ህወሓት ከሽብርተኝነት መዝገብ ተሰረዘ

⚫ 61 የፓርላማ አባላት የውሳኔ ሃሳቡን ተቃውመዋል

በሃሚድ አወል

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከሽብርተኝነት መዝገብ መሰረዙን፤ 61 የፓርላማ አባላት ተቃወሙ። አምስት የፓርላማ አባላትም ድምጽ ከመስጠት ታቅበዋል።

የፓርላማ አባላቱ ተቃውሞ እና ድምጸ ተዐቅቦ የተመዘገበው፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በህወሓት ላይ አስተላልፎት የነበረውን የሽብርተኝነት ፍረጃ ለመሰረዝ ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 13፤ 2015 ባካሄደው “ልዩ ጉባኤ” ላይ ነው። 280 የፓርላማ አባላት በተገኙበት በዛሬው “ልዩ ጉባኤ” በመንግስት ተጠሪ የቀረበው ህወሓትን ከሽብርተኝነት የመሰረዝ የውሳኔ ሃሳብ፤ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካሉት 547 መቀመጫዎች፤ በተቃዋሚ ፓርቲዎች እና በግል ተመራጮች የተያዙት 16ቱ ብቻ ናቸው። ገዢው ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ መቀመጫውን በያዘበት ፓርላማ ያሉ ተወካዮችን፤ ከዛሬው “ልዩ ጉባኤ” አንድ ቀን አስቀድሞ ሰብስቦ ውይይት ቢያካሄድም ከራሱ አባላት ጭምር ተቃውሞን ከማስተናገድ አልዳነም። 

የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን በተገኙበት በትላትናው ስብሰባ ላይ፤ ህወሓትን ከአሸባሪነት የመሰረዝ አስፈላጊነት በተመለከተ ሰፋ ያሉ ማብራሪያዎች ቀርበው እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል። በዚሁ የውይይት መድረክ፤ “ህወሓትን ከአሸባሪነት ከተሰረዘ በኋላ ምን ማስተማመኛ አለ?” የሚለውን ጨምሮ ስጋት ያዘሉ ጥያቄዎች ቀርበው ነበር ተብሏል። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

በዛሬው የፓርላማ ልዩ ጉባኤም በተመሳሳይ መልኩ፤ ከገዢው ፓርቲ የፓርላማ ተመራጮች “ጠንከር ያሉ” አስተያየቶች መቅረባቸውን ስብሰባውን የታደሙ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከእነዚህ የፓርላማ ተመራጮች መካከል የሆኑ አንድ የብልጽግና ፓርቲ አባል፤ “የፖለቲካ መረጋጋት እና ደህንነት በጣም በአሳሳቢነት ላይ ባለበት ሰዓት፤ የህወሓትን አሸባሪነት አንስቶ ወደ  ስርዓቱ ማስገባት ለመንግስትም አደጋ ነው ብዬ የራሴን ምክረ ሃሳብ እሰጣለሁ” ብለዋል። 

“መሬት ላይ ያሉ ልንቀርፋቸው የሚገቡ በርካታ ችግሮች አሉ” ያሉት እኚሁ የፓርላማ አባል፤ “ ‘አሁን ህዝቡስ ከእኛ ጋር ነው ወይ’? የሚለውን ጥያቄ መንግስት ማየት ያለበት ይመስለኛል” ሲሉ መቅደም ያለበት ነገር መኖሩን በአጽንኦት ተናግረዋል።  “የህዝብ ድጋፍ በደንብ ሳይኖረን ይኼንን አሸባሪ ቡድን ወደ ስርዓቱ ውስጥ መክተት ሁለት ዕጣ ፈንታ አለው። አንድ – መንግስት ስልጣኑን ለአሸባሪዎች መስጠት፤ ሁለት – ኢትዮጵያን ወደ ተለየ ቀውስ መስደድ” ሲሉም ውሳኔው ይኖረዋል ያሉትን ውጤት ለፓርላማው አስረድተዋል።

