የጉራጌን የክልልነት ጥያቄ “በአጭር ጊዜ” እውን የማድረግ ዕቅድ እንዳለው ጎጎት ፓርቲ አስታወቀ

በሃሚድ አወል

የጉራጌን የክልልነት ጥያቄ “በአጭር ጊዜ” እውን የማድረግ ዕቅድ ያለው ሀገር አቀፍ ፓርቲ ትላንት እሁድ መጋቢት 3፤ 2015 የምስረታ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ። ጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትህ ፓርቲ (ጎጎት) የተሰኘ ስያሜ ያለው ይህ ፓርቲ፤ ዓላማው “በኢትዮጵያ ኢኮኖሚዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እድገት ውስጥ የጉራጌ ህዝብን ተሳትፎ እና ድርሻ ማሳደግ” መሆኑን በፕሮግራሙ አስፍሯል።

ፓርቲው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ያገኘው ከሶስት ወራት ገደማ በፊት ህዳር 21፤ 2015 ነበር። ጎጎት ጊዜያዊ ፈቃዱን ካገኘ በኋላ በስድስት ክልሎች እና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የመስራች አባላትን ፊርማ ሲያሰባስብ ቆይቷል። ፓርቲው በሶማሌ፣ ሐረሪ፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች 13 ሺህ ገደማ ፊርማ ማሰባሰቡን የፓርቲው አደራጆች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ መሰረት፤ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በሀገር አቀፍ ፓርቲነት የሚመዘገበው 10 ሺህ መስራች አባላት ሲኖሩት ነው። ከመስራች አባላቱ 30 በመቶ ያህሉ የአንድ ክልል መደበኛ ነዋሪዎች መሆን እንዳለባቸው የሚደነግገው አዋጁ፤ ቀሪዎቹ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ክልሎች ቢያንስ በአራቱ መደበኛ ነዋሪ መሆን እንደሚገባቸው ያስገድዳል። 

በቦርዱ የሚጠበቅበትን የመስራች አባላት ፊርማ ያሰባሰበው ፓርቲው፤ በአዲስ አበባው ዋቢ ሸበሌ ሆቴል የመስራች ጠቅላላ ጉባኤውን በትላንትናው ዕለት ያካሄደው በ572 የጉባኤ አባላት ነው። በዚህ ጉባኤ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ እና የኦዲት እና ኢንስፔክሽን አባላት ምርጫ የተከናወነ ሲሆን፤ የፓርቲው መተዳደሪያ ህገ ደንብ፣ ፕሮግራም እና የመመስረቻ ጽሁፍም ጸድቀዋል። 

የጉራጌን በክልል የመደራጀት ጥያቄን በተመለከተ፤ ጎጎት በሙሉ ድምጽ ባጸደቀው የፓርቲው ፕሮግራም በኩል አቋምን አስታውቋል። ፓርቲው በዚሁ ፕሮግራሙ ላይ በክልል የመደራጀት ጥያቄ “ሁሉንም የህግ ሂደቶች ቢያልፍም፤ በገዢውም ሆነ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ተገቢው ድጋፍ ስለተነፈገው፤ ህዝቡ ለአላስፈላጊ እንግልት እየተዳረገ ይገኛል” ሲል ይወቅሳል።

“ይህ የአደረጃጀት እና ሌሎች የጉራጌ ህዝብ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች፤ ህጋዊ እና ተቋማዊ በሆነ ሁኔታ ለመምራት የጎጎት ፓርቲ መቋቋም አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግድ ሆኖ በመገኘቱ ፓርቲው እንዲቋቋም ሆኗል” ሲል ከአዲሱ ፓርቲ መቋቋም ጀርባ ያለውን አመክንዮ ፕሮግራሙ አብራርቷል። የፓርቲው አደራጅ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ መላኩ ሳህሌ፤ የጉራጌ ህዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ፓርቲው በአጭር ጊዜ ሊያሳካው የሚሻው ጉዳይ መሆኑን በጉባኤው ላይ ገልጸዋል።

“ጉራጌ  ህገ መንግስቱ የፈቀደለት [እና] ህግ አክብሮ የጠየቀው የክልልነት ጥያቄ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን መሆን አለበት። ይሄ [የፓርቲው] የመጀመሪያው የአጭር ጊዜ ዕቅዱ ነው” ሲሉ ለጉባኤው ታዳሚዎች ተናግረዋል። ይህ የፓርቲው አደራጅ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ንግግር ከጉባኤው ታዳሚዎች በከፍተኛ ጭብጨባ ድጋፍ አግኝቷል።  

በደቡብ ክልል ከሚገኙ አስራ አንድ ዞኖች እና ስድስት ልዩ ወረዳዎች ውስጥ፤ ነባሩን ክልል ለሁለት የሚከፍለውን የ”ክላስተር” አደረጃጃት ሃሳብ ውድቅ ያደረገው  የጉራጌ ዞን ብቻ ነው። የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ላይ በገዢው ብልጽግና ፓርቲ የቀረበውን ይህን ሃሳብ ውድቅ ያደረገው ከሰባት ወራት በፊት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ባካሄደው ስብሰባ ነበር። ከምክር ቤቱ ውሳኔ በኋላ፤ በዞኑ  ዋና ከተማ ወልቂጤ ተደጋጋሚ የስራ ማቆም እና በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማዎች ተደርገዋል።

