የሰላም ሚኒስቴር “ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት” የቀረጻቸውን ሶስት ፕሮጀክቶች፤ በ13 ቢሊዮን ብር ወጪ ሊተገብር ነው

በአማኑኤል ይልቃል

የሰላም ሚኒስቴር “የዘላቂ ሰላም ግንባታ” አካል የሆኑ እና 13 ቢሊዮን ብር ገደማ ወጪ የሚጠይቁ ሶስት ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ማድረግ ሊጀምር ነው። የአምስት ዓመት የትግበራ ጊዜ ካላቸው ከእነዚህ ፕሮጀክቶች አንዱ፤ ቀደም ሲል በተለያዩ ግጭቶች የሚታወቁ አካባቢዎችን በናሙና በመምረጥ ግጭቶቹን “በዘላቂነት” የመፍታት እቅድ የያዘ ነው። 

ሚኒስቴሩ በዚህ ዓመት ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገባቸው ያሉት ሶስት ፕሮጀክቶች፤ ከተያዘው 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአስር ዓመት ውስጥ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በመስሪያ ቤቱ የተቀረጸ ሰፊ ማዕቀፍ ያለው ፕሮግራም አካል ናቸው። “የዘላቂ እና ሁለንተናዊ ሰላም ግንባታ” የተሰኘ ስያሜ ያለው ይህ ፕሮግራም፤ በውስጡ 12 ፕሮጀክቶችን ይዟል።

በዘንድሮው ዓመት ከሚተገበሩት ፕሮጀክቶች ውስጥ አንደኛው፤ “የተመረጡ የግጭት አካባቢዎችን ወደ ሰላም እና ልማት የማሸጋገር” ውጥን ያለው መሆኑን በሰላም ሚኒስቴር አማካሪ እና የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ ሻንቆ ደለለኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “ይህ ፕሮጀክት ዘላቂ የሆነ ሰላም ለማምጣት ማነቆ የሆኑ ቦታዎችን በየጊዜው እየለየ፤ intervene የሚያደርግ ነው” ሲሉም አክለዋል።  

በዚህ መልኩ የሚለዩ አካባቢዎች ላይ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተመረጡ ያላቸው ዘዴዎችን እንደሚጠቀም አቶ ሻንቆ ገልጸዋል። ከእነዚህ ዘዴዎች መካከል ሽምግልና እና እርቅ፣ በማህበረሰቦች መካከል የሚደረግ ምክክር እንዲሁም ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች እንደሚገኙበት አስረድተዋል። ይህን ፕሮጀክት “በሙከራ ደረጃ” ወደ ትግበራ ለማስገባት፤ በምስራቅ እና በምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ ሁለት አካባቢዎች መመረጣቸውንም ጠቁመዋል። 

ከምስራቅ ኢትዮጵያ የተመረጡት አካባቢዎች፤ በአፋር እና በሶማሌ ክልሎች በሚገኙ ማህበረሰቦች መካከል ተደጋጋሚ ግጭት የሚነሳባቸው የድንበር ስፍራዎች ናቸው። ለፕሮጀክቱ ትግበራ የተመረጠው ሁለተኛው አካባቢ በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘው የመተከል ዞን ነው። ከአማራ ክልል ጋር አዋሳኝ የሆነው ይህ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዞን ተደጋጋሚ ግጭቶች ሲያስተናግድ የቆየ ነው። 

በአስር ዓመቱ የሰላም ሚኒስቴር ፕሮግራም ውስጥ ከተካተቱ እና በዚህ ዓመት ከሚጀመሩት ፕሮጀክቶች ውስጥ ሁለተኛው፤ ግጭቶች ሳይከሰቱ መከላከል እና የቅድመ-ማስጠንቀቂያ ስርዓት መዘርጋትን የያዘ ነው። በዚህ ፕሮጀክት ሊዘረጋ የታቀደው ስርዓት፤ “የቅድመ-ማስጠንቀቂያ መረጃዎች ከታች እስከ ላይ የሚሰባሰቡበት፣ የሚደራጁበት እና የሚተነተኑበት” እንደሚሆን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የፕሮግራሙ ሰነድ ያስረዳል።

