በሃሚድ አወል
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ ካማሺ ዞን፤ ካማሺ ከተማ ለሶስት ወራት ገደማ ተቋርጦ የነበረው የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት፤ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ እንደገና ስራ ጀመረ። ላለፉት ሶስት ወራት ለተሽከርካሪዎች ዝግ ሆኖ የቆየው እና ካማሺ ከተማን በኦሮሚያ ክልል ከምትገኘው ነጆ ከተማ ጋር በሚያገናኘው መንገድም ተሽከርካሪዎች መመላለስ መጀመራቸውን የከተማይቱ ነዋሪዎች እና የአካባቢው ባለስልጣን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በካሚሺ ከተማ የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ለወራት የተቋረጠው፤ በአጎራባች የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች “ኦነግ ሸኔ” በሚያደርሰው ጥቃት ሳቢያ በመሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት በመድረሱ ምክንያት እንደሆነ የካማሺ ከተማ ከንቲባ አቶ አብደታ ደሬሳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። “ነቀምት አካባቢ ባለፈው በነበረው የተኩስ ልውውጥ እዚያ አካባቢ መሰረተ ልማት ላይ ጉዳት ደርሶ ነበር፤ ያንን ተከትሎ ነው የእኛ የተቋረጠው” ሲሉ በሚያስተዳድሩት ከተማ የስልክ ኔትወርክ የተቋረጠበትን ምክንያት አስረድተዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ መሳይ ውብሸት፤ በካማሺ የቴሌኮሚዩኔኬሽን ኔትወርክ ተቋርጦ የነበረው “በተለያየ ምክንያት” እክል በገጠማቸው የፋይበር መስመሮች ላይ ጥገና ማድረግ ባለመቻሉ መሆኑን ጠቁመዋል። መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢው ጥገናውን ማከናወን ያልቻለው “በጸጥታ ችግር ምክንያት” መሆኑንም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በተቋሙ ቺፍ ቴክኖሎጂ ኦፊሰር የሆኑት አቶ ተሾመ ደምሴ፤ “ምዕራብ አካባቢ ያለው የፋይበር አማራጭ መስመሮቻችን በሙሉ ተቋርጠው [ነበር]። በጸጥታ ምክንያት ሄደን መጠገን ባለመቻላችን መቆራረጥ አጋጥሞ ነበር” ሲሉ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል። የካማሺው አገልግሎት መቋረጥ ግን ከዚህ ጋር መገናኘቱን እርግጠኛ እንዳልሆኑ አክለዋል።
በካማሺ ከተማ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት መመለሱን ተከትሎ፤ በከተማይቱ ላለፉት ሶስት ወራት ስራ አቋርጠው የነበሩ ባንኮች ስራ እንደገና መጀመራቸውን አቶ ሺሮሙ አብዲ እና አቶ ደበላ በየነ የተባሉ ሁለት የከተማይቱ ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ካማሺ ከተማን ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ነጆ ከተማ ጋር የሚያገኛኘውም መንገድም ካለፈው አርብ ጀምሮ ተሽከርካሪዎች ማስተናገድ መጀመሩን አመልክተዋል።
አውራ ጎዳናው የካማሺ ከተማን ከክልሉ ዋና ከተማ አሶሳ ጋር የሚያገኛኘው ዋነኛ መንገድ ነው። ከካማሺ ዞን ወደ አሶሳ የሚጓዙ የአካባቢው ነዋሪዎች የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞንን ማቋረጥ ይጠበቅባቸዋል። ተሽከርካሪዎች ላለፉት ለሶስት ወራት ገደማ ያህል መንገዱን መጠቀም ያቁሙት “ኦነግ ሸኔ በሚያደርሰው አደጋ” እንደነበር አቶ አብደታ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ካለፉት ጥቂት ሳምንታት ወዲህ፤ በካማሺ ዞን ውስጥ የሚደረጉ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴዎችም “መሻሻል” እንደታየባቸው ከንቲባው አስታውቀዋል። በከተማይቱ ሰላም እና ጸጥታ ጽህፈት ቤት የሚሰሩት አቶ ደበላ በየነም፤ በዞኑ ያለው የጸጥታ ሁኔታ መሻሻል ማሳየቱን በመጥቀስ የከንቲባውን ሃሳብ አጠናክረዋል። የካማሺ ከተማ ከንቲባ “እስከ ቀበሌ ድረስ እየገባን ስራዎችን እየሰራን ነው። ከዚህ በፊት አይቻልም ነበር። ውስጥ ለውስጥ ያለ እጀባ ነው የምንቀሳቀሰው” ሲሉ በከተማይቱ ለውጥ አሳይቷል ያሉትን የጸጥታ ሁኔታ በምሳሌ አስደግፈዋል።
የካማሺ ዞን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተደጋጋሚ የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች ከሚከሰቱባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው። በዞኑ ለሚከሰቱ ጥቃቶች የክልሉ መንግስት የጉሙዝ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ተጠያቂ ሲያደርግ ቆይቷል። ጉህዴን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ጋር ባለፈው ጥቅምት ወር በአሶሳ ከተማ የሰላም ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል። የክልሉ መንግስት ከአንድ ወር በኋላ በተመሳሳይ የቤኒሻንጉል ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (ቤህነን) ጋር ሌላ ስምምነት ተፈራርሟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)