የሰላም እና የጸጥታ ጉዳዮች የጎሉበት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ማብራሪያ

በአማኑኤል ይልቃል እና በሃሚድ አወል

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተወካዮች ምክር ቤት በአካል ከሚቀርቡባቸው ምክንያቶች አንዱ፤ የመንግስታቸውን የመንፈቅ ዓመት የስራ አፈጻጸም በተመለከተ የፓርላማ አባላት ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ስለሚጠበቅባቸው ነው። በዚህ አሰራር መሰረት ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 19፤ 2015 በተወካዮች ምክር ቤት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለአንድ ሰዓት ተኩል ገደማ ያህል ከፓርላማ አባላት የሚቀርቡላቸውን ጥያቄዎች በቀጥታ ሲያደምጡ ቆይተዋል።

በዛሬው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ጥያቄቸውን ካቀረቡ 25 የተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል አስራ አንዱ ያነሷቸው ጉዳዮች፤ ከሰላም እና ጸጥታ ጋር የተያያዙ ናቸው። እነዚህ ጥያቄዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበሩት ስብሰባዎች ላይ ይስተዋል እንደነበረው በትግራይ ክልል ላይ ያተኮሩ አልነበሩም። ይልቁንም አብዛኞቹ ጥያቄዎች ማጠንጠኛቸውን ያደረጉት በኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች ስላሉ የጸጥታ ሁኔታዎች ነው። እንደ ክልሎቹ ሁሉ የአዲስ አበባ ከተማ ወቅታዊ ሁኔታም የፓርላማ አባላቱን ትኩረት ስቧል።፡  

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀዳሚውን ጥያቄ የማቅረብ እድል ያገኙት፤ የኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን ተመራጩ ዶ/ር አብዱሰመድ ሁሴን ናቸው። የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ተወካዩ፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት በተመረጡበት ክልል ከታጣቂ ኃይል ጋር በሚካሄደው ግጭት “በርካታ ህይወት እና ንብረት” መውደሙን ጠቅሰዋል። የኦሮሚያ ክልል መንግስት ለ“ኦነግ ሸኔ” ታጣቂ ቡድን የሰላም ጥሪ ማቅረቡንም አስታውሰዋል። 

የሰላም ጥሪው በታጣቂ ኃይሉ ተቀባይነት ቢያገኝም፤ “በሁለቱም በኩል ትርጉም ያለው የሰላም ሂደት አልተደረገም” ሲሉ ሂደቱ ወደፊት መራመድ እንዳልቻለ ዶ/ር አብዱሰመድ ገልጸዋል። ለሰላም እጦት መንስኤ የሆነውን ይህን ችግር ለመፍታት እና ተጨባጭ ሰላም ለማምጣት፤ የፌደራሉ መንግስት ምን አይነት ስትራቴጂ እየተከተለ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል። ዶ/ር ከፈና ኢፋ የተባሉ ከኦሮሚያ ክልል የተመረጡ የብልጽግና አባልም “በኦሮሚያ የሰላም ድርድሩ [መቼ] ይጀመራል ብሎ ህዝቡ በጸሎት እየጠበቀ ነው። መቼ ይጀመራል ብለን እንጠብቅ?” ሲሉ ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለሁለቱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፤ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ለ“ሸኔ” ያቀረበው ጥሪ የብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ በወሰነው ውሳኔ መሰረት የተላለፈ መሆኑን ጠቁመዋል። ከ“ሸኔ” ጋር የሚደረገውን “የሰላም ድርድር” ለመምራት በፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት የሚመራ ኮሚቴ መቋቋሙን አስታውቀዋል። “ሸኔን” በሚመለከት ባለፉት ሁለት ወር ገደማ ውስጥ “ከአስር በላይ ሙከራዎች” መደረጋቸውንም ይፋ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ማብራሪያቸው እነዚህ ሙከራዎች የሚፈለገውን ውጤት አለማምጣታቸውን ያመላከተ ገለጻም ተጠቅመዋል። “ያስቸገረው ነገር አንድ የተሰባሰበ ኃይል ባለመሆኑ፤ የምንነጋገርባቸው ኃይሎች የተለያዩ ሀሳብ እና አቋም ይዘው ስለሚመጡ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል። ይህም ሆኖ መንግስታቸው በሀገሪቱ ከሚገኙ ከሁሉም የታጠቁ ኃይሎች ጋር ያለውን ችግር፤ በንግግር የመፍታት አቋም መያዙን ተናግረዋል።

አብይ በዛሬው የፓርላማ ውሏቸው፤ ራሳቸውም እና የሚመሩትን መንግስት በተመለከተ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል። እንዲህ አይነት ጥያቄዎች ካቀረቡ የፓርላማ አባላት መካከል፤ በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን በለሳ ምርጫ ክልልን ወክለው የተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ጀምበር አያልነህ አንዱ ናቸው።