የቅድመ-ማስጠንቀቂያ ስርዓቱ “የተዋረድ እና የጎንዮች የመረጃ ቅብብሎሽ” በማድረግ ግጭቶች ሳይከሰቱ “የመከላከል እና የማክሰም” አቅምን የማሳደግ ግብ እንዳለው በሰነዱ ላይ ሰፍሯል። በዚህ ፕሮጀክት አማካኝነት፤ በየክልሉ ከሚገኙ አካባቢዎች የግጭት ጠቋሚ የሆኑ መረጃዎች በየጊዜ የሚሰበሰቡ ይሆናል። በእነዚህ መረጃዎች ላይ ትንተና የሚሰሩ “የሁኔታ ትንተና ማዕከላት” (situation rooms) በተለያዩ አካባቢዎች ለማቋቋም መታሰቡን አቶ ሻንቆ ተናግረዋል።

በዚህ ፕሮጀክት ሊተገበሩ ከተያዙ እቅዶች ውስጥ፤ በተለያዩ ከተሞች የመንገድ ላይ ካሜራዎችን መግጠም አንዱ መሆኑንም ተናግረዋል። የቅድመ-ማስጠንቀቂያ ስርዓት ዝርጋታን የሚያስፈጸመውን ፕሮጀክት ለመተግበር በአጠቃላይ ሁለት ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ፤ የሰላም ሚኒስቴር የ2015 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸሙን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ባቀረበበት ወቅት አስታውቆ ነበር።

በ2015 እንደሚተገበር የሚጠበቀው ሶስተኛው ፕሮጀክት፤ ባለፉት ዓመታት በሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ሲመራ የነበረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ማስፋት እና ተከታታይነቱን ማረጋገጥ ነው። ፕሮጀክቱ “ብሔራዊ የሰላም እና ህብረ-ብሄራዊ አንድነት ግንባታ፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። 

መንግስት በሚበጅትለት ገንዘብ ሲተገበር በቆየው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፤ በዓመት ውስጥ 10 ሺህ ገደማ የሚሆኑ በጎ ፈቃደኞች ሲሳተፉ መቆየታቸውን አቶ ሻንቆ  አመልክተዋል። በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ብቻ ተገድቦ የቆየውን ይህን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማስፋት፤ በአዲሱ አሰራር “ሁሉንም የሚያካትት ብሔራዊ ፕሮጀክት” ለማድረግ መታቀዱን አስረድተዋል።

በ53 ገጽ የተዘጋጀው የሰላም ሚኒስቴር “የዘላቂ ሰላም ግንባታ” እቅድ፤ በአስር ዓመት ውስጥ የሚተገበሩ ሌሎች ፕሮጀክቶችንም ዘርዝሯል። እነዚህን ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ለማድረግ፤ ተጠሪነቱ ለሰላም ሚኒስቴር የሆነ “የፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት”  እንደሚቋቋም በሰነዱ ላይ ተመላክቷል። ፕሮግራሙን በበላይነት የሚመራው፤ በሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱአለም የሚመራ እና ባለድርሻ አካላት አባል በሚሆኑበት “አብይ ኮሚቴ” እንደሚሆን በሰነዱ ሰፍሯል።

በዚህ ፕሮግራም ውስጥ የተያዙትን ሌሎች ፕሮጀክቶች የመቅረጽ ስራ በአሁኑ ወቅት በመከናወን ላይ መሆኑን ፕሮግራም አስተባባሪው አቶ ሻንቆ ገልጸዋል። የፕሮግራም ሰነዶቻቸው ተጠናቀቅው ወደ ትግበራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ላሉት ሶስት ፕሮጀክቶች ብቻ 13 ቢሊዮን ብር ገደማ በጀት እንደሚያስፈልግ መገመቱን የፕሮግራም አስተባባሪው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የሰላም ሚኒስቴር ለሶስቱ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት፤ ከሁለት ሳምንት በፊት ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ጋር ምክክር ማድረጉን አቶ ሻንቆ አስረድተዋል። ስለ ፕሮጀክቶቹ ገለጻ የተደረገላቸው እና የፕሮግራም ሰነዱ የተሰጣቸው  ለጋሽ ድርጅቶች፤ “የተወሰነ ጊዜ ስጡን” ማለታቸውንም ጠቅሰዋል። ድርጅቶቹ ከፕሮጀክቶቹ መርጠው አሊያም በአንድ ፕሮጀክት ውስጥ ያለን አንድ ክፍል ለይተው ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚችሉም ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)