የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንዳለፈው ዓመት ሁሉ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እንደሚሰጥ ተገለጸ

በአማኑኤል ይልቃል

የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ፈተና መልቀቂያ ፈተና እንደ አምናው ሁሉ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እንደሚሰጥ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት አስታወቀ። ለዚህ ዓመት ፈተና ምዝገባ የሚካሄደው፤ ከመጪው ረቡዕ መጋቢት 20 ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 15፤ 2015 ድረስ እንደሆነም አገልግሎቱ ገልጿል። 

የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ይህንን ያስታወቀው፤ የ2015 የ12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባን አስመልክቶ ዛሬ ሰኞ መጋቢት 18 በሰጠው መግለጫ ነው። የዘንድሮው ፈተና የሚሰጥበት ጊዜ የሚወሰነው፤ ለአንድ ወር ገደማ ከሚቆየው የተማሪዎች ምዝገባ መጠናቀቅ በኋላ መሆኑን የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እሸቱ ከበደ በዛሬው መግለጫ ላይ ተናግረዋል።  

በዘንድሮው የትምህርት ዘመን አንድ ሚሊዮን ገደማ ተማሪዎች በመደበኛ እና በግል ለፈተናው ሊቀርቡ ይችላሉ ተብሎ እንደሚገመት በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል። ፈተናውን ይወስዳሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተማሪዎች ውስጥ 850 ሺህ የሚሆኑት መደበኛ እንደሚሆኑም ተገምቷል። ይሁንና ትክክለኛውን ቁጥር መናገር የሚቻለው ምዝገባው ከተጠናቀቀ በኋላ መሆኑን የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ፈይሳ አስረድተዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የተሰጠውን የ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ፈተና የተፈተኑት፤ 900 ሺህ ገደማ ተማሪዎች ነበሩ። ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 18፤ 2015 የተሰጠውን ይህን ፈተና፤ የማህበራዊ ሳይንስ እና የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች በተለያዩ ጊዜያት እንዲወስዱ መደረጉ አይዘነጋም።

የትምህርት ሚኒስቴር ፈተናው በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እንዲካሄድ የወሰነው፤ “የፈተና ስርቆት እና ኩረጃን ለመቀነስ” በሚል ነበር። በዚህም መሰረት  የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች በሚገኙባቸው ከተማዎች ያሉ ተማሪዎች በእነዚሁ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲፈተኑ ተደርጓል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካሉባቸው ቦታዎች ርቀው የሚገኙ ተማሪዎች ደግሞ፤ በአቅራቢያቸው ወዳሉ ዩኒቨርስቲዎች በመንግስት ወጪ እንዲጓጓዙ ተደርጎ ፈተናውን ወስደዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ስርዓት የዘረጋው፤ የ12ተኛ ክፍል ፈተናን ሙሉ በሙሉ ወደ “ኦንላይን” ስርዓት እስከሚቀይር መሆኑን ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ባለፈው ህዳር ወር ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ተናግረው ነበር። ይህ የፈተና አሰጣጥ አካሄድ ዘንድሮም እንደሚቀጥል የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እሸቱ በዛሬው መግለጫ ላይ አስታውቀዋል። 

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በተሰጠበት ጊዜ የታየው አንዱ ችግር፤ የተፈታኞች መረጃ በትክክል አለመሙላት እንደነበር የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር በመግለጫቸው አመልክተዋል። “ሴት እና ወንድ ብሎ መሙላት፤ የጾታ ስታትስቲክስ ማግኘት ብቻ ሳይሆን በልጆቹ የፈተና ሂደት ላይ በጣም ይረብሻል። ሴት የሆነች ልጅ ወንድ ተብላ ብትሄድ፤ ዶርም የምታገኘው ወንዶች ጋር ቢሆን በጣም ትረበሻለች” ሲሉ ከሚፈጠሩ ስህተቶች ውስጥ ማሳያ ጠቅሰዋል።

ለዚህም ሲባል የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት፤ ስለ ዘንድሮው የተፈታኞች ምዝገባ ከክልሎች አመራሮች ጋር ሲወያይ እና ለመዝጋቢዎች ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱ በዛሬው መግለጫ ላይ ተነስቷል። በዚህ ዓመት ምዝገባ የሚያከናውኑ ግለሰቦች ተፈታኞችን የሚመዘግቡት፤ በበይነ መረብ (በኦንላይን) አማካኝነት መሆኑን የተቋሙ የፈተና አስተዳደር ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንደሰን እየሱስወርቅ ገልጸዋል።

በመንግስት እና የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ መደበኛ እና የማታ ተማሪዎች ምዝገባ የሚያከናውኑት፤ በመንግስት መደበኛ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንደሚሆን አቶ ወንድወሰን አስረድተዋል። የርቀት እና የድጋሚ የግል ተፈታኞች ደግሞ በተመረጡ ወረዳዎች ውስጥ ባሉ የትምህርት ጽህፈት ቤቶች ውስጥ እንደሚመዘገቡ ስራ አስፈጻሚው አክለዋል። 

ፎቶ፦ ከፋይል የተወሰደ

የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ተፈታኞች፤ ምዝገባ በሚያከናውኑበት ወቅት ጊዜ በበይነ መረብ ካሜራ (webcam) አማካኝነት ፎቶግራፍ እንደሚነሱ አቶ ወንድወሰን አመልክተዋል። በዚህም ምክንያት ሁሉም ተፈታኞች ምዝገባውን ለማከናወን የግድ በአካል መገኘት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል። 

ምዝገባው ከተጠናቀቀ በኋላ የሁሉም ተመዝጋቢዎች ሙሉ ዝርዝር በትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲለጠፍ እንደሚደረግ የፈተና አስተዳደር ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል። ተማሪዎች ይህ መረጃ ሲለጠፍ ስህተት መኖሩን ማረጋገጥ እንዳለባቸው የገለጹት አቶ ወንድወሰን፤ መረጃው ወደ ማዕከል ከተላከ በኋላ ለሚኖሩ ስህተቶች ማስተካከያ እንደማይደረግ በአጽንኦት ተናግረዋል። ማስተካከከያ አይደርግባቸውም የተባሉት መረጃዎች፤ ከስም፣ ጾታ፣ ዕይታ፣ ፎቶ እና የትምህርት መስክ ጋር የተያያዙ መረጃዎች ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)