የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ያቋቋመው መርማሪ ኮሚሽን፤ የኢትዮጵያ መንግስትን ወቀሰ  

በተስፋለም ወልደየስ

በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመመርመር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ያቋቋመው ኮሚሽን፤ የመርማሪ ቡድን ወደ ሀገሪቱ ለመላክ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም “የኢትዮጵያ መንግስት አልፈቀደልኝም” ሲል ወቀሳ አቀረበ። የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ ኮሚሽኑ “በተቀመጠለት ኃላፊነት መሰረት ገንቢ በሆነ መልኩ አብሮ ለመስራት ዝግጁ አልነበረም” ሲል ተችቷል።

የመርማሪ ኮሚሽኑ ወቀሳ እና የኢትዮጵያ መንግስት ምላሽ የተደመጠው፤ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ነው። ባለፈው የካቲት ወር አጋማሽ የተጀመረው እና እስከ መጋቢት 26፤ 2015 በሚዘልቀው በዚሁ ዓመታዊ ጉባኤ፤ የበርካታ ሀገራት የሰብዓዊ መብት ይዞታን የተመለከቱ ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።

ትላንት ማክሰኞ መጋቢት 12፤ 2015 በነበረው የምክር ቤቱ ውሎ፤ የኢትዮጵያ እና ቬንዙዌላን ወቅታዊ ሁኔታ የተመለከቱ ማብራሪያዎች ቀርበዋል። ኢትዮጵያን የተመለከተውን ማብራሪያ ለምክር ቤቱ በንባብ ያሰሙት፤ ሶስት አባላት ያሉትን መርማሪ ኮሚሽን በሊቀመንበርነት የሚመሩት ታንዛኒያዊው መሐመድ ቻንዴ ኦትማን ናቸው። 

ኦትማን በዚሁ ማብራሪያቸው፤ መርማሪ ኮሚሽኑ ለምክር ቤቱ የመጀመሪያውን ሪፖርት ካቀረበበት ካለፈው መስከረም ወር ወዲህ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ “በጉልህ መሻሻሉን” ተናግረዋል። በሀገሪቱ ለሁለት ዓመት የተካሄደውን ግጭት ለማቆም በኢትዮጵያ መንግስት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ መካከል ባለፈው ጥቅምት 23 ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ባሉ አካባቢዎች ግጭቶች በሚገባ መቀነሳቸውን እና ይህም እስካሁን ድረስ የዘለቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተወሰዱ ተከታታይ እርምጃዎችን የመርማሪ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር በበጎነት አንስተዋል። ምንም እንኳ እነዚህ እርምጃዎች “በአንጻራዊነት የአካባቢውን የጸጥታ ሁኔታ እንዲሻሻል ቢያደርጉም፤ ከጥቅምት  2013 በኋላ በኢትዮጵያ የተፈጸሙ ጥሰቶችን ክብደት እና መጠን በፍጹም ሊረሱ አይገባም” ሲሉ ኦትማን አጽንኦት ሰጥተዋል።

መርማሪ ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ባቀረበው ሪፖርት፤ በኢትዮጵያ በጥቅምት 2013 ውጊያ ከተቀሰቀሰ በኋላ በግጭቱ የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች የጦር ወንጀሎች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ አሳማኝ ምክንያቶችን ማግኘቱን ሊቀመንበሩ በማብራሪያቸው አስታውሰዋል። ኮሚሽኑ የኤርትራ ኃይሎች በኢትዮጵያ ግዛት ፈጽመውታል የተባሉትን ጨምሮ በሁሉም ወገኖች የተፈጸሙ ጥሰቶችን መመርመር መቀጠሉንም ጠቁመዋል። ምርመራው ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ተፈጽመዋል የተባሉ ብርቱ ጥሰቶችን እና በደሎችን የሚያካትት መሆኑንም አክለዋል።

