በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት እና የፓርቲ ኃላፊዎች፤ “የህዝብን ህብረ ብሔራዊ አንድነት ከሚንዱ፣ ጥላቻን እና ግጭትን ከሚያባብሱ ንግግሮች እና ድርጊቶች እንዲቆጠቡ” ገዢው ብልጽግና ፓርቲ አሳሰበ። የሃይማኖት አባቶች፣ ሚዲያዎች፣ አክቲቪስቶች እና ምሁራንም፤ ያለፉ ቁስሎችን ከሚቀሰቅሱ፣ ጥላቻን ከሚያነግሱ፣ ህዝብ በጥርጣሬ እንዲተያይ ከሚያደርጉ፣ የሀገርን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ ከሚጥሉ ድርጊቶች እና ንግግሮች እንዲጠበቁ ጥሪ አቅርቧል። የፍትሕ እና የጸጥታ አካላትም ይሄን መሰል ንግግሮችን እና ተግባራትን “በቸልታ እንዳይመለከቱ” አቅጣጫ ሰጥቷል።
ገዢው ፓርቲ ማሳሳቢያውን እና ጥሪውን ያቀረበው፤ በፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በኩል ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ነው። ፓርቲው በዚሁ መግለጫው፤ የብልጽግና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከትላንት ሐሙስ መጋቢት 7 ጀምሮ ለሁለት ቀናት ባካሄደው ስብሰባ፤ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት “እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን” በተመለከተ በዝርዝር መወያየቱን አስታውቋል።
የስራ አስፈጻሚው ኮሚቴው በዚሁ ስብስባው፤ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እያታዩ ያሉ ተግዳሮቶች በአምስት ዋነኛ ምክንያቶች የመጡ መሆናቸውን ከስምምነት ላይ እንደደረሰበት አስታውቋል። “መግባባት ያልተፈጠረባቸው እና ያልተፈቱ የታሪክ ዕዳዎች”፣ “ነጻነትን ለማስተዳደር አለመቻል” እንዲሁም “ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች እየገነገኑ መምጣታቸው”፤ በገዢው ፓርቲ በፈተናነት የተነሱ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው። ብልጽግና ፓርቲ በፈተናነት ከጠቀሳቸው ውስጥ “የኑሮ ውድነት” እና “ሌብነት” ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ ታሪክ “ተገቢው ዕውቅና ሊሰጠው የሚገባው ዕድል” እንዳመጣ ሁሉ፤ “መራገፍ የሚገባውን ዕዳ ያሸከመ” መሆኑ መዘንጋት እንደሌለበት የብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዛሬው መግለጫው አመልክቷል። “ኢትዮጵያውያን አያሌ አኩሪ ታሪኮችና በታሪክ ውስጥ ያገኘናቸው ዕድሎች አሉን። በእነዚህ እንኮራለን፤ ለኢትዮጵያ ብልጽግናም እንደ አንጡራ ሀብት እንጠቀምባቸዋለን። በተቃራኒው ደግሞ በታሪካችን ውስጥ ያልፈታናቸው፣ ተጨማሪ ችግር አድርገን የጨመርናቸውና ያልተግባባንባቸው ዕዳዎችም አሉን። እነዚህ ዕዳዎቻችን የእኛ ብቻ አይደሉም። በዓለም ላይ ሀገር የመሠረቱ ሕዝቦች ሁሉ የሚገጥሟቸው ናቸው” ሲል የስራ አስፈጻሚው ኮሚቴው በመግለጫው አስፍሯል።
የታሪክ ዕዳዎች “የመነታረኪያ፣ የመጋጫና የመከፋፈያ ምክንያቶች ሊሆኑብን አይገባም” ያለው ፓርቲው፤ ይህንን ማረም የሚቻለው “በምክክር፣ ይቅርታ እና ዕርቅ” መሆኑን ገልጿል። በኢትዮጵያ የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር፤ እንዲህ አይነት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል መንገድ መሆኑም ፓርቲው በመግለጫው ጠቅሷል። የብልጽግና ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች፤ ያለፉ ታሪካዊ ዕዳዎችን “እንደ ግጭት መሳሪያ ለመጠቀም የሚሹ ኃይሎች” በመታገል፤ ለሀገራዊ ምክክሩ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል።
