በአማኑኤል ይልቃል
ከሶስት ዓመት በፊት ባሳተሙት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ግለ ታሪክ መጽሐፍ ይበልጥ የሚታወቁት አቶ መሐመድ ሐሰን፤ ዋልታ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬትን እንዲመሩ ተሾሙ። አቶ መሐመድ ዋልታን በዋና ስራ አስፈጻሚነት እንዲመሩ የተሾሙት፤ የመገናኛ ብዙሃኑን ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ሲመሩ የቆዩት ዶ/ር ንጉሴ መሸሻን በመተካት ነው።
አዲሱን ሹመት በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ መሐመድ፤ ይፋዊ ርክክብ ባይደረግም በኃላፊነቱ ላይ መሾማቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ተሰናባቹ ዶ/ር ንጉሴ በበኩላቸው፤ ካለፈው ማክሰኞ ታህሳስ 11፣ 2015 ጀምሮ ከዋና ስራ አስፈጻሚነታቸው መነሳታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።
ሁለት የቴሌቪዥን እና አንድ የሬዲዮ ቻናል የሚያስተዳድረውን ድርጅት እንዲመሩ የተሾሙት አቶ መሐመድ፤ ውልደት እና ዕድገታቸው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን አርሲ ነገሌ ወረዳ ነው። አዲሱ ተሿሚ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ2001 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በውጭ ቋንቋዎች እና ስነ ጽሁፍ ትምህርት አግኝተዋል። ዋና ስራ አስፈጻሚው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን “በሊደርሺፕ” የትምህርት ዘርፍ ያገኙት ከሊድ ስታር ማኔጅመንት እና ሊደርሺፕ ኮሌጅ ነው።
አቶ መሐመድ ላለፉት 15 ዓመታት በተለያዩ ብዙሃን መገናኛዎች በተለያየ ደረጃ ተሳትፎ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በ2003 ዓ.ም በተቀላቀሉት ፋና ሬድዮ ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ ገደማ በፕሮግራም አዘጋጅነት ሰርተዋል። በህትመት የብዙሃን መገናኛ ዘርፍ ደግሞ፤ በመጀመሪያ በአዘጋጅነት በስተኋላም በዋና አዘጋጅነት በሰሩበት የ“አዲስ ፕሬስ” ጋዜጣ ላይ የነበረው ድርሻቸው ይጠቀሳል። ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ዓመታት ስታትም ቆይታ በተቋረጠችው “ኢትዮ ምህዳር” ጋዜጣ ላይም፤ በአምደኝነት እና በአዘጋጅነት አገልግለዋል።
አዲሱ የዋልታ ዋና ስራ አስፈጻሚ፤ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል በነበራቸው የአራት ዓመታት ቆይታ፤ በሁለት የተለያዩ ክፍሎች ዳይሬክተር ነበሩ። በዚሁ ተቋም፤ ከ2006 እስከ 2010 ዓ.ም የህዝብ ግንኙነት እንዲሁም የእውቀት አስተዳደርና ስርጭት ዳይሬክተር የነበሩት አቶ መሐመድ፤ ማዕከሉ በሚያዘጋጀው “ቴክ ሳይንስ” የቴሌዥቭን ፕሮግራም ላይም በዋና አዘጋጅነት ሲሳተፉ ቆይተዋል።
በማዕከሉ ይታተም በነበረው “ቴክ ሳይንስ” የተሰኘው ጆርናል ላይ ደግሞ በዋና አዘጋጅነትና አማካሪነት ሰርተዋል። የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የራሱን ቴሌቪዥን ጣቢያ ለማቋቋም ጥናት በሚያደርግበት ወቅት፤ ይህኑ ሂደት ሲመሩ የነበሩት አቶ መሐመድ ነበሩ። ለዚሁም ሲባል በእስራኤል ቴል አቪቭ ከተማ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ጋዜጠኝነት ስልጠና ወስደዋል።