በፓርላማው የመንግስት ተጠሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ያቀረቡትን የውሳኔ ሃሳብ የተቃወሙት የገዢው ብልጽግና ፓርቲ አባል ግን እኒህ አባል ብቻ አይደሉም። ሌላ አንዲት የብልጽግና ፓርቲ ተመራጭም፤ ህወሓትን ከአሸባሪነት መሰረዝ “ጊዜው አይደለም። ቆም ብለን ማሰብ መቻል አለብን” ሲሉ ተደምጠዋል። የፓርላማ አባሏ፤ ከውሳኔው በፊት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት “ዝርዝር ሪፖርት ለፓርላማው ሊቀርብ ይገባል። የስምምነቱ እያንዳንዱ ነጥብ የት እንደደረሰ መገምገም አለበት” ሲሉ በቅድሚያ መደረግ ያለበትን ጉዳይ አመልክተዋል።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ከትጥቅ አፈታት ጋር በተያያዘም የተወካዮች ምክር ቤት አባሏ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። “እንደ አንድ የምክር ቤት አባል ‘ምን ያህል [መሳሪያ] መውረድ ነበረበት?’ ‘ምን ያህል ወረደ?’ ብሎ ህዝብ ቢጠይቀኝ እኔ መልስ የለኝም። በቂ መረጃ አልተሰጠኝም” ብለዋል ተመራጯ። ሌላ ሶስተኛ የገዢው ፓርቲ አባልም በተመሳሳይ የመንግስት ተጠሪው ያቀረቡትን ውሳኔ ሃሳብ “ወቅቱን ያልጠበቀ” ሲሉ ነቅፈውታል። 

ከብልጽግና ፓርቲ አባላት በተጨማሪ የተቃዋሚ ፓርቲ ተመራጮችም በዛሬው ስብሰባ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተመራጩ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ “የፌደራል መንግስቱ ከሞላ ጎደል በሆደ ሰፊነት የሚጠበቅበትን ነገር እያደረገ ቢሆንም፤ በትህነግ ወይም በትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር በኩል ግን የሰላም ስምምነቱ እየተተገበረ ነው የሚል እምነት የለንም” ሲሉ የፓርቲያቸውን አቋም አስታውቀዋል። 

“ከሽብር እና ከጦርነት ፖለቲካ የመስራት ባህሪ ባልተቀየረበት ሁኔታ፤ TPLFን ከሽብር list ማንሳት ታሪካዊ ስህተት ነው ብዬ አስባለሁ” ሲሉም  ዶ/ር ደሳለኝ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። የአብኑ የፓርላማ ተወካይ በአስተያየታቸው ማሳረጊያ ላይ “በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት TPLF የገባውን ቁርጠኝነት መፈጸም አለመፈጸሙ በአግባቡ ተረጋግጦ” ከሽብርተኝነት እንዲሰረዝ ጠይቀዋል። የህወሓት “ቁርጠኝነት” “ገለልተኛ በሆኑ እና ፓርላማው በሚያቋቁመው አካል እንዲጣራ” ሲሉም ተጨማሪ ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዩ በዚሁ ንግግራቸው “መብራራት አለባቸው” ያሏቸውን ጉዳዮችንም አንስተዋል። “ህወሓትን ከሽብርተኝነት ማንሳት ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ ይችላል ወይ?” የሚል ጥያቄ ያነሱት ዶ/ር ደሳለኝ፤ ምክር ቤቱ የውሳኔ ሀሳቡን “ለሌላ ጊዜ እንዲሻገር በተቃውሞ ውድቅ እንዲያደርገው መጠየቅ እፈልጋለሁ” ብለዋል።

የተቃዋሚው የጌዴኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ጌሕዴድ) ተመራጭ አቶ አለሳ መንገሻ በበኩላቸው፤ የሰላም “ስምምነቱ አተገባበር ግልጽ ባልሆነበት፣ ከህዝቡ በርካታ ጥያቄ እየተነሳ ባለበት በዚህ ጊዜ፤ ይኼ ውሳኔ ሃሳብ ጊዜውን የጠበቀ ነው ብለን አናምንም” የሚል የተቃውሞ አስተያየት ሰጥተዋል። ህወሓት ከአሸባሪነት ሊሰረዝ የሚገባው፤ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አተገባባር ሪፖርት ለፓርላማው ከቀረበ በኋላ መሆን እንዳለበት አቶ አለሳ አክለዋል።  

ሶስት ሰዓታት በወሰደው በዛሬው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ልዩ ጉባኤ”፤ የፓርላማ አባላት ግማሽ ያህሉን ጊዜ ወስደው ጥያቄ እና አስተያየታቸውን አቅርበዋል። እድል ካገኙ 14 የፓርላማ አባላት መካከል ሰባቱ፤ የህወሓትን ከሽብርተኝነት የመሰረዝ ውሳኔ ሃሳብን ተቃውመው አስተያየት ሰጥተዋል። የሃሳቡ ተቃዋሚዎች በተደጋጋሚ ሲያነሱት የነበረው ጉዳይ፤ ህወሓትን ከሽብርተኝነት ዝርዝር ውስጥ ከመሰረዝ በፊት “የሰላም ስምምነቱ በህወሓት በኩል ሙሉ በሙሉ መተግበር አለበት” የሚለው ነው።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የውሳኔ ሃሳቡን ደግፈው የተናገሩ የፓርላማ አባላት በበኩላቸው፤ የሽብርተኝነት ፍረጃው መነሳት “የሰላም ስምምነቱን ዘላቂ ያደርገዋል” የሚል መከራከሪያ ሲያቀረቡ ተደምጠዋል። ይህ የፓርላማ አባላቱ ሃሳብ፤ ለጥያቄዎች ምላሽ ሲስጡ በነበሩት በፍትሕ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞትዮስም ተስተጋብቷል። የሽብርተኝነት ስያሜ ማንሳት፤ “ስምምነቱ ላይ ያሉት ነገሮች እንዳለ ተተግብረው አብቅተው፣ ማሳረጊያው ላይ የሚሆን ነገር ሳይሆን፤ ሌሎች ግዴታዎች እየተተገበሩ፣ አብሮ በሂደት ውስጥ መተግበር ያለበት፤ መፈጸም ያለበት ነገር ነው” ሲሉ ሚኒስትሩ አስረድተዋል። 

