የአፍሪካ ህብረት፤ መንግስትን እና በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰውን ታጣቂ ቡድን እንዲያደራድር የፓርላማ አባላት ጠየቁ   

በሃሚድ አወል

የአፍሪካ ህብረት፤ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰውን “ታጣቂ ኃይል” እና መንግስትን እንዲያደራድር ከኦሮሚያ ክልል የተመረጡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጠየቁ። ህብረቱ በክልሉ ለአራት አመታት “የበርካቶችን” ህይወት የቀጠፈውን “ውጊያ” አቅልሎ ማየቱ እንዳሳዘናቸው የፓርላማ አባላቱ ገልጸዋል። 

የተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ ጥያቄውን ያቀረቡት፤ በኦሮሚያ ክልል ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ ዛሬ ሰኞ፤ መጋቢት 11፤ 2015 ለአፍሪካ ህብረት በጻፉት ደብዳቤ ነው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ባለ አንድ ገጽ ደብዳቤ፤ “በትግራይ የተፈጠረው ሰላም በኦሮሚያ እንዲደገም እንፈልጋለን። ስለዚህ የአፍሪካ ህብረት ጣልቃ ገብቶ እንዲያደራደር እና ህዝባችን በሰላም እንዲኖር እንጠይቃለን” ይላል።

በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈው ይኸው ደብዳቤ፤ በኦሮሚያ ክልል ለሚንቀሳቀሰው “የታጠቀ ኃይል” ከክልሉ መንግስት በኩል በቅርቡ የእርቅ ጥሪ መቅረቡን አስታውሷል። የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ወደ እርቅ እንዲመጡ ጥሪ ያቀረቡት፤ ከአንድ ወር በፊት የካቲት 10፤ 2015 በተካሄደው የጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤ ላይ ነበር።

ፎቶ፦ ከOBN ቴሌቪዝን የተወሰደ

አቶ ሽመልስ በክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ባሰሙት በዚሁ ንግግር፤ “በክልላችን የሚንቀሳቀሱ እንደ ኦነግ ሸኔ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች ወደ እርቅ እንዲመጡ በህዝባችን ስም እጠይቃለሁ” ብለው ነበር። ራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ጦር” የሚለው ታጣቂ ቡድን የርዕሰ መስተዳድሩን ጥሪ ቢቀበለውም፤ ጥያቄውን “ግልጽነት የጎደለው” ሲሉ ተችቶታል። 

ታጣቂ ቡድኑ ጥሪው በቀረበበት ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ “ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር በሚደረገው የሰላም ንግግር የኦሮሚያ ክልል የሂደቱ አካል መሆን እንዳለበት” እንደሚገነዘብ ጠቅሷል። ሆኖም የሰላም ሂደቱ “መመራት ያለበት” በፌደራል መንግስት መሆኑን በወቅቱ አስታውቆ ነበር። “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ለዚህ በምክንያትነት ያነሳው፤ ታጣቂ ቡድኑን በአሸባሪነት የፈረጀው የፌደራል ፓርላማ መሆኑን ነው። 

በዚሁ የታጣቂ ቡድኑ መግለጫ የተጠቀሰው ሌላው አበይት ጉዳይ፤ ከፌደራል መንግስት ጋር የሚደረገውን እርቅ “ገለልተኛ” የሆኑ “ሶስተኛ ወገኖች” ሊታዘቡት ይገባል የሚለው ነው። ቡድኑ በሰላም ንግግሩ ላይ ዓለም አቀፍ አካላት እንዲሳተፉ የሚሻው፤ “በእርቅ ወቅት የተደረሱ ስምምነቶችን የተፈጻሚነት ዋስትና መስጠት የሚችሉት” እነርሱ “ብቻ ናቸው” የሚል አቋም ስላለው መሆኑን በመግለጫው አስታውቋል።