ኮሚሽኑ አብዛኛዎቹን ስራዎቹን እያከናወነ የሚገኘው ድርጊቱ ከተፈጸመበት ቦታ ርቆ መሆኑን የጠቀሱት ኦትማን፤ ይህም የሆነበት ምክንያት የኢትዮጵያ መንግስት የኮሚሽኑ የመርማሪ ቡድን ወደ ሀገሪቱ እንዲገባ ባለመፍቀዱ መሆኑን አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ከመርማሪ ኮሚሽኑ ጋር ላለመተባበር ያሳለፈውን ውሳኔ መልሶ እንዲያጤንም ሊቀመንበሩ ጠይቀዋል። 

ለዚህ የኮሚሽኑ ወቀሳ ምላሽ የሰጡት፤ ጄኔቫ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጽህፈት የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ በመሆን በቅርቡ የተሾሙት አቶ ጸጋአብ ክበበው ናቸው። አቶ ጸጋአብ በዚሁ ምላሻቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከመርማሪ ኮሚሽኑ ጋር በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ማዕቀፎች ላይ ለመነጋገር አባላቱን ወደ አዲስ አበባ ጭምር በመጋበዝ ማነጋገሩን አስታውሰዋል። 

መርማሪ ኮሚሽኑ የሚያከናወናቸው ስራዎች፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኢትዮጵያ በጦርነቱ ወቅት ተፈጽመዋል የተባሉ ጥሰቶችን አስመልክቶ በጋራ ባደረጉት ምርመራ ላይ ተመስርቶ የሚደረግ መሆን እንዳለበት፤ ኢትዮጵያ አቋሟን ስታስታውቅ ቆይታለች። ይህንኑ የኢትዮጵያን አቋም አቶ ጸጋአብ በትላንትናው ስብሰባ ላይ አስተጋብተዋል። መርማሪ ኮሚሽኑ “በተቀመጠለት ኃላፊነት መሰረት ገንቢ በሆነ መልኩ አብሮ ለመስራት ዝግጁ አልነበረም” ሲሉም ተችተዋል። 

በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጸሙ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና በደሎችን የሚመረምረው ዓለም አቀፍ ኮሚሽን በተቋቋመበት ወቅት፤ አምስት ኃላፊነቶች ተሰጥተውት ነበር። ኮሚሽኑ በትግራይ ውጊያ ከተቀሰቀሰበት ጥቅምት 24፤ 2013 ዓ.ም ጀምሮ፤ በሁሉም ወገኖች ተፈጽመዋል የሚባሉ የዓለም አቀፍ ሕጋግት ጥሰቶችን የመመርመር ኃላፊነት ተጥሎበታል። ኮሚሽኑ በሚያደርገው ምርመራ፤ የደረሰባቸውን ሃቆች እና ሁኔታዊ ማስረጃዎች የመሰነድ ሚናም አለው። 

መርማሪ ኮሚሽኑ የሰነዳቸውን ማስረጃዎች አጥፊዎችን በመለየት፤ ተጠያቂ ለማድረግ በመካሄድ ላይ ላሉ እና ወደፊትም ሊደረጉ ለሚችሉ ጥረቶች ግብዓት እንዲሆኑ እንደሚያደርግ በተቋቋመበት ወቅት ተገልጿል። ኮሚሽኑ፤ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እና ዕርቅ ማውረድን ጨምሮ እንደ አስፈላጊነቱ ስለ ሽግግር ፍትሕ ለኢትዮጵያ መንግስት ቴክኒካዊ ድጋፍ የመስጠት ኃላፊነትም አለበት። 

የሽግግር ፍትሕን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት እያደረጋቸው ያላቸው እንቅስቃሴዎች፤ በትላንትናው ስብሰባ ተሳታፊዎች ዘንድ በበጎ እርምጃነት ተደጋግሞ ተወስቷል። የጄኔቫውን ስብሰባ በስፍራው በአካል በመገኘት የታደሙት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ የሽግግር ፍትሕ አማራጮችን በተመለከት በብሔራዊ ደረጃ የተጀመረውን ምክክር ተቋማቸው በመልካም እንደሚቀበለው ተናግረዋል። “ተጠያቂነት እና የሽግግር ፍትሕ፤ የሰላም ሂደቱ አንኳር ጉዳይ ሆነው መቆየት ይገባቸዋል” ሲሉም ተደምጠዋል። 

