በሃሚድ አወል
በአዲሱ የመከላከያ ሰራዊት የአዋጅ ረቂቅ ላይ፤ ለወታደራዊ ፍርድ ቤቶች የተሰጣቸው ስልጣን እና ደረጃቸውን አስመልክቶ በተካተቱ አንቀጾች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥያቄ ቀረበ። በአዋጅ ረቂቅ ላይ የሰፈረው፤ በ17 አመቱ የትጥቅ ትግል ወቅት ተሳትፎ ላደረጉ ታጋዮች የሚሰጠው “የትግል ተሳትፎ ሜዳይ” ሽልማትም ጥያቄ ተነስቶበታል።
ጥያቄዎቹ የተነሱት በፓርላማ የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ በመከላከያ ሰራዊት ረቂቅ አዋጅ ላይ ዛሬ አርብ ታህሳስ 14፤ 2015 ይፋዊ የህዝብ ውይይት ባካሄደበት ወቅት ነው። በውይይቱ የቀድሞ ኢትዮጵያ ሰራዊት አባላትን ጨምሮ የፓርላማ ተወካዮች ተገኝተው በአዋጅ ረቂቁ ላይ አስተያየት ሰጥተዋል።
ሶስት ሰዓት ገደማ በፈጀው በዛሬው ውይይት ከተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች መካከል፤ የወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ስልጣንን በተመለከተ በአዲሱ የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ የሰፈሩ አንቀጾችን በተመለከተ የተነሱት በርከት ብለው ታይተዋል።
ከወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ጋር የተያያዘ ጥያቄ ካነሱ ተሳታፊዎች ውስጥ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ አንዱ ናቸው። የዳኝነት ስራ መስራት የመከላከያ ሰራዊት “ተፈጥሯዊ ባህሪ አለመሆኑን” ያነሱት አቶ ክርስቲያን፤ “የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የመሳሰሉ ነገሮች፤ ተፈጥሯዊ ባህሪያቸው ለሆኑ ፍርድ ቤቶች ነው መሰጠት ያለበት” የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል።
በአዲሱ አዋጅ ረቂቁ መሰረት፤ በወንጀል ህጉ የተደነገጉት “የሰብዓዊ ወንጀሎች፣ የእጅ እልፊት እና የአካል ማጉደል ወንጀሎች” በቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን ስር የሚያርፉ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም የአዋጅ ረቂቁ፤ በመከላከያ ሰራዊት ስር ያሉ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች፤ “የዘር ማጥፋት፣ የጦርነት ማቆም ወይም የሰላም ስምምነት ውልን ማፍረስ እና በሰላማዊ ህዝብ ላይ የሚፈጸሙ የጦርነት ወንጀሎችን” እንዲመለከቱ የዳኝነት ስልጣን ይሰጣል።
አሁን በስራ ላይ ያለው አዋጅ፤ በወታደራዊ እና በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ስልጣን ስር የሚታዩ ክሶች በአንድ ተከሳሽ ላይ በሚቀርቡበት ጊዜ፤ ሁሉም ክሶች “ከባድ ቅጣት የሚስከትለውን ወንጀል የማየት ስልጣን ወዳለው ፍርድ ቤት” እንደሚቀርቡ ያትታል። አዲሱ የአዋጅ ረቂቁ ግን ይህን በማሻሻል፤ “አንድ ተከሳሽ ከቀረቡበት ክሶች መካከል ከፊሉ በወታደራዊ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን ስር፤ ከፊሉ ደግሞ በመደበኛ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን ስር የሚወድቅ ከሆነ፤ ሁሉም ክሶች በወታደራዊ ፍርድ ቤት ተጠቃለው ይታያሉ” ሲል ደንግጓል።
አቶ ክርስቲያን በሁለቱም ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ላይ የሚርፉ ጉዳዮች በመደበኛው ፍርድ ቤት ቢታዩ የተሻለ እንደሚሆን ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል። “መደበኛ ፍርድ ቤቶች የተሻለ [የህዝብ] መብትን የማስከበር ችሎታ አላቸው” ሲሉም አክለዋል። አዋጁ ለወታደራዊ ፍርድ ቤቶች የሰጠው ስልጣን “የህዝብ የመብት ጥያቄዎችን ጭምር ባልተገባ መንገድ እየፈረጁ በወታደራዊ ፍርድ ቤት የማየት አዝማሚያ ያዳብራል” ያሉት የፓርላማ አባሉ፤ ይህ አካሄድ የዜጎችን መብት የማጥበብ ሁኔታ እንዳይፈጠር “ብርቱ ስጋት” እንዳላቸው አስረድተዋል።
ከወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ስልጣን በተጨማሪ ባላቸው ደረጃ ላይም አስተያየት ቀርቧል። ሌተናል ኮሎኔል አቡሽ ገብሬ የተባሉ የውይይቱ ተሳታፊ፤ የወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ደረጃ ላይ “አንድ ተጨማሪ ፍርድ ቤት” እንዲቋቋም ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል። በአዋጅ ረቂቁ መሰረት፤ የወታደራዊ ፍርድ ቤቶች “ቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት” እና “ይግባኝ ሰሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት” የተሰኙ ሁለት ደረጃዎች አሏቸው።
