በፍርድ ቤት ውሳኔ ለባለቤቶች የሚወሰኑ የቀበሌ ቤቶች እየጨመሩ በመምጣታቸው፤ ጉዳዩ መፍትሔ እንዲፈለግለት ጥያቄ ቀረበ 

በአማኑኤል ይልቃል

በደርግ ጊዜ የተወረሱ የቀበሌ ቤቶችን አስመልክቶ ለፍርድ ቤት ለሚቀርቡ አቤቱታዎች እና ለሚሰጡ ውሳኔዎች “መፍትሔ እንዲፈለግ” የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ጥያቄ አቀረበ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቀበሌ ቤቶችን በተመለከተ ለፍርድ ቤቶች በሚቀርቡ አቤቱታዎች ምክንያት፤ ቤቶቹ “ከመንግስት እጅ” እየወጡ መሆኑን ቢሮው ገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ይህንን ጥያቄ ያቀረበው፤ ለከተማ እና መሰረት ልማት ሚኒስቴር፣ ለአዲስ አበባ ከንቲባ ጽህፈት ቤት እንዲሁም ለከተማዋ ፍትህ ቢሮ ባለፈው ሰኞ መጋቢት 11፤ 2015 በጻፈው ደብዳቤ ነው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ይህ ባለ አራት ገጽ ደብዳቤ፤ በቀበሌ ቤቶች ላይ “የኔ ነው አልተወረሰብኝም፤ መንግስት ያለ አግባብ ነው የያዘብኝ” የሚሉ ክርክሮች ከቀን ቀን እየጨመሩ መጥተዋል ይላል።  

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስሩ 153 ሺህ ገደማ የመንግስት ቤቶች የሚያስተዳድር ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 135 ሺህ የሚጠጉት በተለምዶ “የቀበሌ ቤት” የሚባሉት ናቸው። እነዚህ ቤቶች በመንግስት ይዞታ ስር የገቡት፤ የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በሐምሌ 1967 ዓ.ም ባወጣው የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት አዋጅ አማካኝነት እንዲሁም በተያያዥ ምክንያቶች ከግለሰቦች ተነጥቀው የመንግስት ንብረት እንዲሆኑ ከተደረጉ በኋላ ነው።

በተለምዶ “የቀበሌ ቤቶች” ተብለው የሚጠሩትን እነዚህን ንብረቶች፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “ከአርባ ዓመት በላይ እያከራየ” ሲጠቀምባቸው ቢቆይም እነርሱን የተመለከቱ አቤቱታዎች ለፍርድ ቤቶች ሲቀርቡ ቆይተዋል። አቤቱታዎች ከቀረበባቸው ክፍለ ከተማዎች ውስጥ፤ የካ፣ ጉለሌ፣ ቂርቆስ እና ንፋስ ስልክ እንደሚገኙበት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ የህግ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ሽፈራው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ቢሮው የቀበሌ ቤቶችን ጋር በተመለከተ ሲከራክርባቸው ከነበረባቸው መዝገቦች ውስጥ በአምስቱ “በቅርቡ መሸነፉን” አቶ ዮናስ ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤት በተላለፉ ውሳኔዎች፤ በየካ እና ጉለሌ ክፍለ ከተማዎች፤ ርክክብ የተፈጸመባቸው ቤቶች እንዳሉም ጠቅሰዋል። የከተማ አስተዳደሩ በመሰል ውሳኔዎች የቀበሌ ቤቶችን ለአቤቱታ አቅራቢዎች ቢያስረክብም፤ ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን በማየት “አከራክረው የማስወሰን ስልጣን የላቸውም” የሚል አቋም አለው። 

የከተማው ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ በጻፈው ደብዳቤም ይህንኑ አቋም አስተጋብቷል። ቢሮው ከቀበሌ ቤቶች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን የማየት ስልጣን በአዋጅ ለቀድሞው “የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ብቻ” የተሰጠ እንደሆነ በደብዳቤው ላይ ጠቅሷል። በ1987 ዓ.ም የተቋቋመው “የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ”፤ በደርግ ጊዜ የተወረሱ ቤቶችን በተመለከተ የሚቀርብለትን ማስረጃ እየመረመረ፣ “ከህግ ውጪ ተወርሰዋል” ያላቸውን እንዲመለሱ ሲያደርግ ቆይቷል። 

