በአማኑኤል ይልቃል
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ በስሩ በሚገኙ የመንግስት ሆስፒታሎች ከስራ ሰዓት ውጪ የሚሰጠው የግል ህክምና ዋጋ ላይ ጭማሪ ሊያደርግ ነው፡፡ ቢሮው የዋጋ ጭማሪውን የሚያደርገው የህክምና ቁሳቁሶች ዋጋ በመጨመሩ እና የህክምና ባለሙያዎች በሆስፒታሎቹ ውስጥ እንዲቆዩ እንደማበረታቻነት የሚጠቀምበትን “የግል ህክምና አገልግሎት” ለማስቀጠል መሆኑን አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ስድስት ሆስፒታሎችን የሚያስተዳድረው ጤና ቢሮው፤ ከስራ ሰዓት ውጪ በሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶች ላይ ያደረገው ጭማሪ በአማካይ አራት እጥፍ ነው፡፡ አዲሱ የዋጋ ተመን ተግባራዊ የሚሆነው የከተማ አስተዳደሩ የሚያስተዳድራቸው ራስ ደስታ ዳምጠው፣ የካቲት 12፣ ዳግማዊ ምኒሊክ፣ ዘውዲቱ፣ጋንዲ መታሰቢያእና ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታሎች በሚሰጧቸው የግል ህክምናዎች ላይ ነው፡፡
በአዲሱ የዋጋ ተመን መሰረት በስፔሻሊስት ሀኪሞች ለሚደረግ ህክምና የካርድ ዋጋ 200 ብር ሲሆን በጠቅላላ ሀኪም ለሚደረግ ህክምና ካርድ ለማውጣት 150 ብር ይከፈላል፡፡ ከ1600 በላይ ለሚሆኑ የህክምና አገልግሎቶች ዋጋ የሚዘረዝረው አዲሱ ተመን ዝቅተኛ ዋጋ ያስቀመጠው ለስፌት ማስለቀቅ (Stitch removal) ሲሆን ይህ የህክምና አገልግሎት 50 ብር ተተምኖለታል፡፡ በዚህ የዋጋ ተመን ላይ ከፍተኛ የሆነው 25,000 ብር ዋጋ የቆረጠለት በጎረሮ አከባቢ የሚደረግ ቀዶ ህክምና (laryngectomy) ነው፡፡

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የህክምና አገልግሎት ምክትል ኃላፊ ዶ/ር ሙሉጌታ እንዳለ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደገለጹት የዋጋ ጭማሪ ከተደረገባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የህክምና ባለሙያዎች የቀድሞው የዋጋ ተመን ዝቅተኛ መሆኑን በመጥቀስ በግል ህክምና አገልግሎት ለመስጠት ፍላጎት ማጣታቸው ነው፡፡ በመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ የግል ህክምና መሰጠት የተጀመረው ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን በዋጋ ተመኑ ላይ ደግሞ ለመጨረሻ ማሻሻያ የተደረገው በ2007 ዓ.ም ነው፡፡ ከኮቪድ-19 መከሰት በኋላ በብዙዎቹ ሆስፒታሎች የግል ህክምና አገልግሎት ተቋርጦ ቆይቷል፡፡ ዶ/ር ሙሉጌታ፣ “አንዳንድ ተቋማት ላይ ዋጋው አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት፤ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎቱን ለማቆም የተገደዱበት ሁኔታ አለ” ብለዋል፡፡
ይህ አይነቱ ቅሬታ በተለይ ከስፔሻሊስት ሀኪሞች እንደሚመጣ እና በዚህ የተነሳ ከመደበኛ ስራ ውጪ ያለ ጊዜያቸውን “ከቤተሰባቸው ጋር” ወይም በሌሎች የግል የጤና ተቋማት ውስጥ በመስራት ማሳለፍ እንደሚመርጡ ተናግረዋል፡፡ በመንግስት ሆስፒታሎች የግል ህክምና አገልግሎት የሚሰጠው ከጧቱ 2፡30 እስከ 11፡30 ካለው የመደበኛው የስራ ሰዓት ውጪ እንዲሁም ቅዳሜ እና እሁድ ነው፡፡
በመንግስት ሆስፒታሎች የሚሰጠው ይህ አገልግሎት ከመደበኛው አገልግሎት ውጪ ያለ “ሁለተኛ አማራጭ” መሆኑን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዮሐንስ ጫላ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል፡፡ በህክምና ባለሙያዎቹ “ትርፍ ሰዓት” የሚሰጠው ይህ የህክምና አገልግሎት ከመደበኛው አገልግሎት የተለየ የክፍያ ተመን እንዳለውም አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ይህንኑ የህክምና አገልግሎት አስመልክቶ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ታህሳስ 11፣ 2015 ያወጣው መመሪያ “ከመደበኛ የህክምና አገልግሎት ጎን ለጎን ባለሙያዎች ከስራ ሰዓት ውጪና በበዓላት ቀን በተመጣጣኝ ክፍያ” አገልግሎት የሚሰጡበት አሰራር እንደሆነ አስፍሯል፡፡ መመሪያው እንደሚያስረዳው ይህ የህክምና አገልግሎት የተዘረጋው በሶስት ምክንያቶች ነው፡፡
