የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመቐለ በረራ የትኬት ሽያጭ ጀመረ

በአማኑኤል ይልቃል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከነገ ጀምሮ በቀን አንድ ጊዜ ወደ ትግራይ ክልል መቐለ ከተማ መደበኛ በረራ እንደሚጀምር አስታወቀ። አየር መንገዱ ወደ መቐለ ለሚደረገው በረራ ዛሬ ማክሰኞ ታህሳስ 18፤ 2015 የበረራ ትኬት መሸጥ መጀመሩን የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ከአንድ ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ ተቋርጦ የነበረው መደበኛ በረራ እንደሚጀመር የተገለጸው፤ ዋና ስራ አስፈጻሚውን አቶ መስፍንን ያካተተ እና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራ የፌደራል መንግስት ልዑክ  ወደ መቐለ ከተማ በተጓዘ በማግስቱ ነው። ከትላንቱ ውይይት በኋላ በተሰጠው መግለጫ፤ ባንክ እና ቴሌኮሚዩኒኬሽንን ጨምሮ መሰረታዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ እንዲጀመሩ በትግራይ ባለስልጣናት ጥያቄ ቀርቦ ነበር። 

ከትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጋር በመሆን መግለጫ የሰጡት አፈ ጉባኤ ታገሰ፤ የባንክ እና የቴሌኮም አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ለማስጀመር ስራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸው ነበር። የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትን በተመለከተ ደግሞ “ነገ ሁሉን ነገር ለማስጀመር፣ [የኢትዮጵያ አየር መንገድ] የትኬት ቢሮአቸውን፤ አጠቃላይ መሬት ላይ ያለውን ሲስተም ቼክ እያደረጉ ነው” ብለው ነበር።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቐለ የሚያደርገውን በረራ የሚያስጀምረው፤ በዋና መስሪያ ቤት የሚገኙ ሰራተኞቹን በጊዜያዊነት በከተማዋ በማሰማራት እንደሆነ አቶ መስፍን ገልጸዋል። በመቐለ አሉላ አባ ነጋ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ የሚሰሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞችን የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አክለዋል። “ለጊዜው ከዚህ ሰዎች እየሄዱ ይሰራሉ፤ ይመለሳሉ። እዚያም ጥቂት ሰዎች አግኝተናል። ጥቂቶቹ ሰዎች እዚያ ያሉትም አብረው ይሰራሉ” ሲሉ ዋና ስራ አስፈጻሚው ሂደቱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።

አየር መንገዱ የመቐለ በረራን በቀን አንድ ጊዜ በማድረግ የሚያስጀምረው፤ ወደ ከተማዋ ለመጓዝ ፍላጎት ያለው መንገደኛ ቁጥር ባለመታወቁ መሆኑን አቶ መስፍን ተናግረዋል። እርሳቸው ይህን ቢሉም፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከነገ ጀምሮ ወደ መቐለ በረራ እንደሚጀምር ባስታወቀ በአንድ ሰዓት ገደማ ውስጥ፤ ለረቡዕ ጉዞ የትኬት ሽያጭ መጠናቀቁን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከአየር መንገዱ የደንበኞች ማስተናገጃ ማዕከል አረጋግጣለች። ለነገው በረራ የትኬት ሽያጭ የተጀመረው ዛሬ ማክሰኞ ረፋድ ሶስት ሰዓት ገደማ እንደሆነ ከማዕከሉ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በትግራይ ክልል ከመቐለ በተጨማሪ በሽሬ እና አክሱም ከተሞች የመንገደኞች በረራ ይሰጥ እንደነበር ይታወሳል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ “በጥቂት ሳምንታት ውስጥ” ወደ ሽሬ ከተማ የመንገደኞች በረራ እንደሚጀምር አቶ መስፍን ጠቁመዋል። አየር መንገዱ ወደ ሽሬ ከተማ ቡድን በመላክ፤ በዚያ ያለውን አየር ማረፊያ ያለበትን ሁኔታ መገምገሙንም አስረድተዋል።

በሽሬ አየር ማረፊያ “የጎደሉ እቃዎች” የማሟላት ስራ ቢከናወንም፤ የአየር ማረፊያው ሰራተኞችን የማሰባሰብ ስራ የሚቀር በመሆኑ ይህንን በማጠናቀቅ “በጥቂት ሳምንታት” ጊዜ ውስጥ በረራ እንደሚጀመር ዋና ስራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል። የአክሱም አየር ማረፊያን ወደ ስራ ማስገባትን በተመለከተ ግን “ቁርጥ ያለ ቀን” መግለጽ እንደሚያስቸግር አቶ መስፍን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

“አክሱም [አየር ማረፊያን] አላየነውም። በወሬ የምንሰማው አውሮፕላን መንደንደሪያው ጉዳት አለው ስለተባለ፤ በደንብ አይተን በደንብ ተጠግኖ ነው [በረራ] የምንጀምረው” ሲሉ ዋና ስራ አስፈጻሚው አብራርተዋል። በአየር ማረፊያው ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን የሚያጠና ቡድን ወደ አክሱም ከተማ የሚላክበት ጊዜ ገና አለመወሰኑንም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)