አቶ መሐመድ በብዙሃን መገናኛ ላይ ከነበራቸው የአዘጋጅነት ሚና ባሻገር፤ የተለያዩ መጽሐፍትን የአርትኦት ስራ ማከናወናቸውን በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ። ራሳቸው የጻፏቸው ሁለት መጽሐፍትም፤ በታተሙባቸው ወቅቶች “አነጋጋሪ” የመሆን ዕድል አግኘተዋል። በ2007 ዓ.ም የታተመው የመጀመሪያው መጽሐፋቸው፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ የሚያቀርቧቸው ሀሳቦችን በ236 ገጽ የሰነደ ነበር።
“የዳኛቸው ሐሳቦች” የተሰኘው ይህ መጽሐፋቸው ግን፤ ከዶ/ር ዳኛቸው በቀረበበት ቅሬታ ውዝግብ ቀስቅሶ ነበር። ዶ/ር ዳኛቸው “ለሰባት አመታት በልዩ ልዩ መገናኛ ብዙሃን እና መድረኮች ያቀረብኳቸውን መጣጥፎችና ንግግሮች ሰብስቦ የእኔን ይሁንታ ሳያገኝ አሳትሟል” ሲሉ ደራሲውን መወንጀላቸው ይታወሳል። አቶ መሐመድ በአንጻሩ የመጽሀፉን አብዛኛው ገጾች የያዙት የ“ግል ትንታኔዎች እና ማብራሪያዎች” መሆኑን በመግለጽ ውንጀላውን እንደማይቀበሉ በወቅቱ አስታወቀው ነበር።
አቶ መሐመድ ይበልጥ ከአንባቢያን ጋር ያስተዋወቃቸው፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ግለ ታሪክ የዳሰሰው “ሰውዬው” የተሰኘው መጽሐፍ ነው። በመጋቢት 2011 ዓ.ም የታተመው ይህ ባለ 499 ገፅ መፅሀፍ፤ አቶ መሐመድ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ማዕከል ውስጥ በሚሰሩበት ጊዜ በተለያዩ ጊዜያት የሰበሰቧቸው መረጃዎችን፣ ዕይታዎች እና ቃለ መጠይቆች መነሻ በማድረግ ያዘጋጁት መጽሐፍ ነው።
አብዛኛው የመጽሐፉ ክፍል የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በነበሩባቸው ጊዜያት ላይ ያጠነጠነ ነው። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የልጅነት ጊዜ የሚነሳው “ሰውዬው” መጽሐፍ፤ በተለይም ስለ አብይ ግለ ስብዕና በሰፊው ያብራራል። የአብይ “ፍልስፍናዎች እና የስኬታማነት ሚስጥሮች”፣ ከሰራተኞቻቸው ጋር የነበራቸው ግንኙት፣ በሰሩባቸው ተቋማት ውስጥ ያስጀመሯቸው አዳዲስ አሰራሮች በመጽሐፉ ላይ በዝርዝር ሰፍረዋል።
አቶ መሐመድ ከ2010 ዓ.ም በኋላ በግል ስራዎች ላይ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል። እስከ አዲሱ ሹመታቸው ድረስም፤ በባለቤትነት በሚያስተዳድሩት “ሃሳብ ሜዳ” በተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙሃን አዘጋጅ ሆነው እየሰሩ ነበሩ። ከዚህ በተጓዳኝ፤ “ሞ ፕሮዳክሽን” በተሰኘው ድርጅታቸው ዘጋቢ ፊልሞችን ሲያዘጋጁ ነበር።
በቀጣዩ ሳምንት ለአዲሱ ተሿሚ ይፋዊ የስራ ርክክብ ያደርጋሉ ተብለው የሚጠበቁት ዶ/ር ንጉሴ፤ በዋልታ በነበራቸው የአራት ዓመታት ቆይታ የተቋሙን ተደራሽነት ያሰፉ ስራዎችን መስራታቸውን አብረዋቸው የሰሩ ይናገራሉ። በዋና ስራ አስፈጻሚነት የኃላፊነታቸው ዘመን፤ ቀድሞ በ105.3 ሜጋ ኸርዝ ላይ ሲሰራጭ የነበረው “አፍሮ ኤፍኤም” የተሰኘው ሬድዮ ጣቢያ “ዋልታ ኤፍ ኤም” ተብሎ በኮርፖሬቱ ስር እንዲሆን አድርገዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ካለፈው ሰኔ 2014 ዓ.ም ጀምሮ በሙከራ ስርጭት ላይ ያለው፤ “አፍሮ ኒውስ” የቴሌቪዥን ጣቢያ በዋልታ ስር እንዲቋቋም ማድረጋቸውን የተቋሙ ሰራተኞች ይገልጻሉ። ይህ ቴሌቪዥን ጣቢያ ይዘቶቹን በውጭ ቋንቋዎች የሚያስተላልፍ ነው። የቴሌቪዥን ጣቢያው በየዕለቱ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ለ16 ሰዓታት፣ በአረብኛ እና ስዋሂሊ ቋንቋዎች ደግሞ ለስምንት ሰዓታት ዝግጅቶቹን ያሰራጫል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)