ከኦሮሚያ ክልል የተመረጡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ የአፍሪካ ህብረት መንግስትን እና ታጣቂ ቡድኑን የማሸማገል ሚና እንዲወጣ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። በፓርላማው የኦሮሚያ ክልል ተመራጮች አስተባባሪ አቶ ብዙአየሁ ደገፋ፤ በሁለቱም ወገኖች በኩል ኮሚቴ ተዋቅሮ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ይሁን ሌላ ቦታ ውይይት እንዲደረግ የፓርላማ አባላቱ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል። “አፍሪካ ህብረት ይህን እንዲያወያይ ነው የጠየቅነው” ሲሉም በደብዳቤያቸው ያቀረቡትን ጥሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።

የፓርላማ አባላቱ ዛሬ ጠዋት በአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት በአካል ተገኝተው ያስገቡት ይኸው ደብዳቤ፤ በህብረቱ ላይ የተሰነዘረ ወቀሳንም አካትቷል። በአፍሪካ ህብረት መሪነት ለሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እልባት መገኘቱን እንዳስደሰታቸው የገለጹት የፓርላማ ተመራጮቹ፤ በኦሮሚያ ክልል ላለው የጸ ጥታ ችግር ተመሳሳይ ጥረት ሊደረግ ይገባ እንደነበር አመልክተዋል። “በኦሮሚያ ክልል ከአራት አመታት በላይ የፈጀውን ውጊያ፤ የአፍሪካ ህብረት አቅልሎ በመመልከቱ በጣም አዝነናል” ሲሉም የፓርላማ አባላቱ በደብዳቤያቸው አስፍረዋል። 

ከኦሮሚያ ክልል የተመረጡ የፓርላማ አባላት፤ በኦሮሚያ ክልል ያለው የጸጥታ ችግር “በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለበት” የሚል አቋማቸውን ሲያሳውቁ የአሁኑ የመጀመሪያቸውን አይደለም። የፓርላማ አባላቱ ከሶስት ወራት ገደማ በፊት ባቀረቡት ምክረ ሃሳብ፤ ለክልሉ የጸጥታ ችግር መፍትሔ ለማምጣት “የሰላም ስምምነት መደረግ አለበት” የሚል ምክረ ሃሳብ አቅርበው ነበር። ይህንኑ ምክረ ሃሳባቸውን፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እና የኦሮሚያ ክልል መንግስትን ጨምሮ ለስድስት አካላት በጻፉት ደብዳቤ በወቅቱ አስታውቀዋል። 

የተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ በዛሬው ዕለትም፤ ለሶስት አካላት ተጨማሪ ደብዳቤ ጽፈዋል። ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ለብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት እና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተጻፈው ይኸው ደብዳቤ፤ በፌደራል መንግስት እና በኦሮሚያ ክልል በሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ሊካሄድ የታሰበው እርቅ “ተግባራዊ እንዲደረግ” የሚጠይቅ መሆኑን የፓርላማ ተመራጮች አስተባባሪው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካሉት 547 መቀመጫዎች፤ 178 ያህሉ የተመደበው ከኦሮሚያ ክልል ለሚመረጡ ተወካዮች ነው።  አሁን በፓርላማ የሚገኙት 170 የኦሮሚያ ክልል ተወካዮች፤ በ2013ቱ ምርጫ ከተካሄደባቸው 170 የምርጫ ክልሎች የተመረጡ ናቸው። ከእነዚህ ተመራጮች ውስጥ ከሶስት ተወካዮች በስተቀር፤ 167 ያህሉ ብልጽግና ፓርቲን ወክለው ወደ ፓርላማ የገቡ ናቸው።

ከገዢው ፓርቲ ውጪ የሆኑት ሶስት ተመራጮች፤ በግል ተወዳድረው የተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑ ናቸው። ከእነዚህ ተወካዮች ውስጥ ዶ/ር ዲማ ነገዎ እና ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ የተመረጡት ከኢሉ አባቦር ዞን ነው። የምስራቅ ሐረርጌ ዞንን በመወከል በግል ተወዳድረው ፓርላማውን የተቀላቀሉት አቶ ጋላሳ ዲልቦ፤ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)