የሲሚንቶ ዋጋ በድጋሚ “በነጻ ገበያ” እንዲመራ ተወሰነ

በአማኑኤል ይልቃል

ካለፈው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ጀምሮ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ዋጋ ሲወሰንለት የነበረው የሲሚንቶ ገበያ፤ ከነገ ጀምሮ “በነጻ ገበያ” እንዲመራ ተወሰነ። አዲሱ ውሳኔ፤ በየአካባቢው የሚኖረውን የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ የመወሰን ኃላፊነት ለፋብሪካዎች ሰጥቷል። ውሳኔው ከዚህ በተጨማሪም፤ በፋብሪካዎች መካከል ያሉትን አከፋፋዮች እና ቸርቻሪዎችን ከሲሚንቶ ገበያ ስርዓት እንዲወጡ ያደረገውን አሰራር የቀለበሰ ሆኗል። 

ላለፉት አምስት ወራት በስራ ላይ በነበረው አሰራር መሰረት፤ የሲሚንቶ አከፋፋዮች የሚመረጡት በክልል እና በከተማ አስተዳደሮች አማካኝነት ነበር። አሁን ይፋ የተደረገው አዲስ መመሪያ በአንጻሩ፤ ፋብሪካዎች “የሲሚንቶ ምርቱን ተደራሽ ያደርጉልኛል” የሚሏቸውን አከፋፋዮች ራሳቸው እንዲመርጡ ነጻነት የሰጠ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ተሻለ በልሁ ዛሬ ታህሳስ 13፤ 2015 በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአዲስ መመሪያ ሊተገብረው ስላሰበው አሰራር ማብራሪያ የሰጡት ሚኒስትር ዲኤታው፤ ከሐምሌ ወር ጀምሮ በመመሪያ የተተገበረው አሰራር ውጤቶችን ቢያስገኝም እንደ ምርት እጥረት ያሉ ተግዳሮቶች መፈጠራቸውን አስረድተዋል። ካሉት ከአስር በላይ ፋብሪካዎች ውስጥ “በአግባቡ አምርተው ለገበያ ማቅረብ የቻሉት” ከሶስት እንደማይበልጡ አቶ ተሻለ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ ከተሰራጨው 18.9 ሚሊዮን ኩንታል ሲሚንቶ ውስጥ፤ 10.2 ሚሊዮን የሚሆነውን ያመረተው ዳንጎቴ ፋብሪካ መሆኑን በማሳያነት አንስተዋል።

በመንግስት የተመረጡት አከፋፋዮች በተቀመጠው አሰራር መሰረት አለማቅረባቸው እና “ህገ ወጥ ሽያጭ” መከናወኑ በዛሬው መግለጫ በችግርነት ከተነሱ ጉዳዮች ውስጥ ይገኙበታል። በዚህ መነሻነት የሲሚንቶ ገበያው በድጋሚ በነጻ ገበያ እንዲመራ መወሰኑን የሚገልጹት አቶ ተሻለ፣ ለዚህም አዲስ መመሪያ መዘጋጀቱን አስረድተዋል። የሲሚንቶ አከፋፋዮች የሚመረጡት በመንግስት እንዲሆን መደረጉን ተከትሎ፤ ከግብይት ሰንሰለቱ ውስጥ እንዲወጡ ተደርገው የነበሩ አከፋፋይ እና ቸርቻሪዎች እንዲመለሱ መደረጉ አዲሱ መመሪያ ካመጣቸው ለውጦች መካከል አንዱ ሆኖ ተጠቅሷል። 

ካለፈው መመሪያ ላይ የቀጠለው እና በአዲሱ መመሪያ ላይ “በጊዜያዊነት” ይቆያል የተባለው ጉዳይ፤ ሲሚንቶ በፋብሪካዎች በር የሚሸጥበት ዋጋ በመንግስት መወሰኑ ነው። ይህ አሰራር የሚቀጥለው የፋብሪካዎቹ ምርታማነት እስከሚጨምር እና የሚፈለገው ያህል ሲሚንቶ ገበያው ላይ እስከሚኖር ድረስ መሆኑን ሚኒስትር ዲኤታው ገልጸዋል።

ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ይህን የቆየ አሰራር በመጠቀም፤ ከመስከረም መጀመሪያ አንስቶ ተግባራዊ ሲደረግ በነበረው የሲሚንቶ የፋብሪካ መሸጫ ዋጋ ላይ ማሻሻያ አድርጓል። በአራት ወራት ውስጥ በድጋሚ የተወሰነው የፋብሪካ በር መሸጫ ዋጋ፤ ቀድሞ በአማካይ 590 ብር ሲሸጥ የነበረውን ሲሚንቶ በአማካይ 758 ብር እንዲደርስ አድርጎታል።

