በአማኑኤል ይልቃል
የዛሬ አራት ዓመት ገደማ የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን አደጋ የተከሰተው፤ የአውሮፕላን አምራቹ በገጠመው የመቆጣጠሪያ ስርዓት ላይ ባለ ችግር ምክንያት መሆኑን በምርመራ እንዳረጋገጠ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህን ያስታወቀው የአውሮፕላን አደጋውን የተመለከተ የተጠቃለለ ሪፖርት ዛሬ አርብ ታህሳስ 14፤ 2015 ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው።
የተጠቃለለ ሪፖርቱን ይፋ ያደረጉት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ፤ ላለፉት ዓመታት ሲደረግ የቆየው ምርመራ ያረጋገጣቸው አራት ዋና ዋና ውጤቶች መሆናቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። የምርመራው የመጀመሪያ ሁለት ውጤቶች፤ አውሮፕላኑን ሲያበሩ የነበሩት የበረራ ባለሙያዎችም ሆኑ አውሮፕላኑ ራሱ ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ህጋዊ እና የታደሰ የበረራ ፈቃድ የነበራቸው መሆኑን ያመላከተ ነው።
አውሮፕላኑ የነበረው የጭነት ክብደት እና ሚዛን በተፈቀደው ልክ መሆኑን ምርመራው ማረጋገጡን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ በሶስተኛ ውጤትነት አንስተዋል። የቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን “ከቁጥጥር ውጪ” እንዲሆን እና አደጋው እንዲፈጠር ምክንያት የሆነው፤ “ኤምካስ” (Maneuvering Characteristics Augmentation System – MCAS) በተሰኘው የአውሮፕላኑ የመቆጣጠሪያ ስርዓት ላይ በነበረ ችግር መሆኑን በምርመራው እንደተደረሰበትም አስታውቀዋል።

ባለፉት ዓመታት ውስጥ የተካሄደው የምርመራ ውጤት፤ ለአውሮፕላኑ መከስከስ ምክንያት የሆነው “ኤምካስ” የተባለው ስርዓት፤ የአውሮፕላኑን አፍንጫ በተከታታይ ለአራት ጊዜያት ወደታች እንዲሆን ሲያደርገው እንደነበር የኢትዮጵያ አውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ኮሎኔል አምድዬ አያሌው በዛሬው መግለጫ ላይ ተናግረዋል። የ“ኤምካስ” ስርዓት የመቆጣጠር ስራውን የሚሰራው በአንድ መረጃ ሰጪ ሴንሰር (angle of attack sensor) ላይ ተመስርቶ መሆኑ፤ ለተሳሳተ መረጃ እንዲጋለጥ እንዳደረገው የምርመራ ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል።
ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላንን ለማብረር ያዘጋጀው መለማመጃ (flight simulator)፤ “ኤምካስ” የተባለው ስርዓት በአደጋ ጊዜ በድንገት እንዲበራ ሲደረግ “ምን አይነት አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል” አለማካተቱን ኮሎኔል አምድዬ በተጨማሪ ችግርነት ጠቅሰዋል። የአውሮፕላን አምራች ኩባንያው፤ በአውሮፕላኑ ላይ የገጠመውን ስርዓት ዲዛይን ለውይይት አለማቅረቡ እና በ“ኤምካስ” ላይ ያለውን ችግር ለተጠቃሚዎች በጊዜ አለማሳወቁ ለዚህ አደጋ ገፊ ምክንያቶች እንደሆኑም አንስተዋል።
የ157 ሰዎች ህይወትን የቀጠፈው አደጋ የተከሰተው በበረራ ቁጥር ET 302 ከአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ ተነስቶ ወደ ኬንያ ናይሮቢ ጆሞ ኬንያታ አየር ማረፊያ ሲበር በነበረው ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን ላይ መሆኑ ይታወሳል። በረራ በጀመረ በስድስት ደቂቃዎች ጊዜ ውስጥ በቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ ጊምቢቾ ወረዳ የተከሰከሰው አውሮፕላን፤ የ35 አገራት ዜግነት ያላቸውን 149 መንገደኞችን እና ስምንት የበረራ ሰራተኞችን ይዞ ነበር።

