በጫሞ ሐይቅ ላይ በደረሰ የጀልባ መስጠም አደጋ የስምንት ሰዎች ህይወት አለፈ

በሃሚድ አወል

በደቡብ ክልል ጫሞ ሐይቅ ላይ በጀልባ ሲጓዙ የነበሩ ስምንት ሰዎች፤ ባጋጠማቸው የማዕበል አደጋ ምክንያት ሰጥመው ህይወታቸው ማለፉን የአማሮ ልዩ ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በአደጋው የሞቱ ሰዎችን ፍለጋ እስከ ዛሬ ከሰዓት ድረስ ቢቀጥልም፤ እስካሁን የተገኘ አስክሬን እንደሌለ ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።

የአማሮ ልዩ ወረዳ አልፋጮ ቀበሌ ነዋሪዎችን አሳፍሮ ወደ አርባ ምንጭ በመጓዝ ላይ በነበረው ጀልባ ላይ የመገልበጥ አደጋ የተከሰተው፤ ትላንት ቅዳሜ መጋቢት 16፤ 2015 ከሰዓት በኋላ መሆኑን የልዩ ወረዳው ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም አራጋው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በጫሞ ሐይቅ ላይ በነበረው ማዕበል፤ የጀልባውን ሹፌር ጨምሮ ስምንት ሰዎችን የጫነችው ባለሞተር ጀልባ “ወዲያው መስመጧን” አቶ ፍጹም አስረድተዋል። 

ፎቶ፦ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ፋይል

አደጋው መከሰቱ እንደታወቀ የተጎጂዎችን ህይወት ለማትረፍ ጥረት ቢደረግም፤ በጫሞ ሐይቅ ላይ በነበረው ከፍተኛ ማዕበል ምክንያት አለመሳካቱን የጽህፈት ቤት ኃላፊው አመልክተዋል። “ከአደጋው መድረስ በኋላ ከአርባ ምንጭ ከተማ በመጡ ዋናተኞች ጭምር ሕይወት ለማዳን ቢሞከርም፤ ነገር ግን በሰዓቱ የነበረው ማዕበል አላስቻለም” ብለዋል። በጫሞ ሐይቅ ላይ የነበረው ማዕበል ዛሬ ጠዋት “ጋብ” ማለቱንም አክለዋል።  

የሟቾችን አስክሬን ለማግኘት እየተደረገ ፍለጋ ከዛሬ ከጠዋት ጀምሮ “ተጠናክሮ መቀጠሉን” አቶ ፍጹም ገልጸዋል። የአርፋጮ ቀበሌ ነዋሪዎች በጫሞ ሐይቅ ዳርቻ ተሰባስበው የአስክሬን ፍለጋ እያከናወኑ መሆኑን አቶ አብነት አሳለ የተባለ የአካባቢው ነዋሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል። “ሁላችንም እዛው ሐይቅ ዳር ነው ያለነው። ‘ሐይቁ ራሱ የመትፋት ባህሪ አለው’ ስለሚባል እሱን እየጠበቅን ነው” ሲል በአካባቢው ያለውን ሁኔታ አስረድቷል። 

የአማሮ ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች ለንግድ እንዲሁም የተሻለ ህክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደ አርባምንጭ ከተማ በሚጓዙበት ወቅት፤ ከየብስ ትራንስፖርት ይልቅ የጀልባ መጓጓዣን እንደሚጠቀሙ የአካባቢው ነዋሪዎች እና የልዩ ወረዳው የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ይናገራሉ። የጀልባ ትራንስፖርት ለመመረጡ አንደኛው ምክንያት፤ ጫሞ ሐይቅን አቋርጦ አርባ ምንጭ ለመድረስ የሚፈጀው ጊዜ በተሽከርካሪ ከሚደረገው ይልቅ በግማሽ ያነሰ መሆኑ ነው። 

ፎቶ፦ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ፋይል

ከአርፋጮ ቀበሌ ወደ አርባምንጭ ከተማ በጀልባ ለመጓዝ አንድ ሰዓት ተኩል የሚፈጅ ሲሆን፤ በየብስ የሚደረሰው ጉዞ ግን ሶስት ሰዓት ያላነሰ ጊዜ ይወስዳል። የየብስ ጉዞ የኮንሶ ዞን እና ደራሼ ልዩ ወረዳን ማቋረጥ የሚጠይቅ በመሆኑ እና በእነዚህ አካባቢዎች ተደጋጋሚ የጸጥታ ችግሮች ሲከሰቱ በመቆየታቸው፤ የአማሮ ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች በጀልባ መጓዝን እንደ ዋነኛ አማራጭ ሲጠቀሙ ቆይተዋል።

“በግጭቶቹ መንገዱ ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ ነበር” የሚሉት የልዩ ወረዳው ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ “በችግር ጊዜ የጀልባ ትራንስፖርት ተመራጭ ነው” ይላሉ። ከአማሮ ወደ አርባ ምንጭ የሚወስደው መንገድ አስቸጋሪ በመሆኑ ምክንያት፤ ወደዚያ የሚጓዙ አሽከርካሪዎች እንደልብ እንደማይገኙም አቶ አብነት አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[ማስተካከያ፦ በዚህ ዘገባ ላይ “በአደጋው ከሞቱት ውስጥ እስካሁን የሁለት ሰዎች አስክሬን በፍለጋ መገኘቱን” የአማሮ ልዩ ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊን በመጥቀስ ዘግበን ነበር። ሆኖም በተደረገው ማጣራት የተገኘ አስክሬን እንደሌለ” ዘግይተው በመግለጻቸው በዘገባችን ላይ ማስተካከያ አድርገንበታል]