በአማኑኤል ይልቃል
የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ በባለ ሶስት እና አራት እግር የ“ባጃጅ” ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው እግድ ከነገ ቅዳሜ መጋቢት 8፤ 2015 ጀምሮ እንደሚነሳ አስታወቀ። የ“ባጃጅ” ተሽከርካሪዎች በየትኛውም ርቀት ከአምስት ብር በላይ ማስከፈል እንደማይችሉ ቢሮው ገልጿል።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ይህንን ያስታወቀው የባለሶስት እና አራት እግር “ባጃጅ” ተሽከርካሪዎችን አስመልክቶ ዛሬ መጋቢት 8፤ 2015 በሰጠው መግለጫ ነው። የቢሮው ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚመራበት መመሪያ መዘጋጀቱን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “አገልግሎቱን ስርዓት ለማስያዝ” እያዘጋጀ ያለው “የአሰራር ማስተካከያ ተግባራዊ እስከሚሆን” በሚል “ባጃጆች” አገልግሎት እንዳይሰጡ ያገደው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የካቲት 30 ነበር። የከተማ አስተዳደሩ ከእግዱ መጣል በኋላ ባወጣው መግለጫ “የባጃጅ አሽከርካሪዎች ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ እንዲሁም የተወሰኑት በወንጀል ድርጊቶች ላይ በመሰማራት የከተማችን ነዋሪ የቅሬታ ምንጭ ሆነዋል” ሲል ወቀሳ አቅርቦ ነበር።
የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊው አቶ ምትኩ ይህንኑ ሀሳብ በዛሬው መግለጫ ላይ አስተጋብተዋል። ኃላፊው የ“ባጃጅ” ተሽከርካሪዎች ከተሰማሩበት መስመር፣ ከአደረጃጀት እና ከመንጃ ፈቃድ ጋር የተያያዙ ችግሮች እንደተስተዋለባቸው አንስተዋል። የ“ባጃጅ” ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች “መስመርን እንደ ርስት የመቁጠር” ችግር ይታይባቸዋል ያሉት ኃላፊው፤ “የተደራጁትም በብሔር ነው” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። “የኮንትራት አገልግሎት በሚል ሽፋን ለሌሎች ወንጀለኞች፤ የተለያየ ስራ ለሚሰሩ ወንጀለኞች ሽፋን ተባባሪ የመሆን ችግሮች አሉ” ሲሉም አክለዋል።
በ“ባጃጅ” ተሽከርካሪዎች አገልግሎት ላይ እነዚህ ችግሮች የተስተዋሉበት አንደኛው ምክንያት፤ አገልግሎቱ የሚመራበት መመሪያ አለመኖሩ መሆኑን አቶ ምትኩ ገልጸዋል። የትራንስፖርት ቢሮው ለዚህ ሲል ያዘጋጀው አዲስ መመሪያ፤ ከስምሪት መስመር፣ ታሪፍ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ አሰራር የሚዘረጋ መሆኑን የቢሮ ኃላፊው አስረድተዋል።
በአዲሱ መመሪያ መሰረት የ“ባጃጅ” ተሽከርካሪዎች አገልግሎት መስጠት የሚችሉት፤ ከዋና መንገድ በወጡ፣ መደበኛ ትራንስፖርት በሌለባቸው እና ከከተማ ውጪ በሆኑ መስመሮች ላይ ብቻ ነው። የ“ባጃጅ” ተሽከርካሪዎች አገልግሎት እንዲሰጡባቸው የተለዩ 138 መስመሮች መዘጋጀቸውን ያስታወቁት አቶ ምትኩ፤ መስመሮቹ ከ0.9 እስከ 2.5 ኪሎሜትር ርቀት ያላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።
የ“ባጃጅ” ተሽከርካሪዎች በእነዚህ መስመሮች ላይ አገልግሎት የሚሰጡበት የታሪፍ አወሳሰን፤ በቁርጥ ተመን (flat rate) የተዘጋጀ መሆኑን የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊው አስታውቀዋል። “የትኛውም ርቀት ላይ ህብረተሰቡ ቢጓጓዝ፤ የትኛውም ርቀት ላይ በተቀመጡት ቦታዎች ላይ ቢጓጓዝ መክፈል የሚጠበቅበት አምስት ብር ብቻ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ከዚህ ታሪፍ በላይ ተላላፊ ሆኖ መስራት አይቻልም። ከዚህ ታሪፍ በላይ ማስከፈል አይቻልም” ብለዋል።
አዲሱ መመሪያ “የባጃጅ” ተሽከርካሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የሚችሉበት ሰዓት ላይም ገደብ ጥሏል። በአዲሱ አሰራር መሰረት “ባጃጆች” የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የሚችሉት፤ ከጠዋት 12 ሰዓት እስከ ምሽት ሶስት ሰዓት ድረስ ብቻ ነው። ይህ የሰዓት ገደብ የተቀመጠው “ከሰላም እና ጸጥታ ስጋቶች” ጋር በተያያዘ መሆኑን ኃላፊው ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ሆኖም የሰዓት ገደቡ “እንደ የሰፈሩ እየታየ ከፍ እና ዝቅ” ሊል እንደሚችል ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በ123 ማህበራት የተደራጁ 9,950 “ባጃጆች” አገልግሎት እንደሚሰጡ የገለጹት አቶ ምትኩ፤ ቢሮው ከዚህ በኋላ ሌሎች ማህበራትንም ሆነ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎችን እንደማይቀበል አስታውቀዋል። በእነዚህ ማህበራት ውስጥ የተደራጁት ተሽከርካሪዎችም ቢሆን አገልግሎት መስጠት የሚችሉት ሰሌዳቸው “ኮድ አንድ” ከሆነ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል።
“የከተማ አስተዳደሩ ባጃጅን የማበረታት ምንም አይነት ፖሊሲ የለውም” ያሉት የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊው፤ በመመሪያው ላይ የተቀመጡትን አሰራሮች የሚተላለፉ የ“ባጃጅ ተሽከርካሪዎች ከ200 ብር እስከ ፈቃድ መነጠቅ ያሉ ቅጣቶች እንደሚጠብቃቸው ተናግረዋል። አቶ ምትኩ እነዚህ አሰራሮች ተግባራዊ ሆነው ከነገ ቅዳሜ ጀምሮ መስፈርቶቹን የሚያሟሉ የ“ባጃጅ” ተሽከርካሪዎች በተሰጣቸው የስምሪት መስመር ላይ አገልግሎት እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።
በ“ባጃጅ” ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው እና ለአንድ ሳምንት ገደማ የቆየውን እግድ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን አስተችቶት ነበር። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትላትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ የ“ባጃጅ” ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው እግድ፤ “ሕገ መንግስታዊ ጥበቃ የተደረገላቸውን መብቶች አደጋ ላይ የሚጥል ነው” ሲል እርምጃውን ተችቷል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ በባለ ሶስት እና አራት እግር የ“ባጃጅ” ተሽከርካሪዎች ላይ የጣለውን ገደብ እንዲያነሳም ኮሚሽኑ በመግለጫው ጠይቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)