በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች 8.3 ሚሊዮን ሰዎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ

በአማኑኤል ይልቃል

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በተደረገባቸው የትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች 8.35 ሚሊዮን ሰዎች የእለት ደራሽ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ ከሶስቱ ክልሎች ከፍተኛ የእርዳታ ጠባቂ ቁጥር ያለበት ትግራይ ክልል ሲሆን በክልሉ ውስጥ 5.2 ሚሊዮን ሰዎች የእለት ደራሽ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

 የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ይህንን ያስታወቀው ዛሬ አርብ ታህሳስ 21፣ 2015 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም እንዳስታወቁት ከፍተኛ የእርዳታ ፈላጊ ቁጥር ባለበት ትግራይ ክልል በሁሉም ዞኖች የእለት ደራሽ እርዳታ ጠባቂዎች አሉ፡፡ በክልሉ ለአንድ ወር የሚያስፈልገው የምግብ እርዳታ መጠን 88,179 ሜትሪክ ቶን መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በግማሽ ያነሰ ወርሃዊ የእርዳታ መጠን የሚያስፈልገው የአማራ ክልል ካሉት 11 ዞኖች ውስጥ እርዳታ ፈላጊ የሆኑት ሶስቱ ናቸው፡፡ በአማራ ክልል እርዳታ በሚፈልጉት ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ሰሜን ጎንደር እና ሰሜን ወሎ ዞኖች 2.4 ሚሊዮን ሰዎች የዕለት ደራሽ እርዳታ ጠባቂ ናቸው ተብሏል፡፡

በተመሳሳይ በሶስት ዞኖች ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች እርዳታ ፈላጊ በሆኑበት በአፋር ክልል የተረጂዎች ቁጥር ከ715 ሺህ በላይ እንደሆነ ኮሚሽነሩ በመግለጫው ላይ ተናግረዋል፡፡ በሶስቱ ዞኖች የዕለት እርዳታ ጠባቂ ለሆኑት 8.3 ሚሊዮን ሰዎች ሙሉ በሙሉ እርዳታ ለማቅረብ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር ሽፈራው፣ “ሰፊ የሆነ የሀብት ምደባ ተካሂዶ እየተሰራ ነው” በማለት የገንዘቡን መጠን ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፡፡

ኮሚሽነሩ በዛሬው መግለጫቸው እንዳስታወቁት በጥቅምት እና ህዳር ወራት ወደ ሶስቱ ክልሎች በተጓጓዘ የምግብ ድጋፍ፤ የመጀመሪያ ዙር የእርዳታ ፍላጎት መቶ በመቶ ተሸፍኗል። በእነዚህ አካባቢዎች የቀረበው የመጀመሪያ ዙር እርዳታ የነዋሪዎችን “የስድስት ሳምንት ፍላጎት” የሚሸፍን እንደሆነ የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ “ሶስቱም ክልሎች ላይ የሚፈለገውን 141,671 ሜትሪክ ቶን ምግብ እና አልሚ ምግብ በማድረስ የመጀመሪያውን ዙር መሸፈን ተችሏል” ብለዋል፡፡ ሁለተኛ ዙር እርዳታ ስርጭት እየተከናወነ መሆኑን እና እስከ አሁን 20 በመቶውን የእርዳታ ፍላጎት መጓጓዙን አስታውቀዋል፡፡

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በተጎዱት ትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ያለው የእርዳታ ፍላጎት “በአጋር አካላት እንዲሸፈን” በእቅድ ተይዞ ነበር፡፡ ይሁንና “አጋር አካላት ዝግጅት እስከሚያጠናቅቁ” መንግስት ከ877 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች እርዳታ ማቅረቡን አመልክተዋል፡፡ በሶስቱ ክልሎች ከፍተኛውን የእርዳታ አቅርቦት እያደረጉ ያሉት የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጥምረት (JEOP) መሆናቸው ተገልጿል፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)