የዋጋ ማሻሻያ  የተደረገው መሰረታዊ የሆኑ ጉዳዮች ታይተው መሆኑን ለጋዜጠኞች የገለጹት አቶ ተሻለ፤ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ አለመሆኑ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል። “በሙሉ አቅሙ የማያመርት ፋብሪካ አስተዳደራዊ ወጪ ጫናው ከፍተኛ ይሆናል” ሲሉም አብራርተዋል።

ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በፋብሪካዎች በር ላይ የሚደረገውን የሲሚንቶ ሽያጭ ዋጋ የመወሰን ስልጣኑን በአዲሱ መመሪያ ይዞ ቢቀጥልም፤ በየአካባቢው የሚኖረውን የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ የመወሰን ኃላፊነት ግን ወደ ፋብሪካዎች እንዲተላለፍ አድርጓል። ፋብሪካዎቹ በመንግስት የተወሰነውን የፋብሪካ በር መሸጫ ዋጋን መነሻ በማድረግ፤ የሲሚንቶ ማጓጓዣ፣ የጫኝ እና አውራጅ ወጪዎችን እንዲሁም “ውስን የትርፍ ህዳግን” በማካተት የመሸጫ ዋጋን ለሚኒስቴሩ የማቅረብ ግዴታ እንደተጣለባቸው አቶ ተሻለ ገልጸዋል።

“የመሸጫ ዋጋ ችግር ካጋጠማችሁ፤ ችግር የፈጠረው ፋብሪካው ነው” ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው፤ ፋብሪካዎች የሚመርጧቸው አከፋፋዮች በደረሰኝ የሚሸጡ መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል። የተመረጡት አከፋፋዮች እና ቸርቻሪዎች ከተቀመጠላቸው የመሸጫ ጣራ በላይ እንዳይሸጡ የመከታተል እና ሲሸጡ ከተገኙ ውላቸውን አፍርሰው ለመንግስት የማሳወቅ ኃላፊነትም የፋብሪካዎች ሆኗል።

በተጨማሪም ፋብሪካዎቹ ምርት የሚያከፋፍሉላቸውን አካላት ሲመርጡ፤ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል “ተደራሽነት የሚያሳልጥላቸውን የአሰራር ስርዓት” መዘርጋት እንደሚጠበቅባቸው ሚኒስትር ዲኤታው አስረድተዋል። በአዲሱ መመሪያ ላይም፤ ፋብሪካዎች አስፈላጊ ከሆነ በየአካባቢዎቹ ርክክብ የሚፈጸምበት የሲሚንቶ መጋዘን ማዘጋጀት እንዳለባቸው ተቀምጧል።

መንግስት በበኩሉ የሲሚንቶ ምርት ከፋብሪካ ለተጠቃሚዎች የሚቀርብበት ሂደት “በተገቢው ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን” የማረጋገጥ ስራ እንደሚሰራ ሚኒስትር ዲኤታው ተናግረዋል። ይሁንና በመንግስት የሚከናወነው የቁጥጥር ስራ የሲሚንቶ ምርትን “ነጻነት የማንቀሳቀስ” ምርትን የሚያግድ እንደማይሆን ገልጸዋል።

አቶ ተሻለ እንደሚናገሩት፣ የቀድሞው መመሪያ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ “በቁጥጥር ስም ሲሚንቶ የሚያድኑ” አካላት መብዛት በችግርነት ታይቷል። በአዲሱ መመሪያ በክልከላነት ከተቀመጡ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ይህንን የተመለከተ ነው። ሚኒስቴሩ ዛሬ ይፋ ባደረገው አዲስ መመሪያ መሰረት፤ የሲሚንቶ እንቅስቃሴን በኬላዎችም ሆነ በተለያዩ ስፍራዎች  “በመገደብ” እና “ምርቱን በመውረስ”፤ “ነጻ የግብይት ሂደትን ማወክ” እንደማይቻል አስታውቋል።

“ከዛሬ ጀምሮ ሲሚንቶ ክትትል፣ ቁጥጥር እየተባለ የሚታደንበት ስርዓት የለም… ማንኛውም አካል በጉዞ ላይ ሲሚንቶን መያዝም፣ መውረስም አይችልም”

አቶ ተሻለ በልሁ – የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ

“ከዛሬ ጀምሮ ሲሚንቶ ክትትል፣ ቁጥጥር እየተባለ የሚታደንበት ስርዓት የለም” ሲሉ ማብራሪያ የሰጡት ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ተሻለ፤ አክለውም “ማንኛውም አካል በጉዞ ላይ ሲሚንቶን መያዝም፣ መውረስም አይቻልም” ብለዋል። ይህን በተመለከተ ተቆጣጣሪ አካላት ከዚህ ቀደም የተሰጣቸው ኃላፊነት እንደተነሳ እና ቁጥጥር የሚካሄደው በመሸጫ ደረሰኝ ላይ ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]