በአማኑኤል ይልቃል
ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከመስከረም መጀመሪያ አንስቶ ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው የሲሚንቶ የፋብሪካ መሸጫ ዋጋ ላይ ማሻሻያ አድርጓል፡፡ ከትላንትና ጀምሮ ለፋብሪካዎች ተሰራጭቷል የተባለው የዋጋ ማሻሻያ ከ506 ብር እስከ 683 ብር የነበረውን የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ የፋብሪካ በር ዋጋ ከ750 ብር እስከ 795 ብር አድርሷል፡፡
በአዲሱ ዋጋ ላይ ከፍተኛው የፋብሪካ መሸጫ ዋጋ የተወሰነለት ዳንጎቴ ሲሚንቶ ከነበረበት 549 ብር ወደ 795 ብር እንዲያድግ ተደርጓል፡፡ ደርባ ሲሚንቶ 761 ብር፣ ሙገር ሲሚንቶ 755 ብር፣ ናሽናል ሲሚንቶ ደግሞ 765 ብር የፋብሪካ መሸጫ ዋጋ ተቆርጦላቸዋል፡፡ ፓዮኒር፣ ኢትዮ እና ኢስት ሲሚንቶዎች በአንጻሩ 753 ብር ሆነዋል፡፡
መስከረም ላይ የዋጋ ትመና ያልተደረገት ኢንቺኒ ሲሚንቶ 750 ብር ተወስኖለታል፡፡ ሀበሻ ሲሚንቶ 754 ብር፣ ኩዩ ሲሚንቶ 752 ብር እንዲሁም ካፒታል ሲሚንቶ 751 ብር የፋብሪካ ዋጋቸው እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በአራት ወራት ውስጥ በድጋሚ የተወሰነው የፋብሪካ በር መሸጫ ዋጋ ቀድሞ በአማካይ 590 ብር ሲሸጥ የነበረውን ሲሚንቶ በአማካይ 758 ብር እንዲደርስ አድርጎታል፡፡
አስራ እንዱ የሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች በአንጻሩ ይወሰንልን ብለው አቅርበው የነበረው ዋጋ በአማካይ 1014 ብር እንደነበር ንግድ ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ እንደ ሚኒስቴሩ መረጃ ከፍተኛ ዋጋ እንዲወሰንለት ያቀረበው ፓዮኒር ሲሚንቶ ነው፡፡ ፋብሪካው አንድ ኩንታል ሲሚንቶ የፋብሪካ በር መሸጫ ዋጋ 1783 ብር እንዲሆንለት ጠይቆ ነበር፡፡ ፓዮኒር አሁን የተወሰነለት ዋጋ ከጠየቀው በ1030 ብር ያነሰ ነው፡፡
ኢንቺኒ ሲሚንቶ ደግሞ 1298 ብር የፋብሪካ በር መሸጫ ዋጋ አስገብቶ 750 ብር እንዲሸጥ ተወስኖለታል፡፡ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ዛሬ ይፋ ያደረገው ይህ የፋብሪካ በር መሸጫ ዋጋ፤ ለስድስት ወራት የሚቆይ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)