የደቡብ ክልል ምክር ቤት የጉራጌ ዞን ተመራጭ ላይ፤ ፍርድ ቤት ለሶስተኛ ጊዜ የምርመራ ቀናትን ፈቀደ 

በሃሚድ አወል

በደቡብ ክልል ምክር ቤት የጉራጌ ዞን ተመራጭ በሆኑት አቶ ታረቀኝ ደግፌ ላይ ለሶስተኛ ጊዜ አስር የምርመራ ቀናት ተፈቀደ። የምርመራ ጊዜውን የፈቀደው የደቡብ ክልል የሀዋሳ ማዕከል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤ የፖሊስን የምርመራ ውጤት ለመጠባበቅ ለታህሳስ 21 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የምክር ቤት አባሉ ጉዳይ ለዛሬ ታህሳስ 12፤ 2015 የተቀጠረው፤ የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንን የምርመራ መዝገብ አይቶ ውሳኔ ለመስጠት ነበር። ፖሊስ ትላንት ለችሎቱ ባስገባው የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ላይ “ምርመራ ለማድረግ” በሚል ተጨማሪ 14 ቀናት መጠየቁን የተጠርጣሪው ጠበቃ አቶ አብዱረዛቅ ነስሩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።  

የታረቀኝ ጠበቃ በበኩላቸው፤ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የጠየቀውን የምርመራ ቀናት ውድቅ በማድረግ፤ የደንበኛቸውን የዋስትና መብቱን እንዲያከብርለት ተከራክረዋል። የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ችሎቱ፤ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንዲቀርብለት በትላንትናው የችሎት ውሎ ትዕዛዝ አስተላልፎ እንደነበር አቶ አብዱረዛቅ ገልጸዋል።

የምርመራ መዝገቡ ዛሬ የቀረበለት የደቡብ ክልል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤ “ለምርመራ ጊዜው ተጨማሪ ጊዜ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን በማመን” ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ አስሩን ፈቅዷል። ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ቀናትን የጠየቀው የተጠርጣሪውን የገንዘብ ዝውውር ከንግድ ባንኮች ለማጣራት እንዲሁም ከብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ተጨማሪ ማስረጃዎችን ለማምጣት በሚል መሆኑን አቶ አብዱረዛቅ ተናግረዋል።

“በወልቂጤ ከተማ የተቀሰቀሰን ሁከት መርተዋል” በሚል ተጠርጥረው ከ25 ቀናት በፊት የታሰሩት አቶ ታረቀኝ ደግፌ ዛሬ ጉዳያቸውን በችሎት ተገኝተው ተከታትለዋል። ከአቶ ታረቀኝ ጋር በተመሳሳይ ወንጀል የተጠረጠሩት አቶ ሰንብት ነስሩም በተመሳሳይ ዛሬ ችሎት ፊት ቀርበዋል።

ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ከዚህ በፊት ለሁለት ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ህዳር 21 በነበረው የመጀመሪያው የችሎት ውሎ፤ ለፖሊስ ሰባት የምርመራ ቀናት ተፈቅደውለት ነበር። ተጠርጣሪዎቹ በተመሳሳይ ህዳር 30 ችሎት በቀረቡበት ወቅት፤ ፍርድ ቤቱ 10 የምርመራ ቀናት ለፖሊስ መፍቀዱ ይታወሳል። 

በአዲስ አበባ ከተማ በፖሊስ ከተያዙ በኋላ ወደ ሀዋሳ ከተማ የተወሰዱት አቶ ታረቀኝ፤ ጉዳያቸውን እየተከታተሉየሚገኙት በሀዋሳ ከተማ በሚገኝ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ ሆነው ነው። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) በመወከል ለደቡብ ክልል ምክር ቤት የተመረጡትን የአቶ ታረቀኝ እስር በተመለከተ ከፓርቲው በቀረበ አቤቱታ መሰረት፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ማብራሪያ እንዲሰጥ መጠየቁን አስታውቆ ነበር። 

ምርጫ ቦርድ ከአንድም ሁለት ጊዜ ጥያቄውን በደብዳቤ ቢያቀርብም፤ ምላሽ አለማግኘቱን ባለፈው ሳምንት ባሰራጨው መረጃ አመልክቷል። ቦርዱ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ታህሳስ 5፤ 2015 ለሶስተኛ ጊዜ በጻፈው ደብዳቤ፤ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን “ምላሽ ያልሰጠበትን ምክንያት እንዲገልጽ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ የደረሰበትን ሂደት በአስቸኳይ እንዲያሳውቅ” በድጋሚ ጠይቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)