ መሆኑን ተከትሎ በጠበቆቹ በኩል ያቀረበው የዋስትና ጥያቄ ተቀባይነት በማግኘቱ፤ ከአንድ ወር በፊት በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር መለቀቁ ይታወሳል። ጋዜጠኛው የዛሬውን የፍርድ ቤት ውሎ ከሁለት ጠበቆቹ ጋር በመሆን በችሎት ተገኝቶ ተከታትሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)