በአማኑኤል ይልቃል
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የክፍለ ከተማ እና ወረዳ ምክር ቤቶች አባላት ብዛት ከ150 እንዳያንስ እና ከ250 እንዳይበልጥ የሚደነግግ አዋጅ አጸደቀ። አዋጁ ከክፍለ ከተማ እና ወረዳዎች የህዝብ ቁጥር ብዛት እንዲሁም ከውክልና ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ተነስተውበታል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት፤ የክፍለ ከተማ እና የወረዳ ምክር ቤት የምርጫ ክልል እና የሚመረጡ አባላትን ለመወሰን የወጣውን ይህንን አዋጅ ያጸደቀው ዛሬ በተጠናቀቀው መደበኛ ጉባኤው ነው። አዋጁ የተዘጋጀው፤ በተያዘው ዓመት የአካባቢ ምርጫን ለማድረግ እቅድ የያዘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የምክር ቤቶቹን አባላት ብዛት እንዲሁም ብዛቱ የሚወሰንበት “ግልጽ እና ተጨባጭ መስፈርት” እንዲላክለት በመጠየቁ መሆኑ ተገልጿል።
የምክር ቤቱ የሰላም፣ ፍትህ እና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሙሉነህ ደሳለኝ፤ ምርጫ ቦርድ የትኞቹ የከተማ አስተዳደሩ መዋቅሮች ለአካባቢ ምርጫ በምርጫ ክልልነት እንደሚያገለግሉ “ተለይቶ፣ በህግ ተደንግጎ እና በምክር ቤት ጸድቆ” እንዲላክለት መጠየቁን ገልጸዋል። ምርጫ ቦርድ ከሁለት ሳምንት በፊት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በክልሎች የምርጫ ህጎች ውስጥ ያሉ ጉድለቶችን የተመለከተ ጥናት በማድረግ ማስተካከያ እንዲደረግ ለክልሎች ደብዳቤ መላኩን አስታውቆ ነበር።
ይሁንና ምርጫ ቦርድ ማስተካከያ እንዲደረግ ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ምላሽ አለማግኘቱን የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ተናግረዋል። የአካባቢ ምርጫ ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ ማስተካከያ አድርጎ ለምርጫ ቦርድ ያስታወቀው የጋምቤላ ክልል መሆኑንም ገልጸው ነበር። ዛሬ ለምክር ቤቱ የቀረበው ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሀሳብ ያቀረቡት አቶ ሙሉነህ፤ አዲስ አበባ ከተማ ከዚሀ ቀደም የምርጫ ክልል እና የምክር ቤት አባላትን የሚወስን ህግ እንዳልነበራት ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አቶ ዣንጥራር አባይ በበኩላቸው፤ የከተማ አስተዳደሩን የታችኛው መዋቅሮች ምክር ቤቶችን የተመለከተ ህግ ከዚህ ቀደም ባይኖርም፤ ሁሉም የክፍለ ከተማ እና የወረዳ ምክር ቤቶች “ወጥ” የሆነ የአባላት ብዛት እንደነበራቸው ለምክር ቤት አባላት አስረድተዋል። “ከዚህ በፊት የነበረው uniform የሆነ ለወረዳዎቹ የሚሰጠው አጠቃላይ የውክልና መጠን፤ 300 የሚል ነበር በሁሉም ወረዳዎች። የክፍለ ከተማን በሚመለከትም 250 የሚል ዳታ [ነበር]” ሲሉ አሁን በስራ ላይ ያለውን የምክር ቤት አባላት አወሳሰን አስረድተዋል።
የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የክፍለ ከተማ እና ወረዳ ምክር ቤቶች አባላት ብዛት “ወጥ” ተደርጎ የተወሰነው ምን አይነት መነሻን በመጠቀም እንደሆነ እንደማይታወቅ ተናግረዋል። ዛሬ ለምክር ቤት የቀረበውን የአዋጅ ረቂቅ ያዘጋጀው ኮሚቴ፤ የምክር ቤት አባላት ቁጥር የተወሰነበትን መነሻ ለመረዳት ባደረገው ጥረት “የተሟላ ቃለ ጉባኤ እንኳ” ማግኘት እንዳልቻለ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል። ከንቲባዋ አዋጁ የተዘጋጀበትን ምክንያት ሲያስረዱም፤ “መነሻ እና በደንብ justification በሌለው ውሳኔ የምክር ቤት አባላት በየወረዳው፣ በየክፍለ ከተማው ‘ይህንን ያህል መሆን አለባቸው’ የሚለው አሰራር እንዲቀር ነው። ህግ እና ስርዓት እንዲኖረው” ብለዋል።
በእነዚህ ምክንያቶች እንደተዘጋጀ በተገለጸው አዋጅ፤ የክፍለ ከተማ እና የወረዳ ምክር ቤቶች የሚኖራቸው ዝቅተኛ የአባላት ብዛት 150 እንደሆነ ደንግጓል። የአዋጅ ረቂቁ እንደሚያስረዳው እስከ 150 ሺህ ነዋሪዎች ያሉት ክፍለ ከተማ፤ 150 የምክር ቤት መቀመጫ ወንበሮች ይኖሩታል። ክፍለ ከተማው ከ150 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን የያዘ ከሆነ፤ በእያንዳንዱ አስር ሺህ ነዋሪዎች አንድ የምክር ቤት መቀመጫ ይጨመራል።
በወረዳዎች ምክር ቤት ላይ ቁጥሩ ዝቅ ተደርጎ፤ ተመሳሳይ አይነት የውክልና ስሌት ተቀምጧል። በዚህ መሰረት እስከ አስር ሺህ ነዋሪዎች ያሉት አንድ ወረዳ፤ በምክር ቤቱ 150 መቀመጫዎች ይኖሩታል። የወረዳው ነዋሪዎች ብዛት ከዚህ የሚበልጥ ከሆነ በአንድ ሺህ ነዋሪዎች አንድ የምክር ቤት መቀመጫ ይጨመራል። ክፍለ ከተማ እና ወረዳዎች የነዋሪዎቻቸውን ብዛት ታሳቢ በማድረግ የምክር ቤት መቀመጫዎችን መጨመር እንደሚችሉ በረቂቅ አዋጁ ላይ ቢሰፍርም፤ የመቀመጫዎቹ ብዛት ግን ከ250 መብለጥ እንደሌለበት ተደንግጓል።
የምክር ቤቶች አባላትን ብዛት በዚህ ስሌት መነሻነት የወሰነው ይህ የአዋጅ ረቂቅ፤ የአዲስ አበባ ክፍለ ከተማዎች እና ወረዳዎች የያዙትን የህዝብ ብዛት ጠቅሶ የሁሉንም ምክር ቤቶች አባላት ብዛት በአባሪ ዘርዝሮ አስቀምጧል። በከተማዋ ያሉት 11 ክፍለ ከተማዎች ውስጥ ያለው የነዋሪ ብዛት ሲደመር 3.98 ሚሊዮን እንደሆነ አባሪው ያስረዳል።
ከክፍለ ከተማዎቹ ውስጥ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር እንዳለው የተጠቀሰው አዲስ ከተማ፤ በምክር ቤት አባላት ብዛት ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል። ክፍለ ከተማው 779 ሺህ ገደማ ነዋሪዎች እንዳሉት በረቂቅ አዋጁ ላይ የሰፈረ ሲሆን፤ በምክር ቤቱ 213 መቀመጫዎች እንደሚኖሩት ተቀምጧል።