ተቋሙ እስከ ሚያዝያ 2000 ዓ.ም ድረስ ይህንን ስራ ሲያከናውን ከቆየ በኋላ፤ የፌደራል መንግስት የቀበሌ ቤቶችን የተመለከተ ሌላ አዋጅ አውጥቷል። “ከአዋጅ ውጪ የተወሰዱ ንብረቶችን ለማስመለስ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን የመቀበያ ጊዜ ገደብ ለመወሰን” በሚል የወጣው ይህ አዋጅ፤ እነዚህ ቤቶች የተመለከቱ ጥያቄዎች በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ካልቀረቡ በይርጋ እንደሚታገዱ ደንግጓል። በዚህም መሰረት ከሐምሌ 2000 ዓ.ም ጀምሮ የቀበሌ ቤቶችን የተመለከቱ ጥያቄዎች በአዋጁ የይርጋ እግድ ተጥሎባቸዋል።

ይሁንና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት “ለማይንቀሳቀስ ንብረት የሚደረግ የመፋለም ክስ ይርጋ እንደማያግደው” ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ፤ የቀበሌ ቤቶችን የተመለከቱ አቤቱታዎች በፍርድ ቤት በመቅረብ ላይ ይገኛሉ። አቤቱታዎቹን የሚመለከቱት ፍርድ ቤቶችም፤ የቀበሌ ቤቶቹ በመንግስት መወረሳቸውን የሚያሳይ “ቅፅ 003” የተባለ ሰነድ እንዲቀርብ እየጠየቁ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ የጻፈው ደብዳቤ ያትታል።

መንግስትን ወክለው በፍርድ ቤቶች የሚከራከሩ ዐቃብያነ ህግ፤ ለአብዛኛዎቹ ቤቶች የተጠየቁትን ሰነድ ማግኘት አለመቻላቸውን ደብዳቤው ያስረዳል። ይህ የሆነበት ምክንያትም “መንግስት በተለያየ ጊዜ በገጠሙት ፈተናዎች ምክንያት [ሰነዶቹ] ከማህደራቸው በመውጣታቸው” መሆኑን ያብራራል። “ይህን ፍርድ ቤቶች ከግንዛቤ ማስገባት ሲገባቸው፤ የተወረሰበት ቅፅ በሚል፤ [መንግስት] ለረጅም ጊዜ በእጁ አድርጎ የሚያስተዳድራቸው ቤቶች ላይ ለግለሰቦች እንዲያስረክብ ውሳኔ እየተሰጠ ይገኛል” ሲልም ቢሮው በፍትህ ተቋማት ላይ ወቀሳ አሰምቷል።

በተጨማሪም በተመሳሳይ መልኩ በቀረበ አቤቱታ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያጸደቀውን የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ከግምት ውስጥ ሳይገባ ውሳኔዎች እየተላለፉ እንደሚገኙ ደብዳቤው አመልክቷል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከዚህ ቀደም ያጸደቀው ውሳኔ፤ መንግስት ለረጅም ጊዜ በእጁ አድርጎ የያዘው ቤት እንደተወረሰ ይቆጠራል” የሚል አንደምታ ያለው ነው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ የህግ ባለሙያ፤ የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔውን በመጥቀስ የቢሮውን መከራከሪያ ይደግፋሉ።

የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ “አስገዳጅ እና በሁሉም ፍርድ ቤቶች የሚተገበር” መሆኑን የገለጹት የህግ ባለሙያው፤ የቀበሌ ቤቶችን የተመለከተ አቤቱታ የቀረበላቸው ፍርድ ቤቶች ይህንን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደነበረባቸው አስረድተዋል። የህግ ባለሙያው በሌላ መልኩ “እስከ ሐምሌ 2000 ዓ.ም ድረስ አቤቱታ ያላቀረቡ እና በዚህም ምክንያት ጥያቄያቸው በይርጋ የሚታገድ ሰዎች፤ በምን መልኩ ነው መብታቸውን ማስከበር የሚችሉት የሚለው አሁንም እንጥልጥል ላይ ያለ ክፍት የሆነ ጉዳይ ነው” ሲሉ የተለየ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ከቀበሌ ቤቶች ጋር በተያያዘ ላጋጠመው ተግዳሮት፤ ውይይት እንዲደረግ መጠየቁ “ችግር እንደሌለው” የሕግ ባለሙያው ያነሳሉ። ይሁንና ውይይቱ የፍርድ ቤቶችን ነጻነት የሚጋፋ አለመሆኑ ጥንቃቄ ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)