የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን የኢኮኖሚ ድጋፍ በሂደት ሙሉ በሙሉ ወደነበረበት ለመመለስ ቅድመ ሁኔታዎች አስቀመጠ

የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የልማት ትብብር እና ለአገሪቱ የሚሰጠውን የኢኮኖሚ ድጋፍ በሂደት ሙሉ በሙሉ ወደነበረበት ለመመለስ፤  የፕሪቶሪያውን “በቋሚነት ግጭት የማቆም ስምምነት” ትግበራ እንደ ቅድመ ሁኔታ አስቀመጠ። የስምምነቱ በዘላቂነት ተግባራዊ መሆን፤ የአውሮፓ ህብረት  ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ስትራቴጂክ ግንኙነት በፖለቲካዊ ውይይት ጭምር እንደገና ለማስጀመር እንደሚያስችል አስታውቋል።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተቀሰቀሰ በጥቂት ቀናት ልዩነት ለአገሪቱ የሚሰጠውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር የበጀት ድጋፍ ያቋረጠው የአውሮፓ ህብረት፤ ከአዲስ አበባ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማረቅ ሊሟሉ ይገባል ያላቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ያስቀመጠው ዛሬ ታህሳስ 13፤ 2015 ባወጣው መግለጫ ነው። ህብረቱ ወደ 90 ሚሊዮን ዩሮ ከሚጠጋው የበጀት ድጋፍ በተጨማሪ፤ ለኢትዮጵያ ያዘጋጀው አንድ ቢሊዮን ዩሮ የልማት እርዳታ በጦርነቱ ምክንያት ሳይያጸድቅ ቀርቷል።

በተደጋጋሚ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር የተገናኙት የአውሮፓ ህብረት ሹማምንት የፕሪቶሪያው “በቋሚነት ግጭት የማቆም ስምምነት” ከመፈረሙ በፊት የተቋረጠውን የበጀት ድጋፍ እና የልማት ትብብር ለማስቀጠል ሊሟሉ ይገባል ያሏቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በዝርዝር ሲያቀርቡ ነበር።

በአውሮፓ ካውንስል በኩል የወጣው የዛሬው የህብረቱ ቅድመ ሁኔታ፤ የቀደሙትን ያካተተ ቢሆንም በዋናነት በፕሪቶሪያው ስምምነት ትግበራ ማዕቀፍ የቀረበ ነው። በተኩስ አቁም፣ ያልተገደበ የእርዳታ አቅርቦት፣ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግጋት እና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተጠያቂነት ረገድ “ተጨባጭ መሻሻል” የህብረቱን የልማት ትብብር እና የኢኮኖሚ ድጋፍ እንደገና ለማስጀመር እንደሚፈቅድ አስታውቋል።

ህብረቱ ከዚህ ቀደም የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ እንዲወጡ በተደጋጋሚ ሲያቀርብ የነበረው ጥሪም በዛሬው መግለጫ የተካተተ ነው። “የኢትዮጵያ መረጋጋት እና የግዛት አንድነት እንደ ሰላማዊ ልማት ሁሉ ለአውሮፓ እና ለቀጠናው ቁልፍ ጉዳይ” መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፤ የአገሪቱ ጎረቤቶች ለፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ ተግባራዊነት “ገንቢ ሚና” እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከ22 ዓመታት ገደማ በፊት በአልጀርስ የተፈራረሙት ስምምነት እና የ2010 “Peace Declaration” ጠቃሚ መሆናቸውን ያስታወሰው የአውሮፓ ህብረት፤ የኤርትራ ወታደሮች ሙሉ በሙሉ በአፋጣኝ ሊወጡ እንደሚገባ ጥሪ አቅርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)