ይህን ተከትሎም በቢሮ ኃላፊነት ሲያገለግሉ የቆዩ ስድስት የዞኑ አመራሮች፤ በወቅቱ የጉራጌ ዞን አስተዳዳሪ በነበሩት አቶ መሐመድ ጀማል ፊርማ ከኃላፊነት ከተሰናበቱ በኋላ ለእስር ተዳርገዋል። ከጉራጌ ዞን ምክር ቤት ስብሰባ በኋላ የዞኑ አስተዳዳሪም ቢሆኑ በስልጣን ላይ መቆየት የቻሉት ለሁለት ወራት ገደማ ብቻ ነው። አቶ መሐመድ “የዞኑን ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ” በሚል ምክንያት ባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉ ይታወሳል። 

በገዢው ፓርቲ ከተደረገው ይህ የአመራር ለውጥ፤ በጉራጌ ዞን የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ማብረድ አልቻለም። ባለፈው ህዳር ወር አጋማሽ በወልቂጤ ከተማ ለሶስተኛ ጊዜ ከቤት ያለመውጣት እና የስራ ማቆም አድማ መደረጉን ተከትሎ፤ ዞኑ በኮማንድ ፖስት እየተመራ ይገኛል። አንዴ ጋብ አንዴ ፋም እያለ የቀጠለውን የጉራጌ ዞን የክልልነት ጥያቄን “እውን አደርጋለሁ” ብሎ የተነሳው ጎጎት ፓርቲ፤ ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ዘርፎች የጉራጌን ህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሚሰራ በፕሮግራሙ አስፍሯል።

በፓርቲው ፕሮግራም የተጠቀሰው “የጉራጌ ህዝብ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያለው ድርሻ እና ውክልና እየተመናመነ መጥቷል” የሚለው ሃሳብ፤ በትላንቱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይም ጎልቶ ተንጸባርቋል። የጎጎት ፓርቲ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መሐመድ አብራር በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “የጉራጌ ማህበረሰብ ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ ስብራቶች ገጥመውታል” ሲሉ ተደምጠዋል። ሰብሳቢው አክለውም፤ “ይሔን [ስብራት] እንጠግናለን ብለን የጀመርነው ነው” ሲሉ ፓርቲው የተቋቋመበትን  ሌላኛውን ምክንያት ገልጸዋል።

“እዚህ ያሰባሰበን እንደ ጉራጌ ማህበረሰብ ማህበረሰባዊ ውክልናችን ፖለቲካዊ ተሳትፏችን መንምኗል ብለን ነው” ያሉት አቶ መሐመድ፤ በጉራጌ ህዝብ ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለመቋቋም “የሀገሪቱ ህግ በሚፈቅደው መልኩ” መደራጀት አይነተኛ መፍትሔ መሆኑን ጠቁመዋል። “በዚህ ጉዳይ መሽኮርመማችን፤ ወደ ኋላ ማለታችን ነው ለዚህ ሁሉ ያደረሰን የሚለው ገፊ ምክንያት ነው ይህን ፓርቲ እንዲመሰረት ያደረገው” ሲሉም የኮሚቴው ሰብሳቢ አክለዋል።

የፓርቲው አደራጅ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ሒንዲያ ሻፊም በጠቅላላ ጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ተመሳሳይ ሃሳብ አንስተዋል። ወይዘሮ ሒንዲያ “ጉራጌ የራሱን አደረጃጀት ፈጥሮ ባለመታገሉ ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ከመደገፍ አልፎ የውጤቱ ተጠቃሚ የሚሆንበት ዕድል ሊፈጠር አልቻለም” ሲሉ የፓርቲውን መመስረት አስፈላጊነት አስረድተዋል።

የጎጎት ፓርቲ አደራጅ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ መላኩ በበኩላቸው፤ ፓርቲው በሀገራዊ እና አካባቢያዊ ምርጫዎች “ንቁ ተሳታፊ” በመሆን የጉራጌ ህዝብ ጥቅምን ለማስጠበቅ  እንደሚወዳደር አመልክተዋል። ፓርቲው በረዥም ጊዜ ሊያሳካው ያቀደው ዕቅድ “ጉራጌ በሀገር ግንባታው ባደረገው አስተዋጽኦ ልክ በርትዕ፣ በዲሞክራሲ፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ጉዳይ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ” መሆኑንም አክለዋል። 

አዲሱ ፓርቲ ይህን ለማስፈጸም የሚከተለው የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም “ለዘብተኛ ሊብራሊዝም” እንደሚሆን በፕሮግራሙ ላይ አስፍሯል። ጎጎት አሁን በስራ ላይ ካሉት የመንግስት የስራ ቋንቋዎች በተጨማሪ፤ ጉራጊኛ የፌደራሉ የስራ ቋንቋ እንዲሆን “በትኩረት” እንደሚሰራም በፕሮግራሙ አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)