ከዶ/ር ጌደዮን በተጨማሪ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን በዛሬው ልዩ ጉባኤ ተገኝተው ለጥያቄዎች ማብራሪያዎች ሰጥተዋል። ህወሓት “ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀበት ምክንያት፤ በያዘው ርዕዮት አለም አይደለም። በያዘው የፖለቲካ ፕሮግራም አይደለም” ሲሉ በትላንትናው ስብሰባ ላይ ያነሱትን ሃሳብ በድጋሚ አንስተዋል። አቶ ሬድዋን በትላንትናው ስብሰባ፤ ህወሓት በአሸባሪነት የተፈረጀው “የህወሓትን አስተሳሰብ እና ሰዎች ስለምንጠላ አይደለም” ማለታቸውን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች መግለጻቸው አይዘነጋም።

የኢትዮጵያን መንግስት ወክለው የፕሪቶሪያውን ስምምነት የተፈራረሙት አቶ ሬድዋን፤ በዛሬው ጉባኤ ህወሓት በአሸባሪነት የተፈረጀበትን ምክንያት ለፓርላማ አባላት አስታወሰዋል። የሽብርተኝነት ፍረጃው “የህወሓትን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቅሞች ለመቆጣጠር፤ በተለይም ለብሔራዊ መረጃ [ደህንነት አገልግሎት] እና ለፌደራል ፖሊስ የተሻለ አቅም ለመስጠት ብቻ ነው” ብለዋል።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ህወሓት ከሽብርተኝነት ዝርዝር የተሰረዘበትን የውሳኔ ሃሳብ ለፓርላማ አባላት በንባብ ያሰሙት የመንግስት ተጠሪው አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ህወሓትን ከአሸባሪነት ስያሜ ለማንሳት ውሳኔውን ያሳለፈበትን ምክንያት አስረድተዋል። “ህወሓት በአሁኑ ወቅት እንደ ድርጅት የሽብር ወንጀል መፈጸሙን ያቆመ እና በቀጣይም በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ ካደረጉት ድርጊቶች ለመታቀብ የገባውን ስምምነት ከግንዛቤ በማስገባት” ህወሓት ከአሸባሪነት ስያሜ እንዲነሳ መወሰኑን ገልጸዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሓትን አሸባሪነት የፈረጀው፤ ከሁለት ዓመታት ገደማ በፊት በሚያዚያ 2013 ዓ.ም መጨረሻ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ነበር። በዚሁ ስብሰባ ላይ፤ ራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ብሎ የሚጠራውን እና በመንግስት “ኦነግ ሸኔ” በሚል የሚታወቀው ታጣቂ ቡድንም በአሸባሪነት መፈረጁ ይታወሳል።   

ሁለቱ አካላት በአሸባሪነት እንዲፈረጁ ለፓርላማው የውሳኔ ሀሳብ የቀረበው በሚኒስትሮች ምክር ቤት በተላለፈው ውሳኔ አማካኝነት ነው። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ህወሓት እና “ሸኔ” በሽብር እንዲፈረጁ ውሳኔ ባስተላለፈበት ስብሰባው፤ ሁለቱ አካላት “የሽብር ወንጀልን ዓላማቸው አድርገው” እንደሚንቀሳቀሱ እና “የሽብር ተግባር መፈጸም የድርጅቶቹ ጠቅላላ መገለጫ” መሆኑን ጠቅሶ ነበር። የሁለቱ ቡድኖች የስራ አመራር ወይም ውሳኔ ሰጪ አካላት፤ የሽብር ወንጀሉን “አምነው የተቀበሉት ወይም አፈጻጸሙን እየመሩት” መሆኑንም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በወቅቱ መግለጹ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ዝርዝር መረጃ ታክሎበታል]