እኚሁ የብልጽግና ፓርቲ ተመራጭ “መንግስት ሀገሪቱን ለማፍረስ አቅዶ እየሰራ ይገኛል” የሚል ሀሳብ በተደጋጋሚ እንደሚደመጥ እና ይህ ሀሳብ “በበርካታ ህዝብ እና አመራሮች” ጭምር ተቀባይነት እያገኘ መሆኑን ጠቅሰዋል። “በእርግጥ እንደሚባለው መንግስት ኢትዮጵያን ለማፍረስ አቅዶ እየሰራ ነው ወይ? በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ክህደት ፈጽሟል ወይ?” ሲሉም ጥያቄ አቅርበዋል። 

ሌላኛው ጠንካራ ጥያቄ የቀረበው በምዕራብ ጐጃም ዞን ከቋሪት ምርጫ ክልል ከተወከሉት ከአቶ ክርስቲያን ታደለ ነው። የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራር የሆኑት አቶ ክርስቲያን “አሁን ላይ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የዜጎች ደህንነት እና የሀገር ሉዓላዊነት ዋነኛ ስጋት ምንጭ ሆኖ የምናየው እርሶ የሚመሩትን መንግስት ነው” የሚል ወቀሳ ሰንዝረዋል። “እርስዎ በአፍዎ ‘ኢትዮጵያ አትፈርስም’ ቢሉንም በተግባር ግን ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት በመንግስትዎ እየተናዱ ነው” ሲሉም ተችተዋል።  

በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች ሀገራት ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ መሪዎች ስልጣናቸውን የሚለቁበት ልምምድ መኖሩን የጠቀሱት አቶ ክርስቲያን፤ “እርስዎስ ስልጣንዎን በመልቀቅ የመፍትሔ አካል ለመሆን አላሰቡም ወይ?” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጭምር ያስፈገገ ጥያቄ  አቅርበዋል። የፓርላማ አባሉ አክለውም “በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ እንዲሁም በማንነት ተኮር የዘር ማጥፋት፣ የዘር ማጽዳት እና የማንነት ማሳሳት ወንጀሎች ተጠያቂ ለመሆን ምን ያህል ዝግጁ ነዎት?” ሲሉ ጠይቀዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመሩት መንግስት ላይ የቀረቡትን ክሶች እንደማይቀበሉ በምላሻቸው ገልጸዋል። በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሀገሪቱ እንዳትፈርስ “መንግስት መስዋዕትነት” መክፈሉን አብይ በማሳያነት አንስተዋል። “መንግስት ኢትዮጵያን አንድ ማድረግ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያን ሊያፈርስ ነው የሚሰራው የሚል ጥያቄ የተነሳው፤ በጥያቄ ደረጃ የተከበረ ጥያቄ ነው። ግን የዓመቱ ምርጥ ቀልድ አድርጌ ነው የምወስደው” ሲሉም ጥያቄውን አጣጥለዋል።

“ ‘አስባችሁ ነው የምታፈርሱት’ ከሆነ ማን አቆመን ታዲያ? እኛ ሀገር ለማፍረስ የምንሰራ ከሆነ፤ ማነው ሀገር ሊከላከል የሚያቆመን ኃይል?” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠያቂዎቻቸውን ጠይቀዋል። ባለፉት ዓመታት በመከላከያ ሰራዊት እንዲሁም የደህንነት እና የፖሊስ ተቋማት “መገንባታቸውን” በማንሳትም እነዚህ ስራዎች “ሀገር ለማጽናት ያለንን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው” በማለት መንግስታቸውን ተከላክለዋል። “የኢትዮጵያ የመፍረስ ስጋት አልፏል” ሲሉ ለፓርላማ አባላት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከእንግዲህ በኋላ እንደዚህ አይነት ስጋት እኛ የለንም” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

እርሳቸው የሚመሩት መንግስት “ኢትዮጵያን ሊበትን ይፈልጋል። ወይም አንዳንዴም ይገነጥላል” የሚል ሀሳብ እንደሚነሳበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ላይ ጠቅሰዋል። “አሁን በግድ ኦሮሞዎች ትገነጥላላችሁ የሚለውን ስቃዩን እንተወው። አንገነጥልም፤ ኢትዮጵያን ስለምንፈልጋት። እሱን ትተን እንዴት በጋራ the new normal ተቀብለን ተግባብተን social contract ኖሮን እንኖራለን ብለን ብንወያይ ነው የሚሻለው” ብለዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከአብኑ አቶ ክርስቲያን ለቀረበላቸው ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽም ሰጥተዋል። “ስልጣንህን ብትለቅ የተባለው በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። ግን ጥሩ የሚሆነው ስልጣን ብንለቅ [ቢባል ነበር]” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ጠያቂውንም ሆነ ሌሎችን የፓርላማ አባላትን አስፈግጓል። አብይ በዚሁ ምላሻቸው ህግ አውጪ፣ አስፈጻሚ፣ እና ተርጓሚ አካላት በመንግስት ውስጥ የስልጣን ድርሻ እንዳላቸው አውስተዋል። “የሁሉ ችግር ምንጭ እና ባለቤት እኔ ብቻ ልሆን አልችልም። ኃላፊነት ከወሰድንም በጋራ ቢሆን ጥሩ ይሆናል ብዬ አስባለሁ” ሲሉም አክለዋል። 