አንድ ሰዓት ከ15 ደቂቃ በወሰደው ኢትዮጵያን በተመለከተው የትላንቱ ውይይት፤ የአውሮፓ ህብረት እንዲሁም 26 ሀገራት በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አቋም አሰምተዋል። ኖርዌይ፤ የኖርዲክ እና ባልቲክ ሀገራትን በመወከል አቋም እና አስተያየቷን ያቀረበች ሲሆን፤ ኮትዲቯር በበኩሏ የአፍሪካ ሀገራትን በመወከል ተመሳሳዩን አድርጋለች። አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ 10 ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የመናገር ዕድል አግኝተዋል። 

ሁለቱ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ተሟጋች ድርጅቶች፤ የመርማሪ ኮሚሽኑ ስራ እንዲቋረጥ የኢትዮጵያ መንግስት የሚያደርገው ግፊት በብርቱ ሲተችቱ ቆይተዋል። በትላትናው ስብሰባ ወቅትም የሁለቱ ድርጅቶች ተወካዮች ይህንኑ ጉዳይ በማንሳት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። በዚሁ ስብሰባ ላይ የተሳተፉት የቻይና ተወካይ በበኩላቸው፤ በ“ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ገብቷል” ያሉትን መርማሪ ኮሚሽን በመቃወም ጠንከር ያለ አስተያየት አስደምጠዋል። 

መርማሪ ኮሚሽኑ የተቋቋመው ከኢትዮጵያ መንግስት እውቅና ውጪ፣ በኃይል ግፊት በማድረግ መሆኑን የጠቀሱት የቻይናው ዲፕሎማት፤ ይህ አካሄድ “ውስብስብ የሆነውን የኢትዮጵያን ጉዳይ የበለጠ ያባብሰዋል” ብለዋል። የተወሰኑ ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ የጣሉት ማዕቀብም፤ የህዝቦቿን ሰብአዊ መብት የሚጋፋ መሆኑንም የቻይናው ተወካይ ገልጸዋል። ማዕቀቡ ወዲያውኑ እንዲነሳ ጠይቀዋል።

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መርማሪ ኮሚሽኑን ለማቋቋም በታህሳስ 2014 የውሳኔ ሃሳብ ባቀረበበት ወቅት፤ ቻይናን ጨምሮ 15 ሀገራት ተቃውመውት ነበር። ኮሚሽኑ በተቋቋመበት ወቅት ተሰጥቶት የነበረው አንድ ዓመት የስራ ዘመን፤ ለተጨማሪ አንድ ዓመት የተራዘመለት ባለው መስከረም ወር መጨረሻ ነበር። ተቀማጭነቱን በኡጋንዳ ኢንቴቤ ያደረገው ይኸው ኮሚሽን፤ አጠቃላይ የምርመራ ሪፖርቱን በመጪው መስከረም ለተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። 

መርማሪ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ በኋላ በአባልነት ተሹመው ከነበሩ ሶስት አባላት ውስጥ፤ አሁንም በአባልነት የቀጠሉት አሜሪካዊው የህግ ባለሙያ ስቴቨን ራትነር ብቻ ናቸው። መርማሪ ኮሚሽኑን ለጥቂት ጊዜያት በሊቀመንበርነት የመሩት ጋምቢያዊቷ ፋቱዋ ቤንሱዳ፤ በሀገራቸው ሌላ ሹመት በማግኘታቸው ኃላፊነታቸውን በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቃቸው ይታወሳል። እርሳቸውን በመተካት የሊቀመንበርነት ቦታውን ተረክበው የነበሩት ኬንያዊቷ የህግ ባለሙያ ካሪ ቤቲ ሙሩንጊም እንዲሁ፤ ከኮሚሽኑ ኃላፊነታቸው እና አባልነታቸው መሰናበታቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)