የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመስከረም አበራ ላይ ክስ ለመመስረት ለዐቃቤ ህግ ሰባት ቀናት ፈቀደ

በሃሚድ አወል

ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር በዋለችው የ“ኢትዮ ንቃት” የዩቲዩብ መገናኛ ብዙሃን መስራች እና ባለቤት መስከረም አበራ ላይ ክስ የመመስረቻ ሰባት ቀናት በፍርድ ቤት ፈቀደ፡፡ ፍርድ ቤቱ የክስ መመስረቻ ቀናቱን የፈቀደው ዐቃቤ ህግ መስከረም በተጠረጠረችበት ጉዳይ የተሰባሰቡ “የቪዲዮ እና ሰነድ ማስረጃዎችን ለመተንተን ጊዜ እንደሚያስፈልገው በማመን” መሆኑን አስታውቋል፡፡

ከ16 ቀናት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለችው መስከረም ዛሬ ሐሙስ ታህሳስ 20፤ 2015 ለሁለተኛ ጊዜ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርባለች፡፡ ችሎቱ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው ፖሊስ ባለፈው ቀጠሮ በተፈቀደለት 14 የምርመራ ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት ለማድመጥ ነበር፡፡ ችሎቱ ከሁለት ሳምንት በፊት ታህሳስ 6፤ 2015 በነበረው ቀጠሮ ለፖሊስ “የሰው ምስክሮችን እንዲያሰባስብ” 14 የምርመራ ቀናትን መፍቀዱ ይታወሳል፡፡

ዛሬ በጽህፈት ቤት በኩል በሶስት ዳኞች በተሰየመው ችሎት ዐቃቤ ህግ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንደደረሰው በመግለጽ ለክስ መመስረቻ 15 ቀናት እንዲፈቀዱለት በጽሁፍ ጠይቋል፡፡ ተጠርጣሪዋን ወክለው በችሎት የተገኙት ሶስት ጠበቆች በበኩላቸው ዐቃቤ ህግ የጠየቀው የክስ መመስረቻ ቀናት ሊፈቀዱለት አይገባም ሲሉ ተቃውመዋል፡፡

ጠበቆቹ ለተቃውሟቸው ያቀረቡት መከራከሪያ ዐቃቤ ህግ ምርመራውን በበላይነት ሲመራው የነበረ መሆኑን ነው፡፡ መስከረም አበራ የተጠረጠረችበት ወንጀል “ዋስትና የማያስከለክል” መሆኑንም ጠበቆቹ በተጨማሪ መከራከሪያነት አንስተዋል፡፡ የፌደራል ፖሊስ መስከረም አበራን ለመጀመሪያ ጊዜ ችሎት ፊት ባቀረበበት ወቅት “በሽብር የወንጀል ድርጊት” እንደጠረጠራት ለችሎቱ አስታውቆ ነበር፡፡

ዐቃቤ ህግም በተመሳሳይ በመስከረም አበራ ላይ ሲደረግ የነበረውን ምርመራ በበላይነት ሲመራ እንደነበር ለችሎቱ አረጋግጧል፡፡ “የተጠርጣሪዋን አያያዝ እና የማስረጃ አሰባሰብ ሂደቱን መርተናል” ያለው ዐቃቤ ህግ “የቪዲዮ፣ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን ተንትኖ ውሳኔ ለመስጠት” ግን ጊዜ እንደሚያስፈልገው ለችሎቱ ገልጿል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጡት ዳኞች ለ20 ደቂቃዎች ያህል ቢሯቸውን ዘግተው ከመከሩ በኋላ ዐቃቤ ህግ “ምርመራውን ሲመራ የነበረ በመሆኑ እና ጉዳዩንም ስለሚያውቀው” በሚል ለክስ መመስረቻ ከጠየቀው 15 ቀናት ውስጥ ሰባቱን ፈቅደዋል፡፡

በሀዋሳ መምህራን ኮሌጅ እና በዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ስነ ዜጋ መምህር የነበረችው መስከረም አበራ፤ አበራ ለእስር ስትዳረግ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ከስድስት ወራት በፊት ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት” ወንጀል ተጠርጥራ በቁጥጥር ስር ውላ ነበር። የ37 ዓመቷ መስከረም፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት በሚገኘው ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ 23 ቀናትን በእስር ላይ ካሳለፈች በኋላ በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር የተለቀቀችው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)