በአማኑኤል ይልቃል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በባለ ሶስት እና አራት እግር የ“ባጃጅ” ተሽከርካሪዎች ላይ የጣለውን ገደብ እንዲያነሳ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጠየቀ። ኮሚሽኑ፤ የከተማ አስተዳደሩ “ላልተወሰነ ጊዜ የጣለው እግድ ሕገ መንግስታዊ ጥበቃ የተደረገላቸውን መብቶች አደጋ ላይ የጣለ” ነው ብሏል።
ኢሰመኮ በተሽርካሪዎቹ ላይ የተጣለው እግድ እንዲነሳ የጠየቀው ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 7፤ 2015 ባወጣው መግለጫ ነው። ኮሚሽኑ፤ አንድ ሳምንት የሆነው የከተማ አስተዳደሩ እግድ፤ መግለጫውን እስከወጣበት ጊዜ ድረስ አለመነሳቱ እንዳሳሰበው አስታውቋል።
ባለፈው ሳምንት የካቲት 30 የተጣለውን እግድ አስመልክቶ የደረሱትን አቤቱታዎች መነሻ በማድረግ፤ ከከተማዋ የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ንግግር ማደረጉን ኢሰመኮ በዛሬው መግለጫው አመልክቷል። የቢሮው ኃላፊዎች በአዲስ አበባ ውስጥ “ወደ አስር ሺህ የሚገመቱ” የባጃጅ ተሽከርካሪዎች “የስራ ፈቃድ ያልተሰጣቸው” መሆናቸውን እንደተናገሩ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
“እንደ አንድ አገልግሎት ሰጪ በከተማዋ አሰራር ሥርዓት ያልተዘረጋላቸው መሆኑን፣ እንዲሁም ሌሎችም ተዛማጅ ችግሮች” ያሉባቸው መሆናቸውም በትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች መነሳቱን ኢሰመኮ ገልጿል። ባጃጆቹ “በአንዳንድ አካባቢዎች ከተቀመጠላቸው የእንቅስቃሴ አካባቢ ውጪ በዋና መንገዶች ላይ” እየሰሩ በመሆኑ “የትራንስፖርት ፍሰት ላይ ጫና” መፍጠሩን ለእገዳው ምክንያት እንደሆነ በከተማዋ ኃላፊዎች እንደተጠቀሰለት ኢሰመኮ በመግለጫው አስታውቋል።
የከተማይቱ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች በሁሉም የባጃጅ ተሽከርካሪዎች ላይ እግድ የጣሉት “ልዩነት እና መድሎ ላለመፍጠር” በሚል እሳቤ እንደሆነ መናገራቸውን በመግለጫው ላይ ሰፍሯል፡፡ ይህ የከተማ አስተዳደሩ እገዳ በተጣለበት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ፤ “መንገድ በመዝጋት” ተቃውሞ ያሰሙ “የጋርመንት አካባቢ ባጃጅ ሹፌሮች” ታስረው ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ በዋስትና እንደተለቀቁ ኮሚሽኑ ገልጿል።
ኢሰመኮ በተሽርካሪዎቹ ላይ የተጣለው እግድ “በከተማዋ ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ መሆኑ፤ የባጃጅ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎቹንና ቤተሰባቸውን ብቻ ሳይሆን፣ እጅግ በርካታ ተጠቃሚዎችንም ችግር ላይ እንደጣለ” መረዳቱን አስታውቋል። ማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ “መተዳደሪያውን፣ ስራውን እና ሙያውን የመምረጥ መብት” ያለው መሆኑ በህገ መንግስቱ እና ኢትዮጵያ ባጻደቀቻቸው “የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች” ጭምር የተረጋገጠ መሆኑን ኢሰመኮ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
“ሕገ-መንግሥታዊ ጥበቃ በተደረገላቸው በእነዚህ ሰብአዊ መብቶች ላይ ገደብ በሚጣልበት ጊዜ” የተለያዩ መርሆዎች ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለባቸው ኮሚሽኑ በመግለጫው አሳስቧል። “መብቶችን ለመገደብ የሚያስችል የሕግ መሠረት መኖር (legality)፣ የገደብ እርምጃ የሚወሰደው ቅቡል ዓላማን ለማሳካት ሲሆን (legitimacy)፣ ዓላማውን ለማሳካት የገደቡ አስፈላጊነት (necessity) እና የገደቡን ተመጣጣኝነት (proportionality) መርሆች ሊከተል ይገባል” ሲል ኢሰመኮ ከግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ጉዳዮችን ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የከተማ አስተዳደሩ እገዳ እነዚህን መርሆዎች ያልተከተለ መሆኑን እንደተናገሩ በመግለጫው ላይ ሰፍሯል። ዋና ኮሚሽነሩ፤ ከባጃጅ የትራንስፖርት ስራ ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ችግሮች ሊፈቱ ይገባ የነበረው “በተገቢው ህጋዊ እርምጃዎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች በማስተዳደር እና ወደ ሕጋዊ” አሰራር በማስገባት እንደነበር ገልጸዋል።
“ወደ ህጋዊ አሠራር እንዲገቡ ማድረግ ሲገባ፣ በጠቅላላ ከተማው ላልተወሰነ ጊዜ ገደብ መጣሉ፤ሕገ-መንግሥታዊ ጥበቃ የተደረገላቸው መብቶችን አደጋ ላይ የጣለ እርምጃ ነው” ሲሉ ዶ/ር ዳንኤል የከተማ አስተዳደሩን እርምጃውን ተችተውታል። “በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንን እንዲሁም ሴቶች እና ህፃናትን ታሳቢ በማድረግ እገዳውን ማንሳትና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ መፈለግ ያስፈልጋል” ሲሉ ዋና ኮሚሽነሩ አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)