አብይ በዛሬው ንግግራቸው፤ ስልጣን የሚገኘው እና የሚለቀቀው “በምርጫ ብቻ ነው” የሚለውን ሃሳብ በተደጋጋሚ እና በአጽንኦት ሲያነሱ ተደምጠዋል። “ስልጣን በኮሮጆ እንጂ በመናጆ አይያዝም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የሶስት ዓመት የስራ ጊዜ እንደሚቀረው አስታውሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለት ሰዓት ገደማ የፈጀ ማብራሪያቸውን ሲያጠናቅቁም ይህንኑ ሀሳብ ደግመው አንስተውታል። የተከበረው ምክር ቤት ሶስት ዓመት አላችሁ። በዚህ ሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ጠንክረን ውጤት ለማምጣት እንስራ። ከዚያ በፊት የሚታሰብ ማንኛውም ነገር አይሆንም” ሲሉ ማስጠንቀቂያ አዘል ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።  

በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ፤ ከፓርላማ አባላት ጥያቄ ቀርቦበት ምላሽ ያገኘው ሌላው ጉዳይ ከሀገሪቱ መዲና አዲስ አበባ ጋር የተያያዘ ነው። አቶ እጅጉ መላኬ የተባሉ የምክር ቤት አባል፤ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ተጓዞች “በመግቢያ በሮች በመታገት ለከፍተኛ ወጪና እንግልት እየተዳረጉ እንደሚገኙ” ተናግረዋል። “ችግሩ በተከሰተበት ክልል አመራሮች ላይ የህዝብ ጫና እያረፈ” መሆኑንም ጠቁመዋል። ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ወክለው ከአማራ ክልል የተመረጡት እኚሁ የፓርላማ አባል፤ “ይህን ሁኔታ መልክ ለማስያዝ በመንግስት በኩል ያለው ፍላጎት ምን እንደሆነ ቢብራራልን” ሲሉ ጠይቀዋል።

ወይዘሮ ስመኝሽ ሳህሉ የተባሉ ሌላ የምክር ቤት አባልም፤ ከአማራ ክልል “በተለይ ወጣቱ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገባ ይታገታል” ሲሉ ተመሳሳይ አስተያየት ሰንዝረዋል። “ታመው ሪፈር ወደ አዲስ አበባ የተጻፉ ህመምተኞችም፤ ሳይደርሱ ቀርተው በመንገድ ሞተዋል” ሲሉ የጉዳዩን አሳሳቢነት በማሳያ አስደግፈው አስረድተዋል። የሰብል ምርት ወደ አዲስ አበባ እንዳይገባ መደረጉ እና በመንገድ ላይ ዘረፋ መካሄዱ፤ በአዲስ አበባ ለተከሰተው የኑሮ ውድነት አንዱ ምክንያት መሆኑን የፓርላማ አባሏ ገልጸዋል። ይኸው የመንገድ መዘጋት የአማራ ክልል አርሶ አደር እና ነጋዴ ግብይቱን እንዲያቆም እንዳደረገውም አክለዋል።

ከቦታ ቦታ መዘዋወር ላይ ያሉ ችግሮችን በተመለከተ ለተነሱት ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፤ ዜጎች በነጻነት ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ የመዘዋወር እና ሰርቶ የመለወጥ መብት እንዳላቸው አንስተዋል። ወደ አዲስ አበባ ከተማ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱንም ጠቁመዋል። “አዲስ አበባ ውስጥ በዚህ ሁለት ዓመት ያለው ፍልሰት፤ አምስት፣ ስድስት ዓመታት ከነበረው ይበልጣል” ሲሉም ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ከተማ ያለው ችግር ከሰዎች ፍልሰት መጨመር ባሻገር፤ የጸጥታ ስጋትን የያዘ ነው ባይ ናቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ።  

“ ‘አዲስ አበባን የብጥብጥ ማዕከል ማድረግ አለብን። አዲስ አበባ ውስጥ ሁከት ካላስነሳን በቀር በቀላሉ መንግስትን መነቅነቅ እና ስልጣን መያዝ አንችልምʼ የሚሉ በአገር ውስጥ እና በውጭ ያሉ ኃይሎች፤ በተቀናጀ መንገድ በርካታ ሙከራዎች ሲያካሄዱ ቆይተዋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ መንግስታቸው ይህን ለመከላከል “ሰፊ ስራ” መስራቱን እና ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል። 

በእነዚህ ስራዎች አፈጻጸም “የሚበላሹ ጉዳዮች” መኖራቸውን ያነሱት አብይ፤ “ነገር ግን ምንም መረጃ ሳይኖረን የሰራናቸው ስራዎች አይደሉም” ሲሉ ውሳኔውን በግብታዊነት የመጣ እንዳልሆነ ሞግተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም “በስፋት መረጃዎች እናገኛለን። ከዚያም ተነስተን ግጭት ለማስቀረት በሚደረጉ ስራዎች ስጋት እንገታለን” ሲሉ መንግስታቸው በሰራው ስራ የተገኘውን ውጤት አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)