ኢትዮ ቴሌኮም የ23 ተቋማትን አገልግሎት በ“ቴሌብር” ማግኘት የሚያስችል መተግበሪያ ይፋ አደረገ   

በአማኑኤል ይልቃል

ኢትዮ ቴሌኮም “ቴሌብር” የተሰኘውን የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት መተግበሪያውን፤ ብዛት ያላቸው አገልግሎቶችን መስጠት ወደሚያስችል “ሱፐር አፕ” አሳደገ። አዲሱ የቴሌ ብር መተግበሪያ እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ራይድ፣ ዲኤስ ቲቪ የመሳሰሉ 23 የሌሎች አገልግሎት ሰጪዎች መተግበሪያዎችን በውስጡ የያዘ ነው።

ኢትዮ ቴሌኮም የቴሌብር መተግበሪያውን ወደ “ሱፐር አፕ” ማሳደጉን የሚያበስርበትን ስነ ስርዓት፤ ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 14፤ 2015 አዲስ አበባ በሚገኘው የሳይንስ ሙዚየም እያካሄደ ነው። ተቋሙ ወደ “ሱፐር አፕነት” ያሳደገውን የቴሌ ብር መተግበሪያ ያስተዋወቀው፤ “እልፍ ጉዳይ በአንድ መተግበሪያ” በሚል መሪ ቃል ነው።

በግንቦት 2013 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የተደረገው “ቴሌ ብር”፤ እስካሁን ድረስ 30 ሚሊዮን ገደማ ደንበኞችን እንዳፈራ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በማብሰሪያ ስነ ስርዓቱ ላይ ገልጸዋል። “ቴሌ ብር” በተያዘው በጀት ዓመት አጋማሽ ብቻ 33.8 ቢሊዮን ብር ዝውውር እንደተፈጸመበት ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ጀምሮ በ“ቴሌ ብር” አማካኝነት አነስተኛ ብድር መስጠት የጀመረው ኢትዮ ቴሌኮም፤ 1.4 ሚሊዮን ለሚሆኑ ደንበኞች እስካሁን ድረስ 2.1 ቢሊዮን ብር ብድር እንዳቀረበ ተገልጿል።

ዛሬ ይፋ የተደረገው “ቴሌብር ሱፐር አፕ” ይዟቸው ከመጣቸው ለውጦች ውስጥ አንዱ፤ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መተግበሪያዎችን በውስጡ መያዙ መሆኑን የኢትዮ ቴሌኮም የማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ታምራት ተስፋዬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ራይድ፣ ዲኤስ ቲቪ እና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚጠቀሙ ደንበኞች የእያንዳንዱን ተቋም መተግበሪያ ስልካቸው ላይ ሳይጭኑ በቴሌ ብር አማካኝነት አገልግሎቶቹን ማግኘት ይችላሉ። 

እስካሁን ድረስ 23 አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በቴሌ ብር ሱፐር አፕ ውስጥ መካተታቸውን ማርኬቲንግ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። አዲሱ የ”ቴሌብር” መተግበሪያ ለተለያዩ ተቋማት የሚደረጉ የገንዘብ ድጋፍ የማሰባሰብ ስራዎች (fundraising) ማከናወን የሚያስችል መሆኑንም አቶ ታምራት አክለዋል።

“ቴሌ ብር ሱፐር አፕ” ያካተተው ሌላኛው አገልግሎት “የታቀደ ክፍያ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ነው። ይህ አገልግሎት እንደ ወርሃዊ ሂሳብ ያሉ በየጊዜው የሚፈጸሙ ክፍያዎችን በእቅድ ውስጥ አስገብቶ፤ መተገብሪያው በራሱ ከሂሳብ ላይ ቆርጦ ክፍያ እንዲፈጸም ለማድረግ የሚያስችል ነው ተብሏል። የአዲሱ መተግበሪያ ሌላኛው አገልግሎት፤ ለብዙ ሰዎች በአንድ ጊዜ ክፍያ መፈጸም መሆኑን ማርኬቲንግ ዳይሬክተሩ አመልክተዋል። 

ዛሬ ይፋ የተደረጉት የቴሌ ብር የምዕራፍ አንድ አገልግሎቶች ሲሆኑ፤ በወራት ጊዜ ውስጥ በምዕራፍ ሁለት ሌሎች አገልግሎቶችንም ለማካተት መታቀዱን አቶ ታምራት ጠቁመዋል። በቀጣዩ ምዕራፍ ይካተታሉ ተብለው ከሚጠበቁ አገልግሎቶች ውስጥ አንዱ መተገበሪያው መልዕክት መለዋወጥ እንዲያስችል ማድረግ እንደሆነ የኢትዮ ቴሌኮም የማርኬቲንግ ዳይሬክተር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)