ገዢው ፓርቲ በሁለተኛ ፈተናነት ያነሳው፤ “ነጻነትን በኃላፊነት የመጠቀም” ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ፤ አካባቢን የማስተዳደር፣ የመደራጀት፣ ሐሳብን የመግለጥ፣ መንግስትን የመቃወም፣ ሚዲያን የማቋቋምና የመጠቀም፣ እምነትን ያለ መንግስት ጣልቃ ገብነት የማምለክ ነጻነቶችን በትግሉ መጎናጸፉን ፓርቲው በመግለጫው አስታውሷል። ሆኖም እነዚህን ነጻነቶች በማስተዳደር ረገድ ችግሮች መስተዋላቸውን ፓርቲው አክሏል።
“በነጻነት መተዳደር ማለት ሕግ በማክበር፣ ሌሎችን ሳይጎዱ፣ ሀገር ሳያፈርሱ እና ግጭት ሳይቀሰቅሱ፤ መብትን ለመጠቀም መቻል ነው። ሕግ እያፈረሱ፣ የሌሎችን መብት እየጣሱ፣ ግጭትና ጥላቻን እየቀሰቀሱ፣ ብሎም ሀገር እያተራመሱ መንቀሳቀስ ግን ወንጀል እንጂ ነጻነት ሊሆን አይችልም” ያለው ብልጽግና ፓርቲ፤ በዚህ ረገድ በተለያዩ አካላት የሚታየው ችግር “በቶሎ ሊገራ የሚገባው መሆኑን” የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መገምገሙን አስታውቋል።
ገዢው ፓርቲ “ነጻነትን የማስተዳደር ችግሮች ተስተውሎባቸዋል” ሲል በመግለጫው የጠቀሳቸው አካላት፤ የአካባቢ አስተዳደሮች፣ ሚዲያዎች፣ የእምነት ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አክቲቪስቶች ናቸው። “ነጻነት ከኃላፊነት ጋር ሚዛናዊነቱን ጠብቆ መሄድ” እንደሚገባው በመግለጫው አጽንኦት የሰጠው ብልጽግና ፓርቲ፤ ይህን በተመለከተ ችግር የተስተዋለባቸው አካላትን ጨምሮ የመንግስት እና የፍትሕ ተቋማት፣ ምሁራን እና የሀገር ሽማግሌዎች የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
የብልጽግና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በመግለጫው በሶስተኛነት የጠቀሰው ተግዳሮት፤ “ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚፈታተኑ ሁኔታዎችን” ነው። “ዛሬ ባለችው ኢትዮጵያ ማንም የበላይ እና የበታች ሆኖ መኖር አይችልም” ያለው ፓርቲው፤ የፓርቲ እና የመንግስት አመራሮች ያሉባቸውን ችግሮች “በውይይት እና በሕግ አግባብ ብቻ እንዲፈቱ ማድረግ አለባቸው” ብሏል። በየደረጃው የሚገኙ እነዚህ አመራሮች “የሕዝብን ህብረ ብሔራዊ አንድነት ከሚንዱ፣ ጥላቻንና ግጭትን ከሚያባብሱ ንግግሮች እና ድርጊቶች” እንዲቆጠቡም ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
የሃይማኖት አባቶች፣ ሚዲያዎች፣ አክቲቪስቶችና ምሁራንም “ ያለፉ ቁስሎችን ከሚቀሰቅሱ፣ ጥላቻን ከሚያነግሡ፣ ሕዝብ በጥርጣሬ እንዲተያይ ከሚያደርጉ፣ የሀገርን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ ከሚጥሉ ድርጊቶችና ንግግሮች እንዲጠበቁ” የብልጽግና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዛሬው መግለጫ ጥሪ አቅርቧል። የሚመለከታቸው የፍትሕና የጸጥታ አካላትም፤ ይህን መሰል ንግግሮችን እና ተግባራትን “በቸልታ እንዳይመለከቱ” ፓርቲው አሳስቧል።
ኢትዮጵያ “በወሳኝ ምእራፍ ላይ” እንደምትገኝ በመግለጫው የጠቀሰው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው፤ ብልጽግና ፓርቲ እየተገበራቸው የሚገኙትን “ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ለማጨናገፍ ከየአቅጣጫው የሚወረወሩ ፈተናዎችን” መሻገር እንደሚገባ አመልክቷል። ይህን እውን ለማድረግም፤ ነጻነቶችን “በኃላፊነት ማስተዳደር”፣ የፕሬስ ነጻነትን “በተገቢው ሕግ፣ ልክና መጠን፤ ሀገርና ሕዝብን በሚጠቅም ቅኝት ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ” እንደሚገባ ገዢው ፓርቲ በመግለጫው ማጠቃለያ አስገንዝቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)