ሌተናል ኮሎኔል አቡሽ፤ ይህ የፍርድ ቤቶች ደረጃ አንድ ባለጉዳይን በይግባኝ ሰሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ቢወሰንበት “በፍሬ ነገር ክርክር ላይ ይግባኝ የሚልበት አካል እንዳይኖረው አድርጓል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የህግ ስህተት ያለበት የወታደራዊ ፍርድ ቤት ውሳኔ የማየት ስልጣን፤ በአዲሱ የአዋጅ ረቂቅ የተሰጠው ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው። ሆኖም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ነገር ግን “የፍሬ ነገር ክርክርን ማየት እንደማይችል” በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፍሯል።
ከመከላከያ ሚኒስቴር ተወክለው በውይይቱ የተገኙ የመስሪያ ቤቱ አመራሮች እና ከፍተኛ መኮንኖች ከወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ጋር በተያያዘ ለተነሱት ጥያቄ እና አስተያየቶች ምላሽ ሰጥተዋል። በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የወታደራዊ ፍትህ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ብርጋዴር ጀነራል መሸሻ አረዳ፤ “ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንጀል የሚፈጸመው በታጠቀ ኃይል ነው። ይሔ ወታደራዊ መልክ አለው። [ወንጀሉ] የሚመለከተው የታጠቀውን ወታደር ነው። የታጠቀው ወታደር ደግሞ መዳኘት ያለበት በወታደሩ ነው” ሲሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የመከላከያ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ዳይሬክተር ኮሎኔል ደምሴ ካሳ በበኩላቸው፤ በወታደራዊ ፍርድ ቤት መታየት ሲገባቸው “አዋጁ ያላካተታቸው ጉዳዮች አሉ” ሲሉ ለውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል። ኮሎኔሉ በወንጀል ህጉ የተጠቀሱ አንዳንድ ወንጀሎች፤ “በወታደራዊ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ስር ሊወድቁ ይገባ ነበር” ባይ ናቸው።
ኮሎኔል ደምሴ “ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ሊመለከቷቸው ይገቡ ነበር” ያሏቸው ወንጀሎች፤ በወንጀል ህጉ “በመከላከያ ኃይል ላይ የሚደረጉ ወንጀሎች” ተብለው የተዘረዘሩ ናቸው። በአዋጅ ረቂቁ እንዲሁም ስራ ላይ ባለው የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ መሰረት፤ እነዚህ ወንጀሎች የወታደራዊ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ስር የሚያርፉ አይደሉም።
በዛሬው ውይይት በተደጋጋሚ የተነሳው ሌላኛው ጉዳይ፤ ለመከላከያ ሰራዊት አባላት የሚሰጡ ሜዳዮች እና የምስክር ወረቀቶችን የተመለከተ ነው። አቶ አበረ አዳሙ የተባሉ የተወካዮች ምክር ቤት አባል፤ ከደርግ መንግስት ጋር በነበረው የትጥቅ ትግል ተሳትፎ ለነበራቸው ታጋዮች ስለሚሰጠው ሽልማት የሚያትተው አንቀጽ “ከአዋጁ እንዲወጣ” ጠይቀዋል።
በአዲሱ የመከላከያ ሰራዊት የአዋጅ ረቂቅ ላይ ከደርግ መንግስት ጋር ከ1967 ዓ.ም እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ በትጥቅ ትግሉ ከአስር ዓመት ያላነሰ ተሳትፎ ያደረገ ታጋይ፤ የትግል ተሳትፎ ሜዳይ ባለዘንባባ እንደሚሰጠው ሰፍሯል። ታጋዩ ከአስር ዓመት በታች ተሳትፎ ያደረገ እንደሆነ ደግሞ ያለዘንባባ ሜዳይ እንደሚሰጠው በአዋጅ ረቂቁ ተቀምጧል።
አቶ አበረ “ከ67 እስከ 83 የነበረ ሰራዊት ይሸለም ብለን አዋጅ የምናወጣ ከሆነ፤ በግልጽ አነጋገር ኢትዮጵያን በግራም በቀኝም እያደማ ያለን ሰራዊት መሸለም ያህል ነው የሚሰማኝ” ሲሉ ድንጋጌው ላይ ያላቸውን ተቃውሞ አሰምተዋል። አቶ ኡርጌሳ ፊጣ የተባሉ የቀድሞ ሰራዊት አባል እንደሆኑ የተናገሩ ተሳታፊም በተመሳሳይ፤ ከ30 ዓመታት በፊት የደርግ መንግስትን ለመጣል በተደረገው የትጥቅ ትግል የተሳታፉ ታጋዮች ሜዳይ ማግኘታቸውን ተቃውመዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለም አንቀጹን ተቃውመው አስተያየት ሰጥተዋል። አቶ ክርስቲያን ድንጋጌውን “የትጥቅ ትግልን የሚያበረታታ አንቀጽ ነው” ሲሉ ነቅፈውታል። በመከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ጥናት እና ምርምር ኃላፊ የሆኑት ብርጋዴር ጀነራል ይታያል ገላው፤ “የትግል ተሳትፎ ሜዳይ በድብቅ ዝም ብሎ የመጣ አይደለም፤ ከየትም አምጥተን አልጨመርነውም” ሲሉ ከዚህ በፊትም ይሰራበት የነበረ አሰራር መሆኑን ተናግረዋል።
የትግል ተሳትፎ ሜዳይ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዋጅ ደረጃ ዕውቅና አግኝቶ በህግ የሰፈረው በ2006 ዓ.ም በወጣው የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ ላይ ነው። በውይይቱ ላይ የተገኙት የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታዋ ማርታ ሊዊጂ፤ ከትግል ተሳትፎ ሜዳይ ጋር በተያያዘ ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ “በአስተያየት ደረጃ መታየት አለበት ያላችሁት ትክክል ነው። እሱ በደንብ የሚታይ ይሆናል። በአዋጁም ማስተካከያ የሚደረግበት ይሆናል” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)