በተከታይነት የተቀመጠው ልደታ ክፍለ ከተማ የምክር ቤት አባላቱ ቁጥር 180 ተደርጎ ተወስኗል። ከሁሉም ክፍለ ከተማዎች ዝቅተኛ የነዋሪዎች ቁጥር ያለው አቃቂ ቃሊቲ ሲሆን፤ 150 የምክር ቤት መቀመጫዎች እንደሚኖሩት ረቂቁ ላይ ሰፍሯል። የሁሉም የክፍለ ከተማ ምክር ቤቶች የአባላት ብዛት ድምር 1,883 ሲሆን የሁሉም ወረዳዎች አጠቃላይ የምክር ቤት መቀመጫዎች ብዛት ደግሞ 20,829 ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙት 120 ወረዳዎች በህዝብ ብዛታቸው መነሻነት፤ ከዝቅተኛው 150 እስከ ከፍተኛው 250 መቀመጫዎችን የያዙ ምክር ቤቶች እንደሚኖሯቸው በረቂቅ አዋጁ አባሪ ላይ ተቀምጧል። ከፍተኛውን 250 መቀመጫ በሚይዘው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ወረዳ ሰባት፤ 122 ሺህ ገደማ ነዋሪዎችን የያዘ በአዋጅ ረቂቁ ላይ ተመልክቷል።
ለምክር ቤቱ የቀረበው የአዋጅ ረቂቅ የደነገገው ሌላኛው ጉዳይ፤ የአካባቢ ምርጫ የሚደረግበትን ምርጫ ክልል የሚመለከት ነው። በረቂቁ መሰረት የክፍለ ከተማ ምክር ቤት አባላትን ለመምረጥ በሚደረገው ምርጫ፤ እያንዳንዱ ወረዳ የምርጫ ክልል ሆኖ ያገለግላል። “ከአንድ ምርጫ ክልል ምን ያህል ተወካይ ወደ ምክር ቤቱ ይገባል?” የሚለው የሚወሰነው “በወረዳው ህዝብ ብዛት ላይ በሚመሰረት ምጣኔ” እንደሚሆን በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፍሯል።
በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁት የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት፤ የህዝብ ቁጥርን የተመለከቱ ጥያቄዎችን በሁለት መልኩ አንስተዋል። በቀዳሚነት የተነሳው በወረዳ እና ክፍለ ከተማዎች ውስጥ ይኖራል ተብሎ የተቀመጠው የህዝብ ብዛት ቁጥር ትክክለኛነት ላይ ነው።
ይህንን በተመለከተ አስተያየት የሰጡ የምክር ቤት አባል “ከህዝብ ቁጥር ጋር በተያያዘ መነሻ የተደረገው ነገር ምንድነው? ለምሳሌ በሁሉም ክፍለ ከተማዎች የተቀመጡት የህዝብ ቁጥሮች፤ አሁን ከሚያስተናግዱት የህዝብ ቁጥር አንጻር እና ከተማችን እያንቀሳቀሰች ካለችው የህዝብ ቁጥር አኳያ ከተማችን የሰጠችውን [የሸማቾች] የኩፖን ቁጥር [እንኳ] አይሞላም” ብለዋል።
እኚሁ የምክር ቤት አባል፤ በአዋጅ ረቂቁ ላይ 143 ሺህ ገደማ ተብሎ የተቀመጠውን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ህዝብ ብዛት በማሳያነት ጠቅሰውም፤ “ክፍለ ከተማው ባለው መረጃ ከ350 ሺህ እስከ 400 ሺህ የሚጠጋ ህዝብ አለኝ ነው የሚለው” በማለት ሞግተዋል። በረቂቅ አዋጁ ላይ የተቀመጠው ቁጥር መነሻ ተደርጎ የምክር ቤት አባላት ቁጥር ሲወሰን፤ “የማይወከል ህዝብ” እንደሚኖርም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ብዛትን በተመለከተ በአዋጅ ረቂቁ ክፍሎች ላይ ተመሳሳይ ያልሆኑ ቁጥሮች መቀመጣቸው፤ የምክር ቤት አባላቱ ጥያቄ ያነሱበት ሌላኛው ጉዳይ ነው። የክፍለ ከተማ ምክር ቤቶችን የሚመለከተው የረቂቁ ክፍል የነዋሪዎችን ብዛት 3.98 ሚሊዮን አድርጎ ሲያስቀምጥ፤ ስለ ወረዳዎች ምክር ቤቶች በሚያትተው ክፍል የተቀመጠው የነዋሪዎች ብዛት ድምር 4.17 ሚሊዮን ነው።
ሁሉንም ክፍለ ከተማዎች የተመለከቱ ቁጥሮች በተለያየ መልኩ ቢቀመጡም፤ የጎላ ልዩነት የታየው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ብዛት ላይ ነው። የክፍለ ከተማው ምክር ቤት መቀመጫ ቁጥር ሲወሰን 275 ሺህ ገደማ ነዋሪዎች እንዳሉ ታሳቢ ተደርጎ ሲሆን፤ የወረዳ ምክር ቤቶች መቀመጫ ብዛት ሲወሰን ግን ይህ ቁጥር ወደ 439 ሺህ ገደማ ከፍ ብሏል።
