በፓርላማው አፈ ጉባኤ የተመራው ልዑክ የመቐለ ጉዞ በተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄ ተነሳበት

በሃሚድ አወል

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ መሪነት በከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ወደ መቐለ የተደረገው ጉዞ በፓርላማ አባላት የአግባብነት ጥያቄ ተነሳበት። የፓርላማ አባላቱ ጥያቄውን ያነሱት ትላንት አርብ ታህሳስ 21፤ 2015 በምክር ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ነው።

ግማሽ ቀን በፈጀው በትላንትናው ዝግ ስብሰባ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን እና የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ የሰላም ሂደቱን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎም በዚሁ ማብራሪያ ላይ ተገኝተው ነበር፡፡ በትላንትናው ስብሰባ የተሳተፉ ሶስት የምክር ቤት አባላት ከደቡብ አፍሪካ እስከ መቐለ ስለዘለቀው የሰላም ስምምነት ሂደት ለአባላቱ ማብራሪያ መሰጠቱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል፡፡

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት ሂደት ያለበትን ደረጃ እና ታጣቂዎቹ ወደ መደበኛ ህይወት ስለሚመለሱበት አኳኋን ለአባላቱ ማብራሪያ መሰጠቱን ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል። በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ ታህሳስ 17፤ 2015 በአፈ ጉባኤው መሪነት ወደ መቐለ የተደረገው ጉዞ የማብራሪያው አንድ አካል ነበር።

የምክር ቤት አባላቱ፤ በአፈ ጉባኤው የተመራውን ጉዞ በተመለከተ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎችን ማብራሪያ ለሰጡት የመንግስት ኃላፊዎች ማቅረባቸውን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡ በውይይቱ ላይ አብዛኛውን ዕድል ያገኙት የገዢው ብልጽግና ፓርቲ አባላት፤ “አሸባሪ ከተባለ ቡድን አመራሮች ጋር ለመነጋገር አፈ ጉባኤው ለምን ወደ መቐለ ሄዱ?” የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የብልጽግና ፓርቲ ተወካይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

አንድ ሌላ የምክር ቤት አባል ደግሞ፤ “ ‘አሸባሪ ከተባለ ቡድን ጋር በቅርበት በዚህ ልክ [መቐለ] ሄዶ መወያየት እንዴት መጣ?’ የሚል ሃሳብ ተነስቷል” ሲሉ በውይይቱ የተንጸባረቀውን ተመሳሳይ ሃሳብ አጋርተዋል፡፡

ሌላ የውይይቱ ተሳታፊ “አምባሳደሩ [አቶ ሬድዋን] በሰላም ድርደሩ ሂደት ውስጥ ሁኔታዎች ፈር ሲይዙ ቡድኑን ከሽብር መዝገብ የማሰረዝ ሂደት እንደሚኖር ጠቆም አድርገው አልፈዋል” ሲሉ ለተነሳው ጥያቄ የተሰጠውን ምላሽ ገልጸዋል፡፡ “ነገሮችን ሰፋ አድርጎ በማየት፤ ህወሓትን በማራቅ ብቻ ሳይሆን በማቅረብም ለትግራይ ህዝብ አማራጭ ሃሳብ ማቅረብ ያስፈልጋል” የሚል መልስ መሰጠቱንም የፓርላማ አባሉ አክለዋል፡፡

የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን በበኩላቸው “አሸባሪ ብለን መገናኘቱን ከማቆም እንደዚህ አይነት ቀረቤታ እየፈጠርን ነው ወደ ሰላም ማምጣት የምንችለው” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ተሳታፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገረዋል፡፡

በአፈ ጉባኤው የተመራው ቡድን ያደረገው ጉዞ ላይ ከቀረበው “ጠንከር” ያለ አስተያየት በተጨማሪ የምክር ቤቱ አባላት ለሰላም ሂደቱ ያላቸውን ድጋፍ መግለጻቸውን ሶስቱም ተሳታፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። “ህወሓትን በጥንቃቄ መያዝ ያስፈልጋል” የሚል ስጋት አዘል አስተያየትም ተደጋግሞ ከምክር ቤት አባላቱ መነሳቱን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ጠቁመዋል።

ስጋቱን እንደሚጋሩት ለፓርላማ አባላት የጠቆሙት የመንግስት ኃላፊዎቹ፤ “ህወሓትን ከማራቅ፣ ከመግፋት ይልቅ እያቀረብን ወደ ሰላም ማምጣት መቻል አለብን” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)