አውሮፕላኑ የተከሰከሰው መጋቢት 1፤ 2011 ዓ.ም ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ከ44 ደቂቃ ላይ ነበር። ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን ከምድር የተላተመበት ኃይል፤ በግምት አስር ሜትር ጥልቀት ያለው ጉድጓድ እንዲፈጠር እንዳደረገ በዛሬው መግለጫ ተወስቷል። አውሮፕላኑ ከቦሌ አየር ማረፊያ በተነሳ በደቂቃዎች ልዩነት ውስጥ ከራዳር ውስጥ መጥፋቱን እና ከአየር ትራፊክ ጋር የነበረው ግንኙነት መቋረጡን ተከትሎ፤ ከኢትዮጵያ አየር ኃይል እና “አቢሲኒያ ፍላይት ሰርቪስ” ከተባለው የግል የበረራ ኩባንያ የተውጣጣ የፈልጎ ማዳን ቡድን ተሰማርቶ እንደነበር የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ በመግለጫቸው አስታውሰዋል።
አደጋው ከታወቀ በኋላ በሚኒስቴሩ ስር ያለው የምርመራ ቢሮ፤ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ምርመራ መጀመሩን ዳግማዊት ተናግረዋል። በምርመራው ላይ የፈረንሳይ የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ባለሙያዎች መሳተፋቸውንም አክለዋል። የምርመራ ቢሮው በ30 ቀናት ውስጥ የምርመራ ውጤቱን ማሳወቁን እና በዚህም ላይ ተመስርቶ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ይፋ ማድረጉን ጠቅሰዋል። ይሁንና ከዚያ በኋላ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከሰቱ፤ የመጨረሻ ሪፖርት ይፋ ለመድረግ የሚደረገው ምርመራ እንዲዘገይ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።
በዛሬው መግለጫ ላይ በጋዜጠኞች ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ፤ “የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ሂደቱ፤ ከቦይንግ ኩባንያ ጫና ነጻ ነበር ወይ?” የሚለው ይገኝበታል። ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ኮሎኔል አምድዬ፤ በእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ውስጥ “የጥቅም ግጭት የሚያጋጥም ጉዳይ መሆኑን” አንስተዋል። የጥቅም ግጭት የነበረ ቢሆንም፤ የአውሮፕላኑ አምራች ኩባንያ መረጃዎችን በማቅረብ ከኢትዮጵያ አውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ ጋር ሲሰራ መቆየቱን አስረድተዋል።

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ በበኩላቸው “ብዙ ጫናዎች ነበሩ። ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ አልፈናል” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ህግ መሰረት ምርመራውን የሚመራው አደጋው የተከሰተበት ሀገር መሆኑን ያነሱት ዳግማዊት፤ “የተጎጂዎችን እምባ ሊያብስ እና በዘላቂነት የአቪዬሽን ሴክተሩ ላይ ተመሳሳይ አደጋ እንዳይከሰት የሚያደርግ ነጻ፣ ግልጽ እና ዓለም አቀፍ አሰራሮችን የጠበቀ ምርመራ ለማድረግ ችለናል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ አውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን ባወጣበት ጊዜ፤ ቦይንግ ኩባንያ ይቅርታ እንደጠየቀና ማስተካከያ ማድረግ መጀመሩንም በአዎንታዊ ጎኑ አንስተዋል። ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላንን በድጋሚ ወደ በረራ ለማስገባት የወሰደውን ረጅም ጊዜ እና በኩባንያው የተወሰዱ እርምጃዎችን በማሳያነት የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ ይህ የሆነው ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ ባሳየችው ጠንካራ አቋም ምክንያት እንደሆነ በአጽንኦት ተናግረዋል።
“ ‘ምን አልባት ኢትዮጵያ እንደዚህ አይነት አቋም ባትይዝ እና እነዚያን ጫናዎች ተቋቁመን ማለፍ ባንችል፤ በዚህ ደረጃ እንደርስ ነበር ወይ? ለአቪዬሽን ዘርፍ አስተዋጽኦ ማድረግ ባለብን ልክ እንድናደርግ ያስችለን ነበር ወይ? ካልን፤ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚወድቅ ነው” ሲሉ ሚኒስትሯ አጠይቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ዘግየት ብሎ ተጨማሪ መረጃ ታክሏል]