አንዲት የምክር ቤት አባል ይህንን ልዩነት አንስተው “ይሄ የፖለቲካ ውክልና ጉዳይ ነው። የresource ምደባን በጣም ያዛባል። ተጠያቂነትንም የሚያስከትል ስህተቶችን ሊያሰራ ይችላል” ሲሉ በአዋጁ ላይ ካለው “ዳታ” አቀራረብ ጀምሮ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። ለእነዚህ ጥያቄዎች አስተያየት የሰጡት ምክትል ከንቲባው አቶ ዣንጥራር፤ በረቂቅ አዋጁ የተለያዩ ክፍሎች ላይ የታየው የህዝብ ብዛት ቁጥር ልዩነት “ጉድለት” መሆኑን በመጥቀስ መታረም እንዳለበት ተናግረዋል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ የሰፈረው የህዝብ ብዛት፤ በከተማዋ ውስጥ ካለው ነዋሪ ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ አለመሆኑ የህዝብ ቆጠራ ካለመካሄዱ ጋር የሚያይዝ መሆኑን ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል። ይህ አዋጅ ሲዘጋጅ ጥቅም ላይ የዋለው የህዝብ ቁጥር ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የተገኘ የአዲስ አበባ ህዝብ ቁጥር ትንበያ መሆኑንም አስረድተዋል።
“በተለያዩ ጥናቶች፤ አሁን ያለው የአዲስ አበባ ህዝብ ከፍ ያለ ቁጥር እንደሆነ ይታመናል። እኛም በዕለት ተዕለት ስራችን እናውቀዋለን። ግን ደግሞ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣንን ትንበያ መውሰድ ካልቻልን ህጋዊ ሊሆን አይችልም” ሲሉም አብራርተዋል። የምክር ቤቶቹ የመቀመጫ ብዛትም፤ በዚሁ መነሻነት የተወሰነ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ የህዝብ ቆጠራ እስከሚካሄድ ድረስ ከስታትስቲክስ አገልግሎት ከሚገኘው መረጃ ውጪ መጠቀም “ህጋዊ” እንደማይሆን በመግለጽ የአቶ ዣንጥራርን ሀሳብ አጠናክረዋል። የምክር ቤቶቹን መቀመጫ ብዛት “ከፍ እናድርገው” የሚል ሀሳብ ካለ ውይይት ሊደረግበት እንደሚችልበት ከንቲባዋ ጥቆማ ሰጥተዋል። የምክር ቤት አባላት ቁጥር ሲጨምር “የተማረ፣ ጊዜውን የሚሰጥ፣ ተነሳሽት ያለው፣ ለህዝብ በትክክል ውክልና ክብር ኖሮት የሚሰራ” ሰው እንደሚያስፈልግ አዳነች አስረድተዋል።
የምክር ቤት አባልነት “በፖለቲካ ቁርጠኝነት (political commitment) የሚሰራ የነጻ አገልግሎት” መሆኑን ያነሱት ከንቲባዋ፤ በዚህም ምክንያት “በርካታ የህዝብ ቁጥር” ከማስገባት ይልቅ “ወንበሮቹን ውስን” ማድረግ የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል። ከእነዚህ ማብራሪያዎች በኋላ፤ የአዲስ አበባ ከተማ ከክፍለ ከተማና ወረዳ ምክር ቤት የምርጫ ክልል እና የሚመረጡ አባላትን ለመወሰን የተዘጋጀው አዋጅ፤ በ75 የከተማይቱ ምክር ቤት አባላት ድጋፍ፣ በሶስት ተቃውሞ እና በአንድ ድምጸ ተዐቅቦ ጸድቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)