በመመሪያው ላይ ከተጠቀሱት ዓላማዎች ውስጥ የመክፈል አቅም ላላቸው ህክምና ፈላጊዎች አማራጭ ስርዓት መዘርጋት እና ከግል ህክምና አገልግሎት በሚገኘው ተጨማሪ ገቢ የመደበኛ አገልግሎቶችን ጥራት ማሻሻል ይገኙበታል፡፡ መመሪያው በቀዳሚነት ያስቀመጠው ዓላማ ግን በከተማ አስተዳደሩ ስር ባሉ የመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ የሚሰሩ የህክምና ባለሙያዎች “ተጨማሪ ገቢ እያገኙ ጤና ተቋሙ ውስጥ እንዲቆዩ ማበረታታት” የሚለውን ነው፡፡ ጤና ቢሮው የህክምና ባለሙያዎች በትርፍ ጊዜያቸው በሚሰጡት የግል አገልግሎት “የስራ ተነሳሽነታቸውን ማሳደግና የሙያተኞችን ፍልሰት ለመቀነስ” ማቀዱ በመመሪያው ተጠቅሷል፡፡
የጤና ቢሮው የዋጋ ማሻሻያውን ያደረገበት ሌላኛው ምክንያት የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ የህክምና ግብአቶችና ቁሳቁሶች ዋጋ መጨመሩ ነው፡፡ለግል ህክምና አገልግሎት ዋጋ በተተመነበት 2007 ዓ.ም እና አሁን ያለውን የውጭ ምንዛሬ ተመን ልዩነት የሚጠቅሱት የጤና ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ዮሐንስ፣“ለህክምናው የሚወጡትን ግብአቶች ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ ነው” ብለዋል፡፡

የአዲሱ የግል ህክምና አገልግሎት ዋጋ ተመን ከዚህ ቀደም ለግል ህክምና ዋጋ ያልወጣላቸውን አገልግሎቶች ያካተተ መሆኑን በቢሮው የአጋርነት እና ትብብር ዳይሬክተር አቶ በሽር መሀመድ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው የዋጋ ዝርዝር የያዘው 285 የህክምና አገልግሎቶችን ሲሆን አዲሱ በአንጻሩ ለ1632 የህክምና አገልግሎቶች ዋጋ ተምኖ ማስቀመጡን አስረድተዋል፡፡ ሆስፒታሎች ከዚህ ቀደም ዋጋ ላልተወሰነላቸው አገልግሎቶች የሚያስከፍሉት ዋጋ የተለያዩ መሆኑን አክለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የዋጋ ጭማሪ ያደረገው ግን በግል ህክምና አገልግሎቶች ላይ ብቻ አይደለም፡፡ የከተማዋ የጤና ተቋማት በመደበኛነት የሚሰጧቸው የህክምና አገልግሎቶች ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ ጭማሪ ተደርጎባቸዋል፡፡
በመደበኛ የህክምና አገልግሎቶች ላይ የተደረገው አማካይ የዋጋ ጭማሪ ሁለት እጥፍ ሲሆን፤ 10 ብር የነበረው ካርድ ማውጫ ዋጋ 30 ብር ሆኗል፡፡ በአዲሱ የመደበኛ ህክምና የዋጋ ተመን ላይ ትልቁ ክፍያ የተተመነው ልብ አካባቢ ያለን እጢ ለማውጣት የሚደረግ ቀዶ ጥገና (pericardiectomy) ሲሆን 2,735 ብር ዋጋ ተቆርጦለታል፡፡
የመደበኛው ህክምና ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ ተግባራዊ መሆን የጀመረ ሲሆን በግል የህክምና አገልግሎት ላይ የሚደረገው ጭማሪ ተግባራዊ የሚሆነው ሆስፒታሎቹ በአዲሱ መመሪያ መሰረት አገልግሎቱን ሲያደራጁ መሆኑን አቶ በሽር ገልጸዋል፡፡ አዲሱ መመሪያ ከዚህ ቀደም በየሆስፒታሎቹ “ተመሳሳይ ባልሆነ መልኩ” ሲሰጥ ለቆየው ይህ አግልግሎት ወጥ ስርዓት የሚዘረጋ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በግል የህክምና አገልግሎት ላይ ወጥ አሰራር የለባቸውም ከሚባሉት እና ከጤና ባለሙያዎች ዘንድ ቅሬታ ከሚነሳባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ከአገልግሎቱ የሚገኘው ገቢ ክፍፍል የሚደረግበት አሰራር መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ በአዲሱ መመሪያ መሰረት ከግል ህክምና አገልግሎት ገቢ ላይ ትርፍ የሚታሰበው የአላቂ የህክምና መገልገያዎች ወጪ ከተቀነሰ በኋላ ነው፡፡
ከተጣራው ትርፍ ላይ አስር በመቶው ለሆስፒታሉ ገቢ የሚደረግ ሲሆን 15 በመቶው በአገልግሎቱ ላይ ለተሳተፉ የአስተዳደር ሰራተኞች ተመድቧል፡፡ ቀሪው 75 በመቶ ገቢ ለህክምና ባለሙያዎች ለሚተላለፍ ነው፡፡
በአገልግሎቱ ላይ የሚሳተፉ የህክምና ባለሙያዎች ከተገኘው ገቢ ላይ ክፍፍል የሚያደርጉት የትምህርት ደረጃቸው፣ በሥራው ላይ ያላቸው ተፈላጊነት እና ያሳለፉትን የሥራ ሰዓት መሰረት ባደረገ “የገቢ ክፍፍል ቀመር” መሰረት እንደሚሆን መመሪያው ላይ ሰፍሯል፡፡ በተጨማሪም ሆስፒታሉ፣ የህክምና ባለሙያዎች እና የአስተዳደር ሰራተኞች ከሚያገኙት ገቢ ላይ አንድ አንድ በመቶ የሚቀነስ ሲሆን ይህ ሶስት በመቶ ገቢ “የግል ህክምና ክፍል ቀጣይነትን ለማረጋገጥ” እንደሚውል ተደንግጓል፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)