በሃሚድ አወል
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ከመንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት “መልሶ ለማጤን” የሚያስችል ጥናት የሚያደርግ ግብረ ኃይል ማቋቋሙን የፓርቲው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ገለጹ። የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በበኩላቸው፤ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የፓርቲውን የአምስት ዓመት ጉዞ ትንተና የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ግብረ ኃይሉ የተቋቋመው፤ የፓርቲው ብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 2፤ 2015 ባካሄደው ስብሰባ መሆኑን የፓርቲው ምንጮች ተናግረዋል። ብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በዚሁ ስብሰባው፤ የፓርቲውን የስድስት ወራት አፈጻጸም የገመገመ ሲሆን እና በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይም ውይይት አድርጓል።
በወይይቱ ላይ የመሪው ክንፍ ሪፖርት ማቅረቡን የተናገሩት የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ሙሉዓለም ተገኘወርቅ፤ ፓርቲው ከመንግስት ጋር ያለው ግንኙነት ላይ ውይይት እንደተደረገበት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። “ሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮችን ስንገመግም አንድ አብረን ያየነው አጀንዳ [እንጂ]፤ ለብቻው የቀረበ አጀንዳ አይደለም” ሲሉም ጉዳዩ ውይይት የተደረገበትን አውድ አስረድተዋል።
የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ግን ፓርቲው “ከመንግስት ጋር ያለውን አብሮ የመስራት ግንኙነት፤ እንደገና ማጤን እንደሚያስፈልገው” ውሳኔ ማሳለፉን ተናግረዋል። ኢዜማ ከመንግስት ጋር ያለውን ግንኙት ለመፈተሽ የወሰነው፤ “መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚከሰቱ ችግሮች የሚሰጣቸው ምላሾች ችግሮችን የሚያባብሱ እና ሌሎች አዳዲስ ችግሮችን የሚፈጥሩ በመሆናቸው ነው” ሲሉ የፓርቲው ምንጮች ምክንያቱን አብራርተዋል።
ይህንንም በተመለከተ ጥናት የሚያደርግ ግብረ ኃይል መቋቋሙን እና የሁለት ሳምንት ጊዜ እንደተሰጠው እነዚሁ ምንጮች አስረድተዋል። ከግብረ ኃይሉ ግምገማ በኋላ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው፤ ጠቅላላ ጉባኤ ሊጠራ እንደሚችልም ጠቁመዋል። በኢዜማ መተዳዳሪያ ደንብ መሰረት፤ በየሶስት ዓመቱ የሚካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ የፓርቲው ከፍተኛ የስልጣን አካል ነው። የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ፤ አስቸኳይ ጉባኤ የመጥራት ስልጣን እንዳለው መተዳደሪያ ደንቡ ይደነግጋል።
ኢዜማ ከመንግስት ጋር ለመስራት ሲወስን “በትብብር ለውጥ ማምጣት የሚቻልባቸው ጉዳዮች አሉ” ከሚል ትንተና መሆኑን የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። “በገዢው ፓርቲ ውስጥ ያሉ የብሄር መጓተቶች” እንዲሁም ከሰሞኑ ከአድዋ ክብረ በዓል ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ክስተቶች “ኢዜማ ከመንግስት ጋር መስራቱ ላይ የራሱ ተጽዕኖ ይኖረዋል” የሚሉት ዶ/ር ሙሉዓለም፤ እንዲያም ቢሆን ግን ጉዳዩ የብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው “ዋነኛ አጀንዳ አልነበረም” ሲሉ አስተባብለዋል።
“ፖለቲካዊ የኃይል አሰላለፍ ላይ ለውጥ ይታያል፤ የሚታዩ ትክክል ያልሆኑ የህግ አሰራሮች አሉ” ያሉት ዶ/ር ሙሉዓለም፤ “እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ትንተና መስራት፤ በትክክል ጥናት ማድረግ አለብን ብለን ወስነናል” ሲሉ በስብሰባው የተላለፈውን ውሳኔ ገልጸዋል። ጥናቱን እንዲያደርግም በፓርቲው መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የሚመራ ግብረ ኃይል መቋቋሙን አመልክተዋል። ግብረ ኃይሉ የጥናት ግኝቱን “በአጭር ጊዜ” ለብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው እንደሚያቀርብም አስታውቀዋል።
ኢዜማ ከመንግስት ጋር አብሮ ለመስራት ውሳኔ ያሳለፈው፤ በመስከረም 2014 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነበር። ፓርቲው በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤው፤ በመንግስት የስራ አስፈጻሚ ቦታዎች ላይ የኢዜማ አባላትን ለመሾም ከገዢው ብልጽግና ፓርቲ የቀረበውን ጥያቄ መቀበሉ ይታወሳል። በጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔው መሰረት የፓርቲው መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስቴር ሆነው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ካቤኒ ሲቀላቀሉ፤ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ ደግሞ የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን እንዲመሩ በከንቲባ አዳነች አቤቤ ተሹመዋል።
ይህ የፓርቲው ውሳኔ፤ የኢዜማ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከተወሰኑ የፓርቲው አባላት ተቃውሞ ሲቀርብበት ቆይቷል። ጠቅላላ ጉባኤው በተካሄደበት ወቅት የፓርቲው የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት የኮሚዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊ የነበሩት አቶ ዘላለም ወርቅአገኘሁ፤ የፓርቲውን ውሳኔ በመቃወም ራሳቸውን ከፓርቲው ማግለላቸውን አስታውቀው ነበር።
ከዚህ ውሳኔ አንድ ዓመት ገደማ በኋላ “የለውጥ አመራር” ነን ያሉ የፓርቲው አመራሮች፤ ኢዜማ ከመንግስት ጋር ባለው ግንኙነት ላይ የተለየ ሃሳብ ይዘው ቀርበዋል። ኢዜማ ከገዢው ፓርቲ ጋር በተያያዘ የተከተለው “ለዘብተኛ አካሄድ”፤ ፓርቲው በሕዝብ ዘንድ ያለው “ተቀባይነት እና ተሰሚነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፏል” ሲሉ እነዚሁ የፓርቲው አመራሮች መተቸታቸው ይታወሳል።
ከእነዚህ የፓርቲው አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት የቀድሞው የፓርቲው ምክትል መሪ አቶ አንዷለም አራጌ፤ “ከመንግስት ጋር ያለው ነገር ለከት ማጣት የለበትም። በአግባቡ መያዝ አለበት። መርህ ያለው ደርዝ ያለው አያያዝ መሆን አለበት እንጂ፤ ዝም ብሎ በነሲብ የሚሰጥ ድጋፍ ሊሆን አይገባም የሚል ልዩነት አለን” ሲሉ ተናግረው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)