የትግራይ ክልል መንግስት መስሪያ ቤቶች፤ ለሰራተኞቻቸው ብድር እንዲሰጡ ተፈቀደላቸው 

በአማኑኤል ይልቃል

በትግራይ ክልል የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ እስከሚከፈላቸው ድረስ ከመስሪያ ቤቶቻቸው ብድር እንዲወስዱ ተፈቀደላቸው። የክልሉ መስሪያ ቤቶች ለሰራተኞቻቸው ማቅረብ የሚችሉት ከፍተኛ ብድር፤ አራት ሺህ ብር እንደሆነ ተገልጿል። 

የትግራይ ክልል መንግስት ሰራተኞች የመከላከያ ሰራዊት ክልሉን ለቀቆ ከወጣበት ከሰኔ 2013 ዓ.ም አንስቶ፤ ላለፉት 21 ወራት ደመወዝ አልተከፈላቸውም። የፌደራል መንግስት እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ባደረጉት ስምምነት መሰረት ሊቋቋም ይገባ የነበረው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግስት እስካሁን ባለመቋቋሙ፤ የገንዘብ ሚኒስቴር ወደ ክልሉ ገንዘብ አለመላኩን ባለፈው ሳምንት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቆ ነበር።

እስካሁን በጀት ያልተለቀቀላቸው የክልሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፤ በባንክ ሂሳባቸው ውስጥ ካለው ገንዘብ ውስጥ ለሰራተኞቻቸው ብድር ለመስጠት ጥያቄ ማቅረባቸውን እና ጥያቄያቸው ተቀባይነት ማግኘቱን የክልሉ የገንዘብ እና ፕላን ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አረጋዊ ገብረሚካኤል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ቢሮው በክልሉ ለሚገኙ ለሁሉም የዞን፣ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም መስሪያ ቤቶች ባለፈው ሳምንት ሐሙስ መጋቢት 7፤ 2015 በጻፈው ደብዳቤ፤ ብድር እንዲሰጡ መፍቀዱን ኃላፊው አስታውቀዋል።

የዶ/ር አረጋዊ ፊርማ ያረፈበት ይኸው ደብዳቤ፤ በክልሉ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች “ሙሉ ለሙሉ ባልተከፈተው ከበባ” ምክንያት አሁንም ችግር ውስጥ መሆናቸውን አትቷል። ለክልሉ የመንግስት ተቋማት  ደመወዝ መክፈል የሚያስችል በጀት እስከሚመደብ ድረስም፤ መስሪያ ቤቶቹ በባንክ ሂሳባቸው ውስጥ ካለው ገንዘብ ላይ ከአራት ሺህ ብር ያልበለጠ ብድር ለሰራተኞቻቸው እንዲያቀርቡ እንደተፈቀደ በደብዳቤው ላይ ሰፍሯል።

መስሪያ ቤቶቹ የሚሰጡት ብድር በቀጣይ ለሰራተኞቹ ከሚከፈል “የተስተካከለ ደመወዝ” ላይ የሚታሰብ እንደሆነም ተጠቅሷል። የተፈቀደውን የብድር መጠን ለሰራተኞቻቸው ለማቅረብ የሚያስችል ገንዘብ የሌላቸው የክልሉ መዋቅሮች እና መስሪያ ቤቶች፤ “ገንዘብ ካላቸው አካላት ተበድረው” መስጠት እንደሚችሉም በደብዳቤው ተመላክቷል።

የትግራይ ክልል የገንዘብ እና ፕላን ቢሮ ከዚህ በተጨማሪም የግንቦት እና ሰኔ 2013 ዓ.ም ደመወዝን ሳይወስዱ የባንክ አገልግሎት ለተቋረጠባቸው ሰራተኞች ደመወዝ እንዲከፈላቸው መፍቀዱን በደብዳቤ አስታውቋል። ይህንን ክፍያ የሚፈጽሙ የክልሉ መስሪያ ቤቶች “አስፈላጊውን ማጣራት እና ጥንቃቄ” እንዲያደርጉ ቢሮው በደብዳቤው አሳስቧል።

የፌደራል መንግስት በ2015 በጀት ዓመት ለክልሎች ለመስጠት እቅድ ከያዘው 209.3 ቢሊዮን ብር ድጋፍ  ውስጥ፤ 12.4 ቢሊዮን ብር ያህሉን የመደበው ለትግራይ ክልል ነው። የገንዘብ ሚኒስቴር ይህንን የድጎማ በጀት እስካሁን ወደ ትግራይ ክልል መላክ ባይጀምርም፤ በክልሉ በሚገኙ አራት የፌደራል መንግስት ዩኒቨርስቲዎች ስር ላሉ ሰራተኞች የሶስት ወር ደመወዝ ክፍያ የሚሆን ገንዘብ ባለፈው ሳምንት ማስተላለፉ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)